>

"የከንቲባ" አዳነች 0% እውነት ሲገለጥ...!!! (ጴጥሮሳውያን) 

“የከንቲባ” አዳነች 0% እውነት ሲገለጥ…!!!

ጴጥሮሳውያን 
      
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የካቲት ፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም. ለአዲስ አበባ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ የሥራ ክንውን ዘገባ (ሪፖርት) አቅርበዋል። ከንቲባዋ በዚህ ፖለቲካዊ ሸፍጥ ባልተለየው ንግግራቸው ቢያንስ ሁለት ሐቆችን ለመደፍጠጥ ሞክረዋል።
☞አንደኛ በኦርቶዶክሳውያን የተነሣባቸውን ተቃውሞ በሚከተሉት ሃይማኖት እና በብሔረሰባዊ ማንነታቸው ምክንያት ያጋጠማቸው ተቃውሞ አስመስለው አቅርበዋል። በዚህ «ድረሱልኝ» በመሰለ የውሸታሙ እረኛ ጩኸታቸው  ስሕተታቸውን በሌላ ሕዝብን ከሕዝብ በሚያጋጭ ከባድ ስሕተት ለመሸፈን ሲጥሩ ተስተውለዋል።
☞ሁለተኛ ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አዲስ አበባ ውስጥ ያልሰጡትን ቦታ የሰጡ አስመስለው አቅርበዋል።
፩ኛ ከንቲባዋ አድሎ በተሞላ የተዛባ አሠራራቸው ምክንያት ኦርቶዶክሳውያን ዜጎች «የኛ ከንቲባ አይደሉም!» በሚል መርሕ ያነሡትን ሰላማዊ ተቃውሞ በብሔራቸው እና በሃይማኖታቸው ምክንያት የተነሣባቸው ተቃውሞ አስመስለው ለማቅረብ ሞክረዋል። በዚህ ርካሽ ፖለቲካዊ ጨዋታ ተከባብረው በሚኖሩ የተለያየ ሃይማኖት ተከታይ ዜጎች መካከል አላስፈላጊ ፉክክርና መገፋፋት ከፍ ሲልም ግጭት ለመጫር የሚደረግ ሙከራ ይመስላል።
   ከንቲባዋ በተደጋጋሚ በአደባባይ የተገለጠ አድሏዊ እና ኢፍትሐዊ አሠራራቸውን በፍትሐዊ አሠራር እንጂ የብሔር እና የሃይማኖት ምሽግ ውስጥ በመደበቅ ለማዳፈን እንደማይቻል ልንነግራቸው እንወዳለን። የሕዝብን አደራ የተሸከሙ፣ ለሕዝብ ጥቅም የቆሙና ስልጡን ፖለቲካን የሚያራምዱ ባለሥልጣናት ስሕተትን በሌላ ትልቅ ስሕተት ለመሸፈን አይሞክሩም። እርሳቸው ግን በዚህ ዐውድ አይገኙም። እውነት ሲገለጥ የውሸት ክምር መናዱ፣ መፈራረሱ እንደማይቀር ዘንግተውታል። ሕዝብን ለጊዜው መዋሸት ቢቻልም ለሥልጣን መንበራቸው ሲሉ ሲያታለሉት የኖሩትን እንዴት እና በምን መንገድ እንደሚቀጣ ለእርሳቸውና ለካቢኔያቸው ታሪክን ጠቅሰን ማስታወስ የተገባ አይደለም። ከዐራት አምስት ዓመታት በፊት አዛዦቻቸው የነበሩ ሰዎች ዛሬ የት እንዳሉ እንዲያስታውሱ መክረን ማለፍ ግን ግዴታችን ነው።
የዚህችው ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ተወካዮች ናቸው በተደጋጋሚ ከከንቲባ አዳነች ጋር ለመነጋገር ደጅ ሲጠኑ የቆዩት። ደጅ ጥናታቸው በማን አለብኝነት ሰሚ አጥቷል። ቤተ ክርስቲያን በቀደመው ከንቲባ አሠራር ሙሉ በሙሉ መብቷ ተከብሮ አይደለም በሽልማት ዕውቅና የሰጠቻቸው። ነገር ግን እያንዳንዷ መልካም ሥራ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ እንዳላት የምታስተምር ቤተ ክርስቲያን ናትና ጅምራቸውን በማድነቅ ለበለጠ ሥራ ከማበረታታት ወደ ኋላ አላለችም። እናም ለበጎ ሥራቸው ዕውቅና ሰጥታለች።
   ዛሬም እርሳቸውን «ከንቲባችን አይደሉም!» የሚል አቋም የያዙት የዚህችው ቤተ ክርስቲያንን ልጆች ናቸው።
ዛሬም በእርሳቸው ግልፅ የወጣ ፕሮቴስታንታዊ ወገንተኝነት ምክንያት በኦርቶዶክሳውያን ላይ የተፈጠረው ስሜት ወደ አልተገባ አቅጣጫ እንዳይሔድ እና ነገሩ በጊዜ ታርሞ መረጋጋት እንዲፈጠር የእንወያይ የወዳጅነት እጃቸውን ዘርግተው ጥሪ ያደረጉላቸው የቀድሞውን ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማን ካባ የሸለሙ አበው ሊቃነ ጳጳሳት እጆች ናቸው።
