2.2 ቢሊዮን የሕዝብ ብር የት ገባ?
ባልደራስ
እስክንድር ነጋና ስንታየሁ ቸኮል ማዘጋጃ ቤት እንዳይገቡ ተከለከሉ!
የአዲስ አበባ መስተዳድር በ1957 ዓ.ም. በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ተመርቆ የታነፀውን ታሪካዊውን የማዘጋጃ ቤት ሕንፃ አድሷል። ለእድሳቱ 2.2 ቢሊዮን ብር ወጭ ማድረጉንም ይፋ አድርጓል። በመሆኑም የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች እስክንድር ነጋና ስንታየሁ ቸኮል ሁለት ሕዝባዊ ጥያቄዎችን አንስተዋል፦
፩. ለእድሳት ብቻ ሳይሆን አዲስ ሕንፃ ለመገንባትም ቢሆን እጅግ የተጋነነው 2.2 ቢሊዮን ብር ለምን ምን አገልግሎት እንደዋለ ዝርዝር መረጃ ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን
፪. በእድሳት ሰበብ የታሪካዊው ሕንፃ ቅርሳዊ ገፅታ የጠፋ በመሆኑ መስተዳድሩ ማብራሪያ እንዲሰጥና ወደ ነበረበትም እንዲመልስ
እነኝህን ጥያቄዎች እስክንድር ነጋና ስንታየሁ ቸኮል ትናንት ረቡዕ ጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም. የከንቲባ ፅህፈት ቤቱን በቢሮው ተገኝተው ጠይቀዋል። ሆኖም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የሥራ ሓላፊ የጥያቄዎቹን መልስ አዘጋጅተው እንደሚጠብቋቸው በመንገር ለዛሬ ሐሙስ ጥር 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ከቀኑ በ8:30 በከንቲባ ፅ/ቤት ቢሮ እንዲገኙ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ነበር።
ይሁን እንጂ በቀጠሯቸው መሰረት ዛሬ ቢገኙም በርከት ያሉ የማዘጋጃ ቤት ግቢ ጠባቂ ወታደሮች በር ላይ ከልክለው መልሰዋቸዋል። እነ እስክንድር ከላይ የተገለፀው ቀጠሮ እንዳላቸው ቢያስረዷቸውም “አዎ እናውቃለን። ግን አታስገቡ ተብለናል” ብለዋል ወታደሮቹ።
በዚህ ተስፋ እንደማይቆርጡና ተመላልሰው እንደሚጠይቁ እስክንድርና ስንታየሁ ተናግረዋል።
“ማዘጋጃ ቤቱ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም። 2.2 ቢሊዮን ብር ነው ወጣ የሚባለው። በዚያ ላይ የነበረውን አሻራ አጥፍተው ብልጭልጭ፤ የዱባይ ሞል አስመስለውታል። ይህንን ነው እነርሱ ‘ጥሩ ሠራን’ የሚሉት። ጥሩ አይደለም። ብልጭልጭ ነገርን እንደ ጥሩ መመልከት እውነት ለመናገር ኋላ ቀርነት ነው” ብለዋል የባልደራስ ፕሬዚደንት እስክንድር ነጋ።
እድሳት ሲደረግበት የቅርስን ጉዳይ የሚከታተሉ ተቋማት ፈቃድ፣ ምክርና አስተያየትም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
“በወ/ሮ አዳነች አቤቤ የሚመራው የአዲስ አበባ መስተዳድርና በአብይ አሕመድ የሚመራው የፌዴራል መንግሥት ቅርሳችንን በላጲስ እያጠፉት ነው። ይሄ መታወቅ አለበት። መቆም አለበት” ሲሉም ፕሬዚደንቱ ጨምረዋል።
ሕጉ ግልፅ ድንጋጌ እንዳለው የገለፁት እስክንድር እድሳቱ በቅርስና ግንባታ አዋጆች መሰረት መፈፀም እንዳለበትም ጠቅሰዋል።
“አንድ ሰው ጠቅላይ ሚንስትር ወይም ከንቲባ ስለሆነ እንደ ግል ቤቱ እየመጣ ማፍረስ የለበትም” ሲሉም አክለዋል።
ቅርሱ ሲፈርስ ብሎም ከእያንዳዱ ሰርቶ አደር አዲስ አበቤ ግብር የተሰበሰበ 2.2 ቢሊዮን ብር እንደ ዋዛ ወጣ ሲባል ሕዝብ ዝርዝሩን የማወቅ መብት እንዳለውም አቶ ስንታየሁ ቸኮል ተናግረዋል። ይህ እንዲሆን ያለመሰልቸት ተመላልሰው እንደሚጠይቁም ጠቅሰዋል።
እስክንድርና ስንታየሁ ትናንት ወደ ማዘጋጃ ቤቱ ግቢ ከገቡ በኋላ ስብሰባ ላይ ሆነው ሰዎቹን ከተሸበበው መስታዎት ባሻገር የተመለከቱ ካድሬዎች ሲተረማመሱና በከፊል አዳራሹን እየለቀቁ ሲወጡ ተመልክተናል። የባልደራስ አመራሮች ወጥተው ሲሄዱም ሲገቡ ያልነበሩ ወታደሮች በአራቱም አቅጣጫ ከግቢ ውስጥና ከግቢ ውጭ ማዘጋጃ ቤቱን ከበውት ነበር።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቪዲዮ መረጃዎችን ከሰዓታት በኋላ እናቀርባለን።