>

ሀገሬ ምጸትሽ በዛ፤ መሀሉ ድግስ ዳር ዳሩ ጠኔ፣ ጦርነትና ጅምላ ጭፍጨፋ....!!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ሀገሬ ምጸትሽ በዛ፤ መሀሉ ድግስ ዳር ዳሩ ጠኔ፣ ጦርነትና ጅምላ ጭፍጨፋ….!!!!
ያሬድ ሀይለማርያም

*…. ሸገር በድግስ ከተጠመደች ይኸው ወራቶች ዘለቁ። በሲመተ ብልጽግና የጀመረው ድግስ ዱያስፖራን አምነሽንሾ የአፍሪካ ገዢዎችን ጃኖ አልብሶ ተጠናቋል። የሀገራችን መከራ፣ እርዛት፣ ጠኔና ረሀብ፣ ሰቆቃ፣ ስደትና መፈናቀል፣ የጅምላ ግድያ እና ጦርነቱም እንዲሁ በከፋ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል
አዲስ አበባ የቀሪውን የአገሪቱን አስከፊ ገጽታ ለመጋረድ ጭምብል ሆና የከረመች ትመስላለች። ግርግዳዎቿ በቀለም ተለቅልቀው እና በሚያማምሩ ፎቶዎች ተውበው፣ ህንጻዎቿም በመብራት አሸብርቀው ለእንግዶቿ የአይን ቁስል ከመሆን ተርፋለች።  ዲያስፖራውን እና የአፍሪካ ገዢዎችን ጠብ እርግፍ ብላ በሰላም ሸኝታለች። ድግስ በሽ ነበር።
 – ከጭምብሉ ጀርባ አፋር በጦርነትና በርሃብ ፍዳውን እያየ ነው። ከጦርነቱና ካስከተለው ርሃብ ሽሽት በሺዎች ብዙ ማይልስ በእግር ለመጓዝ ተገደዋል፣
– ከጭምብሉ ጀርባ በጦርነቱ የወደሙ እና ክፉኛ የተጎዱ በርካታ የአማራ እና የአፋር ክልል ከተሞች ገና አመዳቸውን አላራገፉም፣ ከቁስላቸውም አላገገሙም፣
– ከጭምብሉ ጀርባ በርካታ ሕጻናትን ጨምሮ ቁጥራቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከኦነግ ሽኔን ጥቃት በመሸሽ ደብረብርሃን እና ሌሎች ከተሞች ተጠልለው የመንግት ያለሃ ይላሉ። ገሚሶቹም በሽኔ ታጣቂዎች ተከበው ድረሱልን ይላሉ። ዛሬ እንደተገለጸውም ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ በሽኔ ታጣቂዎች መገደላቸውን የመንግስት ሚዲያዎች ጭምር ዘግበዋል፤
መንግስት እነዚህን በሸገር ድምቀት የተጋረዱ የሚመስሉ የሀገሪቱን አንገብጋቢ፣ አሳሳቢና ጊዜ የማይሰጣቸው ችግሮች በአፋጣኝ እና ቅድሚያ ወይም ልዩ ትኩረት (priority) ሰጥቶ በጊዜ ካልፈታ ዳሩ ብቻ ሳይሆን መሀሉም ጤና መክረሙን እንጃ፤ መሀሉም ዳር ይሆናል።
ቅድሚያ አስከፊና አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ላሉ ዜጎች ትኩረት ይሰጥ!!!
Filed in: Amharic