ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ አስቸኳይ መግለጫ በአፋርና በአማራ ላይ የሚደረጉ ጭፍጨፋዎችን እናወግዛለን….!!!
የህዝብን ሕይወት መታደግ ያልቻለ መንግሥት “በቃ” ሊባል ይገባል!!!

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አመራር አባላት ሰሞኑን ከወለጋና ከምዕራብ ሸዋ የተፈናቀሉ ወገኖችን ደብረብርሃን ከተማ በመሄድ ባነጋገሩበት ወቅት፣ ተፈናቃዮቹ በቤተሰባቸው፣ በዘመዶቻቸውና፣ በንብረታቸው ላይ የደረሰውን ዘር ተኮር ጭፍጨፋና ጥቃት እንባቸውን ወደሰማይ እየረጩ አስረድተዋል። በጥቃቱ የኦሮሚያ መስተዳድር ባለሥልጣናት እጅ እንዳለበትም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ አክለውም፣ በአሁኑ ሰዓት ወደ 60ሺ የሚጠጉ የአማራ ተወላጆች በኦነግ/ ሸኔና ተባባሪዎቻቸው ተከበው የሞት ጥላ ተጋርዶባቸው እንደሚገኙ በመግለፅ፣ የኢትዮጵያ ህዝብና የፌደራል መንግሥቱ ከሞት እንዲታደጋቸው የድረሱላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
እንዲሁም፣ በሰሜን ግንባር በኩል ጦረኛው ህወሓት፣ በአፋር ግንባር በኩል ላለፉት ተከታታይ ሳምንታት የማጥቃት ዘመቻ በመክፈት ከወታደራዊ ኢላማዎች ባሻገር በሠላማዊ የአፋር ነዋሪዎች ላይ መጠነ-ሰፊ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡ ይህ ጉዳት፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ አፋሮች ላይ ለረጅም አመታት የኢኮኖሚ ድቀት የሚያደርስባቸው መሆኑን የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች እያስጠነቀቁ ይገኛሉ፡፡ ይህ ሲሆን፣ ህወሓትን የአፋር ክልል ኃይሎች ሲፋለሙ የፌደራሉ መከላከያ ኃይል በሙሉ ኃይሉ እንዲገባ አልተደረገም፡፡ ይህ ሁኔታ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡

ውድ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ፣ በአሁኑ ሰአት ከንፁሃን ወገኖችህ ከአሰቃቂ እልቂት አውጡን ከሚል የወገን ጥሪ በላይ ሊያሳስብህ የሚችል ጉዳይ ሊኖር አይችልም። ወገኖቹ እየታረዱ እንቅልፍ የሚተኛ ህዝብ የህሊና እዳ ተሸካሚ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ከልክ ያለፈ ትዕግስትህ ሊበቃ ይገባል፡፡ “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” እንደሚባለው፣ መንግሥትን የሚመሩት ተረኞቹ ኦህዴዶች እና ተባባሪዎቻቸው የንጹሃን አፋሮችን እና አማሮችን እልቂት ለማስቆም ፍላጎት እንደሌላቸው ተገንዝበህ፣ በመንግሥት ላይ በተለያዩ ህጋዊና ሰላማዊ መንገዶች ተቃውሞህን እንድታሰማ እንጠይቃለን። የዜጎቹን በሀገራቸው በህይወት የመኖር መብታቸውን የማያስጠብቅን መንግሥትና መሪ “በቃ” ሊላቸው ይገባል፡፡
በመጨረሻም፣ መላው የአገራችን ሕዝብም ሆነ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የጉዳት ሰለባ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የእርዳታ እጃችሁን እንድትዘረጉላቸው አጥብቀን እንማፀናለን፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
ቀን፡- የካቲት 02/06/2014 ዓ.ም