>

የአማራን ህዝብ የዘር ፍጅት ለምን ማስቆም አልተቻለም? ( ሸንቁጥ አየለ)

የአማራን ህዝብ የዘር ፍጅት ለምን ማስቆም አልተቻለም?

ሸንቁጥ አየለ

*…. የአማራ ህዝብ መዳን እንዳለበት በአማራ ላይ የታወጀዉ የዘር ፍጅት ስሩ ተቆርጦ መጣል እንዳለበት ሁላችንም በአንድ ሀሳብ እንስማማለን::
*…. ጥያቄዉ ግን በምን ስም ተንቀሳቅሰን በኦሮሚያ:በደቡብ:በጋምቤላ :በቤኒሻንጉል : በአዲስ አበባ እንዲሁም በመላ ሀገሪቱ ያለዉን አማራ እንዴት በአንድ አንቀሳቅሰን ለድል እናብቃዉ የሚል ነዉ:: በኔ እይታ አማራዉን ተደራጅ በምንልበት ጊዜ የሚከተሉት መሰረታዊ እዉነታዎችን ያገናዘበ አካሂያድን አስበን ተደራጅ ልንለዉ ይገባል::
1ኛ.በዙሪያዉ ያሉ/ቢያንስ የአማራን ነገድ እንደ ጠላታቸዉ የማይመለከቱ/ሌሎች ነገዶች አብረዉት ባይደራጁ እንኳን በጠላትነት እንዳይነሱበት የሚያስችል ሁኔታን ግንዛቤ ዉስጥ ልናስገባለት ይገባል::
2ኛ.ከአማራ ክልል ዉጭ ያለዉ የአማራ ማህበረሰብ በአሰፋፈሩ:በጋብቻዉ እና በአነበረዉ ስነልቦናዊ ጭብጡ የተነሳ ከሌሎች ነገዶች በቀጥታ የሚነጥለዉን ብሎም በአማራነት ብቻዉን ተነጥሎ መደራጀትን እሽ አይልም::ተደራጁ ብሎ መቀስቀስ አንድ ነገር ነዉ::ግን ህዝብ እሽ ብሎ መደራጀቱ ደግሞ ሌላ ነገር ነዉ::
3ኛ .  ከአማራ ክልል ዉጭ ያለዉ 51% አማራ የተማረዉ:ሀብት እጁ ያስገባዉ እና ለብዙ ዘመናት መንግስትን በመዘወር የኖረ በሚኖርባቸዉ አካባቢዎች የማህበረሰቦች አጠቃላይ ቅቡልነት ያተረፈ ህዝብ ነዉ::ይሄ ህዝብ እራሱንም ኢትዮጵያን ለማዳን በአማራ ክልል ከሚኖረዉ የአማራ ማህበረሰብ እኩል ጉልበት:አቅም እና ፍላጎት ያለዉ ህዝብ ነዉ::ሆኖም እንዲደራጅ ሲጠዬቅ የቆመበትን ተጨባጭ እዉነታ ያገናዘበ አካሂያድ የግድ ሊቀርብለት ይገባል::አንዳንድ ተቃዋሚዎች አሁን አሁን እንደሚሉት እንዲሁም የብ አዴን ዉሾች እንደሚመስላቸዉ ይሄ ከአማራ ክልል ዉጭ የሚኖረዉ ጉልበት የሌለዉና ጥቂት ቁጥር ያለዉ ደካማ ህዝብ አይደለም::
4ኛ. ብዙ ጊዜ ሌላዉ ስለ አማራ መደራጀት ሰዎች ንፅጽር በሚሰሩበት ጊዜ የአማራን ህዝብ ከትግሬ ማህበረሰብ ጋር በማነጻጸር የአማራን ህዝብ ሁኔታ ያለመረዳት አካሂያድ አለ::ለምሳሌ የትግራይ ህዝብ ተሰባስቦ የሚገኘዉ በአንድ በትግራይ ክፍለ ሀገር ነዉ::ስለዚህ ትግሬን ያሰባሰበዉ ከብሄር ማንነቱ በተጨማሪ የክፍለሃገራዊ አቀማመጡ ነዉ::የአማራ ህዝብ ግን ከትግሬ ህዝብ የተለዬ እዉነታ የተላበሰ ህዝብ ነዉ::የአማራ ህዝብ በመላ ሀገሪቱ የሚገኝ ህዝብ ከመሆኑም በተጨማሪ በመላ ሀገሪቱ ያለዉ ጉልበት እጅግ ግዙፍ ነዉ::