   በዚህ እውነት ምክንያት ነው ከንቲባዋ አድሏዊ አሠራራቸውን የሚያጸድቅ ሃይማኖታዊና ብሔረሰባዊ ከለላ ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት፣ በተለያየ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል የነገር እሳት ለመጫር መኳተናቸውን ፍሬ አልባ የሚያደርገው።
፪ኛ ከንቲባዋ ባለፉት ሦስት ዓመታት ለፕሮቴስታንት 98ሺሕ ካሬ ቦታ ሲሰጡ  ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ካሬ ሜትር መሬት እንደሰጡ አስመስለው አቅርበዋል።
   እውነቱን በተድበሰበሰና ፖለቲካዊ ሸፍጥ በተሞላበት ዘገባ ሸፋፍነው ነገሩን በቅርብ ለማይከታተል ሰው በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የከፈቱትን የተጠና ጥቃት ለመደበቅ ሞክረዋል። ለኦርቶዶክሳውያን «የፍትሕ ያለህ» ለሚል ድምፅም ሌላ ገጽታ ለመስጠት ተጣጥረዋል። ሁለቱም ሙከራቸው ግን የእውነት መንሽ ሲነካቸው ነፋስ እንዳየ ገለባ መሆናቸው አይቀርም።
    መጀመሪያም ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ይዞታዎቿ እንዲከበሩላት እና የምእመኖቿ ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ስለመጣ ቤተ ክርስቲያን ተክለው፣ የአምልኮ ሥርዐታቸውን የሚፈጽሙበት ቦታ እንዲሰጣት ነው እንጂ የጠየቀችው ቦታ የማግበስበስ ጥያቄ አላቀረበችም፤ ፍላጎቱም የላትም። እርሳቸው ግን አንድ ሚሊዮን ካሬ ሜትር በሦስት ዓመት ብቻ ሰጥቻለሁ አሉ።
    እውነት ተናግረው ቢሆን መልካም ነበር፤ በዚህ የተዛባ መረጃቸው ከንቲባዋ በርካታ ሰሚዎችን እንደሚያደናግሩ ይታወቃል። የተያያዙትን የሸፍጥ ፖለቲካ ያልተረዱ የዋሐንም ስለ ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ሥዕል ያበላሽዋል። በመሆኑም ሐሰቱን ሐሰት ማለት የተገባ ነውና እውነቱን በትንሹ እንገልጣለን።
፪.፩ ከእርሳቸው በፊት እርሳቸው በተቀመጡበት የሓላፊነት ወንበር ላይ
የነበሩት የተከበሩ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በ፳፻፲፩ ዓ.ም. አዲስ የአምልኮ ቦታዎች አሰጣጥ ላይ የመወሰን ሓላፊነት ያለበት የከተማው ካቢኔ ለሁሉም የሃይማኖት ተቋማት የማምለኪያ ቦታ ሲፈቅዱ እኩል ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንም አምስት ቦታዎች ተሰጥቷታል። ከከተማው ሕዝብ ሰማንያ በመቶ ለሚሆነው እናት ለሆነች ቤተ ክርስቲያን ፍትሕን በሚያሰፍን ሁኔታ አይደለም የከተማው መስተዳድር ካቢኔ የቦታ ድልድሉን ያደረገው። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን በወቅቱ ሀገራችን የነበረችበትን ሁኔታ በማጤን በዝምታ አልፋው ነበር።
ይባስ ብሎ ሌሎች የእምነት ተቋማት ቦታቸውን ተረክበው፣ ቦታውን ለአገልግሎት አውለውታል። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ግን በክፍፍሉ ካገኘቻችው አምስት ቦታዎች ውስጥ ሦስቱ እስካሁን እልባት አላገኙም። ቤተ ክርስቲያን ቦታዎቹን ተረክባ፣ ቤተ ክርስቲያን መትከል እና አገልግሎት መስጠት አልቻለችም። ይህም  ከንቲባዋ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን እና ምእመኖቿን በተመለከተ የሚከተሉት የማዳከም ስልታዊ አካሔድ ውጤት ነው።
