“ሸኔን በሪፖርት፣ ፋኖን በጥይት አይሆንም እረ አይሆንም…!!!”
አሳዬ ደርቤ
*… ለህልውናው የሚታገለውን ፋኖ ለማጥቃት ከማሰብ አስቀድሞም የንጹሐንን ሕልውና ሲነጥቅ ከርሞ በሪፖርት የተደመሰሰው አሻባሪ ላይ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ ግድ ይላል፡፡
አራዳው ብልጽግና በሥሙ ሲጠሩት ‹‹አቤት›› ባይ አመራር የሌለው የሽብር ድርጅት እውን አድርጎ የንጹሐንን ሐብትና ሕይወት ሲያስወድም ከረመ፡፡
ከሰሞኑም ከጌጃው ብልጽግና ጋር ባደረገው ስብሰባ ፋኖን ከመምታት በፊት ሸኔን ደምስሻለሁ ማለት እንደሚቀድም ተረድቶ በታጣቂው ፈንታ ተጠቂው ላይ በወሰደው እርምጃ የቀማቸውን መሣሪያዎች ሲያሳየን ነበር፡፡
ከእነዚህም መሣሪያዎች መሃከል አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ማንገቻ ያለው ቁመህ ጠብቀኝ ጠመንጃ ቀላቅሎ ‹‹ከሸኔ ያስፈታኋቸው ናቸው›› እያለ ሲነግረን ነበር፡፡ ከዚህ ባለፈም ‹‹21 የሸኔ ታጣቂዎች እጅ ሰጡ›› በሚል ዜና 28 መንገደኞችን የያዘ ፎቶ ለጥፎ ‹‹ሰባቱ እግር የሰጡ ናቸው ወይ?›› የሚል ትችት ሲያስተናግድ ነበር፡፡
ያ ሁሉ ልፋት ታዲያ፣ አሸባሪው ሃይል አፋር ገብቶ ቅልጥ ያለ ትግል እያደረገ ባለበት ሁኔታ ‹‹ድል አድርጌያለሁ›› ብሎ የተመለሰው አካል፣ ፋኖን መትቶ አማራን ለዳግም ጥቃትና ለባርነት ከመዳረግ የሚመነጭ ነው፡፡ ኦነግ በሪፖርት ሲደመሰስ የከረመው የፋኖን ደም በጥይት ለማፍሰስ ነው፡፡ ኢ-መደበኛ ሃይል የተባሉት አሁንም ድረስ ሕያው ሆነው የንጹሐንን ሕይወት በመቅጠፍ ላይ የሚገኙት አሸባሪዎች ሳይሆኑ ‹‹የመጣብህ ጠላት በመደበኛው የጸጥታ ሃይል የሚመከት ስላልሆነ ተነስና ለህልውናህ ታገል›› በሚል የክተት ጥሪ በእራሱ ስንቅና ትጥቅ ሲዋጋ የከረመው ፋኖ ነው፡፡
የሆነው ሆኖ ግን
ፋኖ ላይ ጣትን ከመቀሰር በፊት ድል በሚል ሥም መሃል መንገድ ላይ የተቋረጠውን ትግል መቋጨት ያስፈልጋል፡፡
ለህልውናው የሚታገለውን ፋኖ ለማጥቃት ከማሰብ አስቀድሞም የንጹሐንን ሕልውና ሲነጥቅ ከርሞ በሪፖርት የተደመሰሰው አሻባሪ ላይ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ ግድ ይላል፡፡
ያን ጊዜ ኢመደበኛውም ሆነ መደበኛው ፋኖ እርምጃ ሳትወስዱበት በፊት ነፍጡን ጥሎ ማረሻውን እና ደብተሩን ያነሳል፡፡
ከዚህ ውጭ ግን መላው የአማራ ሕዝብ በወራሪ ጠላት እና በቆማሪ መንግሥት መሃከል ወድቆ እየዋተተ ባለበት ሁኔታ፣ ፋኖ ላይ የሚወሰድ እርምጃ፣ የሥልጣን ስጋት ከመሆን አልፎ ለባለሥልጣናት ምቾት የሚፈጥር ስላልሆነ የክልሉ መንግሥት ችግሩን በውይይት እንዲፈታው እንመክራለን፡፡