5ኛ.አንዳንድ ሰዎች:ድርጅቶች እና ተማርን የሚሉ የአማራ ፖለቲከኞች እኛ ስለ ኢትዮጵያ አያገባንም::ማዳን ያለብን አማራን ብቻ ነዉ ብለዉ በአደባባይ ይናገራሉ::ሆኖም እኛ የተማርን ሰዎች ካሁን ብኋላ ኢትዮጵያ የሚባል ስም/ሀገር ይፍረስ/ አያገባን የሚል አቋም ብናራምድ እንኳን ህዝቡ ከተጨባጭ ሁኔታ/ከተጨባጭ ኑሮዉ/ የተነሳ ይሄን አይነት ሀሳብ ፈጽሞ አይቀበለዉም ብቻ ሳይሆን እኛኑ በልዩ ልዩ መልክ ይዋጋናል::
6ኛ. አንዳንዶች ደግሞ የአማራን ጥንታዊ ግዛቶች ይዘን ሀገር ሆነን መኖር አለብን ይላሉ::ከምሬታቸዉ እና በአማራ ህዝብ ላይ ከሚደርሰዉ መከራ አንጻርም ፈጾሞ ሌሎች ነገዶች ጋር መኖር ማለት የአማራን ነገድ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስጠፋት ነዉ ይላሉ::ሆኖም ችግሩ የሚነሳዉ “እሽ የአማራ ሀገር የምትሉትን ካርታ ሰርታችሁ አምጡ” ሲባሉ ነዉ::የብ አዴን የበታችነት በሽታ የዋጣቸዉ የአማራ ብሄረተኞች 51% አማራዉን ያገሉና የአማራ ሀገር የሚሉት ወያኔ የአማራ ክልል የሚለዉን ነዉ::እናም ይሄን ካርታ ሰርተዉ ይዘዉ ከች ይላሉ::በአለም ላይ 51% የህዝብ ብዛቱን ሜዳ ላይ በትኖ ሌላ ሀገር ለመስራት የሚደረግ የድንቁርና ትግል በጣም ያሳፍራል::ሌሎች ደግሞ የዓማራ ሀገር የሚሉትን በካርታ ላይ ሲያሰፍሩት ከሞላ  ጎደለ አሁን ያለችዉን የኢትዮጵያን ካርታ የሚያጠቃልል ይሆናል::ይሄ ደግሞ ሌላ ጣጣ ነዉ::አሁን ያለችዉን ኢትዮጵያ የአማራ አዲስ ሀገር ከምታደርግ ታዲያ አሁን ያለችዉን ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከጠላቶችህ እጅ ነጥቀህ እጅህ አታስገባም የሚል ጥያቄ ሲጠዬቁ መልስ የላቸዉም::
7. አማራ ሲባል ከክልሉ ዉጭ ያለዉን 51% አማራ እያገለሉ ጎንደር:ጎጃም:ሸዋ እና ወሎ ላይ የማተኮር ከፍተኛ አባዜ ዉስጥ ገብተናል::ሌላዉ ቀርቶ አዲስ አበባ ላይ ከ65% እስከ 70%  የአማራ ማህበረሰብ ሆኖ ሳለ በአማራ ስም መሰባሰብ በሚደረግበት ጊዜ ስለዚህ ህዝብ አያገባኝም የሚል ግልጽ ንግግሮች ሰምተናል:: እና አማራን ማዳን ሲባል 51% አማራን ለተጨባጭ ትግል የማያነሳሳ ተጨባጭ እንቅስቃሴ እንዴት ማድረግ ይቻላል?