  ፪.፪. በ፳፻፲፫ ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ካቢኔ ለእምነት ተቋማት ባደረገው አዲስ የአምልኮ ቦታ ክፍፍል እጅግ በሚያሳዝን እና ፀሐይ በሞቀው አድልኦ 80% የከተማዋ ነዋሪ ለሆነው ኦርቶዶክሳዊ ዜጋ አምስት ቦታዎች ብቻ ነው የተፈቀደ። ሒደቱ አልቆ ቤተ ክርስቲያን ተረክባ እየተገለገለችባቸው  ያሉት ግን ሦስቱን ብቻ ነው። በአንፃሩ ለተለያዩ የፕሮቴስታንት ድርጅቶች ከ36 በላይ የተረጋገጡ ቦታዎች ተሰጥቷቸዋል፤ ካርታና የባለቤትነት ማረጋገጫም በፍጥነት አልቆ ስለተበረከተላቸው እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ። (በዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ማብራሪያ ማንበብ ከፈለጉ እነሆ ማስፈንጠሪያው )https://www.facebook.com/100615401510513/posts/454427476129302/ ስለዚህ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከመንግሥት ለቤተ ክርስቲያን የተፈቀዱ ቦታዎች በድምሩ ዐሥር ሲሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥያቄዎችን እንዳይመልስ ተደርጎ በተዘረጋው የከንቲባዋ አግላይ ቢሮክራሲ ምክንያት ሒደቱ አልቆ የተረከበቻቸው ግማሽ ያህሉን ነው።
፪.፫. ሃምሳ ዓመታት በጋብቻ የኖሩ ታዋቂ ባለትዳሮች ሕይወቱን እየኖሩት የጋብቻ ወረቀት ግን እጃቸው ላይ ላይኖር ይችላል። እንበልና በሆነ ምክንያት የጋብቻ ወረቀቱን ፈልገው ወደ ማዘጋጃ ቤት ሔደው በወጣት የድርጅቱ ሠራተኛ አማካይነት ቢፈራረሙ፣ ያ ወጣት የማዘጋጃ ቤት ሠራተኛ የሃምሳ ዓመት ባለትዳሮችን የሞሸርኳቸው፣ ያጋባኋቸው እኔ ነኝ ብሎ ክሥተቱን የራሱ ስኬት አካል አድርጎ ማውራት አይችልም። ያልተወለደበትን ዘመን ታሪክ ለራሱ መውሰድ አይችልምና።
ወይዘሮ አዳነች የዚህን ወጣት አፈራራሚ ዓይነት ገጸ ባሕርይ ይዘው ነው በምክር ቤቱ ውስጥ የተወኑት። ትወናቸው ኅሊና ያላቸውንና ጥቂት ደቂቃ ወስደው የቁጥር ሪፖርታቸውን በተጠየቅ ለመሞገት የሚሞክሩ የምክር ቤቱን አባላት እንኳ አያሳምንም። ምክንያቱም አባላቱ ከ1,000,000 (አንድ ሚሊዮን ) ካሬ በላይ አዲስ የቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ቦታ በሦስት ዓመት ውስጥ በተሰጠባት ከተማ ከሆነ የሚኖሩት እዚህም እዚያም የከተማዋ ክፍት ቦታ ሁሉ በአዳዲስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ ተሞልቶ ማየት ነበረባቸውና። ይህን ማየት ግን አይችሉም። ከንቲባዋ መሬት ላይ የሌለ የተዛባ መረጃ እየሰጡ ነውና። በተጨማሪም አዲስ ቦታ ሲሰጥ ውሳኔ የሚተላለፈው በከተማው ካቢኔ አማካኝነት በመሆኑ መቼ ነው አዲስ አንድ ሚሊዮን ቦታ ስጦታ ጉዳይ ለካቢኔ ቀርቦ ውሳኔ ያገኘው? ሰጠሁት ያሉት ቦታ አዲስ ቦታ ስላልሆነ ለካቢኔም አልቀረበም፤ እርሳቸውም ስጦታውን ለቤተ ክርስቲያን በመስጠት ተፈጻሚ እንዲሆን አላደረጉም።
     በሦስት ዓመት ውስጥ በሕግ ተፈቅዶልን የሠራናቸው ጥቂት አብያተ ክርስቲያናት እንኳ በግብረ ኃይል እየፈረሱ፣ ነዋየ ቅድሳት እንደ አልባሌ ዕቃ የትም ለተወረወሩብን ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያኑ ደግሞ ከንቲባዋ በአደባባይ ቅጥፈታቸው በቁስላችን ላይ እንጨት ሰድደውበታል። በካቢኔ ውሳኔ የተሰጠን ቦታ ላይ ለማገልገል የተገኙ ካህናት በድንጋይ ተወግረው፣ በዱላ ተደብድበው ለተባረሩብን ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያን የእርሳቸው አመራር ዘመን የዜግነት መብታችን መሬት ተጥሎ የተረጋገጠበት ዘመን ነውና «ከንቲባችን» ብለን ለመቀበል ተቸግረናል።
