>
5:26 pm - Tuesday September 17, 3039

ይብላኝ ለእናንተ....!!! (ክርስቲያን ታደለ)

ይብላኝ ለእናንተ….!!!

ክርስቲያን ታደለ

 
*… «እየታጀቡ ስለሆነ እርምጃ እንወስዳለን» ብሎ ማለትስ ከምቀኝነትና ቅናት በምን ይለያል? «ሚስትህ ከሚስቴ በላይ ቆንጆ መሆን የለባትም» ከማለትስ በምን ይለያል? ሰባኪዎችንና አክቲቪስቶችን በሪፐብሊካን ጋርድ የሚያሳጅብ ባለሥልጣንስ እንዲህ መቅናት ይቻለዋልን?
**      **
ዓሳ ስለውኃ ያለው አረዳድ ከኮረት ጋር ተመሳሳይ ሲሆን እጅጉን በጣም አስገራሚ ይሆናል። ፋኖነትን ማኅበረሰባዊ ውርስ እና የልቡና ውቅር እሴት አድርጎ ለሺህ ዘመናት በኖረ ማኅበረሰብ ውስጥ ያደገ ሰው፤ በተለይ በስነሰብ ጥናት ላይ የሊቅነት ካባ የደረበ ሰው፤ ፋኖነትን በመንገደኛ ቅኝት (etic perspective) ተንትኖ ብያኔ ሲሰጥ አንዳች የተበላሸ ነገር ስለመኖሩ ከእርግጠኝነትም በላይ  ጠቋሚ ነው።
የታጠቀ ኃይልን በብቸኝነት የማንቀሳቀስ መብት የሚያጎናጽፈው የመንግስትነት ካባም የሕዝብን ትውልድ ዘለል እሴት «ኢመደበኛ» በሚል ሰም ለበስ ፍረጃ ለምን የሚሉ የነቁ–የበቁ ሰዎቻችንን ያሹትን እርምጃ ለመውሰድ መብትን የሚያጎናጽፍ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። ፋኖነትን ከወደረኝነትና አቻ መንግስትነት እየተነተኑና እያስተነተኑ ሌት ተቀን የሚያላዝኑ ጥቂቶች በእርግጥም ስለሰላምና የተረጋጋ መንግስታዊ ሥርዓት የሚገዳቸው ሆነው ሳይሆን ከርሳቸውን ለመሙላት የሚያደርጉት አደግዳጊነት ተለምዷዊ ግብራቸው ነው።
ሆነ ተብለው ተቀርፀው በሚወርዱ አጀንዳዎች ሕዝባችን እርስ በርሱ እየተናቆረ ማኅበራዊ ረፍት አጥቶ በአገራዊና ቀጠናዊ ፖለቲካ ትኩረት እንዳያደርግ በርካታ ወጥመዶች መኖራቸው እሙን ነው። በመንግስት የእለት ተእለት ተግባር ላይ አንዳችም እክል ባልፈጠሩ፤ እንዲያውም የአገር አንድነትና የሕዝብ ደኅንነት አደጋ በወደቀበት ጊዜ ሁሉ ሕይወታቸውን በሰጡን ወንድሞቻችን ላይ የሚደረገው ውርክቢያና ማሳደድ በምንም አመክንዮ ከልክነት የጎደለ ነው።
«አመደበኛ» ተብለው ተፈርጀው እርምጃ እንደሚወሰድባቸው የሚዛትባቸውና የሚሳደዱ ወንድሞች፤
በትክክል ምን የሕግ መተላለፍ ፈፀሙ?
በሕግ መተላለፉስ ጉዳት የደረሰበት ግለሰብ ወይ አካል አለወይ?
ጉዳቱ መቼ ደረሰ?  ጉዳቱስ ምንድን ነው?
ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ማቅረብ ስለመቻላቸው እርግጠኛ አይደለሁም። በእርግጥም ሕፃን ያገተ፣ ንጹኃንን የገደለ፣ የሰረቀ፣ መንግስታዊ ሥራዎች እንዳይከናወኑ ያወከ፣ በዜጎች የእለት ተእለት ኑሮ ላይ መቃወስን የፈጠረ፣…ካለ በማስረጃ ተደግፎ ይቅረብልንና እኛም አብረን እናውግዝ። ማውገዝ ብቻ ሳይሆን መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ጭምር  በሁሉም አዎንታዊ ተሳትፎዎች በጋራ እንቁም።