8. ብዙዎች ደግም አሁን የአማራ ክልል የሚባለዉ ላይ ብናተኩር እና እሱን ለድን ብናበቃዉ ቀሪዉን አማራ ማዳን እንችላለን የሚል ሀሳብ እያራመዱ ነዉ::
በኔ ሀሳብ ይሄ ስህተት ነዉ::
9. እንዴዉም አንዳንዶች ወደ ክፍለ ሃገር ሁሉ በመሄድ ይሄኛዉ ክፍለ ሀገር ቀድሞ ከዳና ሌሎችን ያድናል::ስለዚህ እዚህኛዉ ላይ ብናተኩር የሚል ሀሳብ አላቸዉ::
ይሄም ስህተት ነዉ::
10. ለሰላሳ አመታት ከኦሮሞ አክራሪ ፖለቲከኞች እና ከትግሬ አክራሪ ፖለቲከኞች ጋር በመተባበር እስከ ዛሬ ድረሰ የአማራ ህዝብ ዋና ጠላት እና አሳራጅ የሆነዉ ብአዴን  እዉነተኛ የአማራ ፖለቲከኞችን እና ምሁራንን ብሎም ባለሀብቶችን ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ በአማራ ብሄረተኝነት ስም ማታለል ችሏል::ሌላዉ ቀርቶ ከክልሉ ዉጭ ያለዉን የአማራ ሙሁር እና ፖለቲከኛም እንዲሁም ባለሀብት  በሀሰተኛ ተስፋ አታሎታል::ከክልሉ ዉጭ ያለዉ አማራ የሚመስለዉ ብአዴን የተባለ ስብስብ ተጠናክሮ አንድ ቀን እንደሚታደገዉ ነዉ::ሆኖም የብአዴን ቁልፍ  ፍልስፍናዉ ከአማራ ክልል ዉጭ ያለዉን አማራ ወራሪ ነዉ:እሰዉ ሀገር የሄደ ነዉ የሚል አቋም ያራምዳል::ይሄንንም አቋም ያሲያዙት ርክስ መንፈስ የተጠናወታቸዉ አክራሪ የትግሬ ፖለቲከኞች ናቸዉ::አክራሪ የትግሬ ፖለቲከኞች ለአማራ ህዝብ ካላቸዉ ጥላቻ የተነሳ ኢትዮጵያ የሚባለዉ ሀገር የራሳቸዉ ሀገር እንዳልሆነ ሁሉ በመስበክ በራሳቸዉ ህዝብ ላይ ጭምር ክህደት ሰርተዋል::ይሄንኑ ክህደታቸዉንም ለብአዴን አስተምረዉ ከአማራ ክልል ዉጭ ያለዉ አማራ የሚኖረዉ አለ ሀገሩ ነዉ የሚል አቋም አሲዘዉታል::ይሄን የርኩሰት አስተምህሮት አክራሪ የኦሮሞ ፖለቲከኞች የአማራን ህዝብ ለመፍጀት እንደ መነሻ ተጠቅመዉበታል::ሆኖም ከአማራ ክልል ዉጭ ያለዉ የአማራ ምሁር እና ፖለቲከኛ ብሎም ባለሀብት ይሄን ነገር ጠንቅቆ ተረድቶ ለራሱ እንዳይቆም ብአዴን በአማራ ብሄረተኝነት ስም በደንብ አታሎታል::ብአዴን የሚያድነዉ መስሎት ተኝቶ አንጋጦ የሚተብቀዉ 51% አማራ ጉዱን አላወቀም እንጂ እንኳን ብአዴን በአማራ ብሄረተኝነት ስም የተደራጁ ተቃዋሚዎች ሁሉ የካዱት ህዝብ ነዉ::
11.  አንዳንዶች ደግሞ የአንድነት ፖለቲካ ለአማራ ህዝብ የማይበጅ እና እስከዛሬ ተፈትኖ የአማራን ህዝብ ተሸናፊ ያደረገ ነዉ ይላሉ::ሆኖም የትችታቸዉን ትክክለኛ መሰረት አጥርተዉ የመረዳት ብዥታ አለባቸዉ::
