ምንዳርአለው ዘውዴ
*….. “አምባገነኖች ድንቁርና ወለድ ንግግር፣ ዘር ተኮር ዲስኩር፣ ደም ጠሜ እለላ (ማናፋት) ባሽኳለሉ ቁጥር ተዉ አይሆንም፣ ተዉ ይህ መንገድ ገደል ይከተናል እንደማለት ታላቅ ንግግርዎ፣ ሚሌኒየም ሰበር ራዕይዎ፣ ጥልቅ እይታዎ፣ ሳይንሳዊ እዉቀትዎ፣ ማር-ዘነብ አፍዎ፣ ድል በሰር ቃልዎ፣ ስርቅርቅ ድምጥዎ፣ ምናሊዛ መልክዎ እያሉ በበገሰማይ ኑክሊየራቸዉ (በጭባጨባቸዉ) እያጀቡ ነዉ ሀገራችንን ከድጡ ወደማጡ እንድትንሸራተት የሚያደርጉት።
*…. ከህሊናው የተሰደደ ሰው እዳውን በሀገርና በወገን እጣ ፈንታ ላይ ነው የሚያወራርደው…?!!?
ብዙ አምባገነን እና ኋላ ቀር የአለማችን አገዛዞች እንመራሃለን የሚሉትን በሚሊየን የሚቆጠር ህዝብ ለረሃብና ቸነፈር፣ ለጥማትና ችጋር አጋልጠዉ የሚላስ የሚቀመስ ለምስኪን ህዝባቸዉ ከማቅረብ ይልቅ ላሞሌ ጌቶቻቸዉ ( ብድርና እርዳታ ለሚሰጧቸው) በጆሮ የሚበላ የህዝብ ግንኙነት ቀለብ ይሰፍራሉ።
የህዝባቸዉን ነፍስ ለማቆየት የሚያስችለዉን ኩርማን ከማፈላለግ ይልቅ፣ ህዝቡ የሚልስ የሚቀምሰዉን ነገር ከማፈላለግ ይልቅ ለረሃቡ ማስተባበያ ሰበብ አደን ይወጣሉ። ሰበብም ይታደናል፣ ሰበብ ተይዞ ከቤት ይገባል፣ ሰበብ ይጠበሳል፣ ሰበብ ይበላል። ረሃብም ህዝብን ያለከልካይ በቁሙ ይበላል።”
“ሰው በአምባገነኖች ቀኑ ዳምኖ ነገው በዛሬው ጨክኖ፣ ቀን በሰጣቸው ቅሎች የተነፈከተ አለት ሆኖ፣ ከቄዬው ሊሰደድ፣ ካገሩ ሊርቅ ይገድድ ይሆናል፡፡ ይህም ጤናማ ህሊና ባለው ሰው ሁሉ ላይ ያለ ነው፡፡
ሠው ኑሮን ለማሸነፍ፣ ከርኀብና እርዛት ጨካኝ ሰይፍ ለመትረፍ፣ ከምጣኔያዊ ቁርቁዘት ለማምለጥ፣ የዘመንን እበት የቀንን ገንገበት ለመብለጥ፣ ከጊዜ አተላ ሽታ ከፍትህ እጦት ዝቅታ ለመትረፍ፣ ካገሩ ሊሰደድ ይችላል፡፡ ይቺም በጤናማ ሰው ያለች ናት፡፡
ሰው ባገሩ በገነነ የእርስ በእርስ ውጊያ ሳቢያ፣ ከደም ጠሜ የጦር አበጋዞች የጦስ ዶሮነት ለማምለጥ፣ ተምሬ እተልቃለሁ ብሎ፣ ነግጄ እከብራለሁን ተስሎ ካገሩ ይሰደድ ሆናል፡፡ ይህ ሁሉ የስደት አይነት እንደየጊዜው ንፋስ፣ እንደየዘመኑ እስትንፋስ፣ እንደየዘመን ጌኛው የኮርቻ ግላስ፣ አንደመጻፊያው አሊያም እንደመግደያው እርሳስ በሰው ልጆች ላይ ሊደርስ ይችላል፡፡
ይህ ሁሉ የስደት አይነት አንድ እጅግ የሚያመሳስለው ነገር አለ፡፡ ሁሉም ተሰዳጅ እዳው በራሱ ነው፡፡እዳውን ራሱ ለመክፈል ወስኖ የሚገባበት የህይወት ውሳኔ ነው፡፡
ነገር ግን፣ ሰው ከራሱ ህሊና ሲሰደድ የምናገኘው የስደት አይነት ከስደቶች ሁሉ እጅግ የከፋው ነው፡፡ ይህ የስደት አይነት እጅግ የከፋው የስደት ገጽ የሆነበት ምክንያት እዳው በተሰዳጁ ላይ የሚቀር ባለመሆኑ ነው፡፡ ከህሊና መሰደድ እዳው ለሀገር ነው፡፡ ከህሊናው የተሰደደ ሰው እዳውን በሀገርና በወገን እጣ ፈንታ ላይ ነው የሚያወራርደው።”