ጉዳዩ «ሳይዘምቱ ዘምተናል ብለዋል፤ ያላስለቀቁትን ቦታ አስለቅቀናል ብለዋል» የሚል የትግል ተሳትፎ ኦዲት ከሆነ፤ የቀረበው ክስ እውነት እንኳን ቢሆን ከነቀፌታ በዘለለ መንግስታዊ እርምጃ እስከመውሰድ የደረሰ አቋም የሚያስይዝ አይሆንም። በተነሳው ጭብጥ ላይ መወቃቀስ ከተጀመረም ጉዳዩ በአመዛኙ በወቃሽ ነኝ ባይ ቢበረታ እንጂ የሚያንስ አይሆንም። ሕዝባችን ይህን ሁሉ ውርደትና ፍዳ ያየው ወቃሾች የተሰጣቸውን መንግስታዊ ኃላፊነት መወጣት ባለመቻላቸው እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብን ይሆን? «እየታጀቡ ስለሆነ እርምጃ እንወስዳለን» ብሎ ማለትስ ከምቀኝነትና ቅናት በምን ይለያል? «ሚስትህ ከሚስቴ በላይ ቆንጆ መሆን የለባትም» ከማለትስ በምን ይለያል? ሰባኪዎችንና አክቲቪስቶችን በሪፐብሊካን ጋርድ የሚያሳጅብ ባለሥልጣንስ እንዲህ መቅናት ይቻለዋልን?
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንድን አካባቢ በተለዬ ሁኔታ የማጥላላት፤ በተናበበና በተቀናጄ ሁኔታ የማጠልሸትና የማኮሰስ አዝማሚያዎችን እያየን ነው። ምቀኝነትና ቅናት አፍ አውጥተው እስኪናገሩ ድረስ ሰነድ ተሰንዶ፤ ወንዝ ዘለል አሰላለፎች ተዘርግተው፤ የሆነ አካባቢ ፖለቲከኛ፣ ባለሀበት፣ ወጣት፣ ልኂቅ፣…ሕዝባችን… ላይ የማያባሩ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻዎች እየተሰሩ ነው። ለአገር አንድነትና ለሕዝብ ደኅንነት የዋለው ሁሉንአቀፍ ውለታ ከማንም ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ ሳይሆን ተሳትፎውን የማኮሰስ፤ መስዋእትነቱን የማራከስ፤ ሁኔታዎች ታዝበናል። ፍርኃትና የበታችነት ስሜት ያደረባቸው ክንቱዎች ራሳቸውን መንግስትን ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም የወርቅ ሚዛን አድርገው አቅርበው ሰነድ አዘጋጅተው ጭምር ዘመቻ መክፈታቸውን ካወቅን ውለን አድረናል። አፍ እንጂ ጭንቅላት ስለሌላቸው፤ የእለት ጉርሳቸውን እንጂ የነገውንም ማሰብ የማይችሉ ጥርቅሞች ስለሆኑ፤ «ቅና ያለው በእናቱ ይቀናል» ብለን ንቀን ትተናቸው ነበር። ይኼ የቅናትና ምቀኝነት የጠመናሂ እሳቤ (scarce mentality) መንግስታዊ መዋቅር ተደግፎ ሲመጣ ግን በእርግጥም ያስደነግጣል። ሕዝባችን ወጥመዱን በእርግጠኝነት ይሻገረዋል። በኃቃችንም ውሸታችሁን እንደበረዶ እናቀልጠዋለን። ስኬታችንን ከማጨናገፍ ይልቅ ሰማይን ያህል ዳንቴል ሰርታችሁ ፀሐይን መከለል ይቀላችኋል። ወንድማማችነትን ለከርስ መሙያ ሸቀጥ ከሚያውል ይሁዳ ጋር የምንጋራው አንዳችም  ጉዳይ ግን አይኖረንም።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ልጆቿን ይባርክ!
Filed in: Amharic