የአማራ ነገስታት ለሽህ ዘመናት አሸናፊ የነበሩት በኢትዮጵያ አንድነት ፍልስፍና ተመርተዉ ነዉ::ስለዚህ የአንድነት ፍልስፍና አሸናፊ አያደርግም ማለት ልክ አይደለም::የአማራ ህዝብ እዉነተኛ እና የአሸናፊነት ታሪክም የነገስታቶቹ ታሪክ ነዉ::ይሄን የነገስታቶች የአሸናፊነት እና የአንድነት ታሪክ ሳያዉቁ ስለ አማራ ህዝብ መናገር ነዉር ነዉ::
አንዳንዶችም ላለፉት 30 አመታት የነበሩ ተቃዋሚዎችን እንደ ማጣቀሻ ያቀርባሉ::ሆኖም ተቃዋሚዎች የሚሏቸዉን በየዘርፉ ተንትነዉ አያቀርቡም::
ላለፉት 15 አመታት የኢትዮያን አንድነት ተቃዉሞ በማጭበርበር እና በማስመሰል ሲመሩ የነበሩት በአብዛኛዉ ጸረ አማሮች ናቸዉ::እንዴያዉም አንዳንዶቹ ጸረ አማራ ከመሆናቸዉም በላይ የአማራን ህዝብ ህልዉና የካዱ ከዚያም ዘሎ አማራ አራጅ ከሆነዉ ኦነግ ጋር የወገኑ ነበሩ::ለምሳሌ ግንቦት ሰባት 15 አመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካ መርቷል::ሆኖም ይሄ ሃይል ዋና ስራዉ የነበረዉ አማሮችን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉጭ የማድረግ ስራ ነዉ የሰራዉ::ይሄ ሀይል የአንድነት ፖለቲካ አራምዳለሁ ቢልም ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ተፈጥራለች ብሎ የሚያምን ነዉ::ይሄ ሀይል አማሮችን እንደ ወያኔዎች እና ኦነጎች ወራሪ እና ቅኝ ገዥ ናቸዉ ብሎ የሚያምን ነዉ::ይሄ ሀይል በበታችነት በሽታ በሚሰቃዩ ጸረ አማራዎች የሚመራ ሀይል ነበር::ሆኖም ይሄን ሀይል የኢትዮጵያ አንድነት ያለዉን ሁሉ ተከትሎ የሚሮጠዉ ሀይል ተከትሎት ሮጧል::በዋናነትም አማራ ሀብታሞች እና የአማራ ምሁራን ይሄን ሀይል እንኮኮ ብለዉት ነበር::የሆኖ ሆኖ ግን ይሄን ሀይል የኢትዮጵያ አንድነት ሀይል አለት ታላቅ ስላቅ እና ነዉር ብሎም ድንቁርና ነዉ::
ቅንጅትን በተመለከተ ቅንጅት የኢትዮጵያን ህዝብ በአንድ አንቀሳቅሶ አሸንፏል::ቅንጅት በትክክል የአንድነት ፖለቲካን ጉልበት የሚያሳይ ነዉ::ስለዚህ የተቃዉሞ ፖለቲካዉን በተመለከት ሰፋ አድርገን ማዬት ይኖርብናል እንጂ በጅምላዉ መፈረጅ የለብንም::
——————————
=================================
ድምዳሜ
——
አማራዉን ፈጽሞ ማዳን ካስፈለገ ኢትዮጵያን በተግባርም በስምም እጅ ማስገባት የሚያስችል እንቅስቃሴ መደረግ አለበት::
ስለዚህ በኔ እይታ ኢትዮጵያን እንዴት እጅ ማድረግ ይቻላል የሚለዉ ጥያቄ ነዉ ቁልፍና መሰረታዊ ጭብጡ::ኢትዮጵያን በአስተማማኝ እጅ ማድረግ የግድ ነዉ:: ነዉ::ኢትዮጵያን ከወያኔ:ከኦነግ እና ከጸረ ኢትዮጵያዉያን ሀይላት ሁሉ ማላቀቅ ሲቻል ብቻ እዉነትም አሸናፊ መሆን እንችላለን::
ከላይ የተጠቀሱትን እዉነታዎች ተግባራዊ ለማድረግ ኢትዮጵያ ብሎ ከመነሳት ዉጭ አማራጭ ያለን አይመስለኝም::ኢትዮጵያ ብለን በምንነሳበት ጊዜ ሀገር እንዲኖራቸዉ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዉያኖች(ከአክራሪ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እና ከአክራሪ የትግሬ ፖለቲከኞች ዉጭ ያለዉ) ከኛ ጋር ይሰለፋሉ::የሚኖረንም ጉልበት መላዉ ኢትዮጵያን የሚያድን ይሆናል::
እዚህ ጋ የሚነሳዉ ጥያቄ ኢትዮጵያ ብለን ከተሰባሰብን ኦነጋዊዉ:ህዉሃታዊዉ ገብቶ ያፈርሰናል የሚል ነዉ::ይሄ ፍርሃት ግን ልክ አይደለም::ምክንያቱም አማራ ብለን ብንነሳም ድርጅቱ የሚመለምላቸዉን አባሎቹን አጥርቶ መመልመል ካልቻለ አማራ ነኝ እያለ ከብአዴን ጋር የተሰለፈዉ የአማራ ምሁር/ካድሬ/ፖለቲከኛ ገብቶ ድርጅቱን ያፈራርሰዋል::ይሄንንም በተጨባጭ አይተናል::
ላለፉት ሰላሳ አመታት እንዳዬንዉ የአማራ ህዝብ ዋና የዕልቂቱ አክርኪቴክቶች ከአማራ አብራክ የወጡት በደማቸዉ አማራ የሆኑት ጭምር ናቸዉ::ስለዚህ ዝም ብሎ አማራ አማራ የሚለዉ አደረጃጀትን ስለተከተልንም አማራን ማዳን ይቻላል ማለት አይደለም::ጣሊያናዊዉ ፕሮፌሰር ሰባስኪ እንዳለዉ አማራ ባንዳ ከሆነ ፍጹም ባንዳ ነዉ የሚሆነዉ::ፕሮፌሰር ሰባስኪ የጣሊያንን ጥናታዊ ሰነድ በርብሮ እንዳስቀመጠዉም አማራዉ ጀግና ከሆነ ፍጹም ጀግና እና ማንም እፊቱ የማይቆም ሀያል ነዉ::ስለዚህ የአደረጃጀቱ እዳ ያለዉ ጀግኖችን ፈልፍሎ ከማግኘቱ ላይ ነዉ እንጅ በጅምላ አማራ አማራ እማለቱ ላይ አይደለም::
—–
የዚህ ሁሉ ትንተና ድምዳሜዉም አንድ እና አንድ ብቻ ነዉ::ሀገራችን ኢትዮጵያን ከጠላቶቻችን እጅ ሁሉ ፈልቅቀን ለማዉጣት ኢትዮጵያን የማዳን እንቅስቃሴ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነዉ::በዚህ ሂደት ዉስጥም የአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ሀገር እንዲኖራቸዉ የሚፈልጉ በርካታ ሚሊዮን ኢትዮጵያዉያን ከኛ ጋር ይሰለፋሉ:: ስለሆነም ኢትዮጵያን ማዳን የችግሮቹ ሁሉ ቁልፍ መፍቻ ነዉ::
—–
ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይባርክ !
ኢትዮጵያን ለማዳን ከአክራሪነት የጸዳዉን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ልቡን እግዚአብሄር በአንድ ያናበዉ !
Filed in: Amharic