     ለአንዳንድ ከአዲስ አበባ ከተማ መቆርቆር በፊት ለተተከሉ እና ከከተማዋ መቆርቆር ጋር ተያይዘው ለተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት የባለቤትነት ካርታ ማረጋገጫ በቀድሞው የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ስለተሰጠ ብቻ በዘገባቸው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቱ ለዘመናት ይዘውት የቆዩትን ቦታ በእርሳቸው ልግሥና ያገኙት አስመስለው አቅርበዋል። ለምሳሌ መስቀል አደባባይ ለሚገኘው ለደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ፣ ለቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ፣ ለገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሒደቱ ላላቀው ሰአሊተ ምሕረት እና ሌሎች መሰል ነባር አብያተ ክርስቲያናት ናቸው የባለፉት ሦስት ዓመታት ስጦታዎች ተደርገው የቀረቡት።
  በእርሳቸው የከንቲባነት ዘመን ቤተ ክርስቲያን የተቀበለችው አዲስ ቦታ 29 ሺሕ ካሬ ብቻ ነው። በአንፃሩ በተናጥል አላስተናገድኳቸውም ያሉት የወንጌል አማኞች ኅብረት አባል የእምነት ድርጅቶች በእርሳቸው የሓላፊነት ዘመን በተናጥል የተሰጣቸው ቦታ በድምር ሲሰላ 98 ሺሕ ካሬ ነው። ከንቲባዋ ይህን ዕርቃኑን የቀረ ኢፍትሐዊ አሠራራቸውን ለመሸፈን ነው ወደ ኋላ ሔደው በቀድሞው ምክትል ከንቲባ ዘመን ለነባር ይዞታቸው ካርታ የተሠራላቸውን የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታዎችንና የነባር አብያተ ክርስቲያናትን ይዞታ ካርታዎችን የእርሳቸው ፍትሐዊ አሠራር ውጤት ማሳያ አድርገው በአዲስ አበባ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ያቀረቡት።
ማጠቃለያ
☞ ከንቲባዋ ፖለቲካዊ ሸፍጥን ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያንን ለትችት አጋልጠው ለመስጠት ሞክረዋል። አልተሳካም እንጂ እርሳቸውና በተለያዩ ቢሮዎች ላይ የሾሟቸው ሓላፊዎች በኦርቶዶክሳውያን ላይ ያደረሱትን እና እያደረሱት ያሉትን በደል ለማዳፈን ሞክረዋል።
☞ አድልኦና ኢፍትሐዊነት በተሞላ አሠራራቸው ምክንያት የተነሣባቸውን ተቃውሞ በብሔረሰባዊ እና ሃይማኖታዊ ማንነታቸው ምክንያት የተነሣባቸው ተቃውሞ አስመስለው በማቅረብ ተከባብሮ በሚኖረው ሕዝብ መካከል የነገር እሳት ለመጫር ሞክረዋል። ምክንያቱም በምክር ቤቱ የተናገሩት ከተራ ሪፖርት የማሳመር ፍላጎት ያለፈና የተዛባ መረጃ ለሕዝቡ በመስጠት የኦርቶዶክሳውያንን መብት የማስከበር ትግል የማኮላሸት ቅዠት ውጤት ነው። ከእርሳቸው ጋር የጋራ ሃይማኖታዊ እና ብሔረሰባዊ ማንነት ላላቸው ለቀድሞው ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማን ቤተ ክርስቲያን ዕውቅና መስጠቷ በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ፊት ሰዎች በሥራቸው እንጂ በማንነታቸው እንደማይመዘኑ ግልጽ አድርጎ ያሳያል።
☞ ለፕሮቴስታንት ድርጅቶች  አዲስ 98 ሺሕ ካሬ መስጠታቸውን ለመደበቅ ካላቸው ፍላጎት የተነሣ በቀድሞው የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ የተሠጡትን የጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት ያልተሟላ ካርታ  ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አዲስ አንድ ሚሊዮን ካሬ መሬት የሰጡ አስመስለው አቅርበዋል።
ይህ ሁሉ ፖለቲካዊ ሸፍጣቸው ለሚመሩት መስተዳድር እንዳሰቡት ቅቡልነትን ሰጥቶ የኦርቶዶክሳውያንን የፍትሕና ያለ አድልኦ የመስተናገድ ጥያቄን የማኮላሸት ዓቅም የለውም። ያልተቀበልናቸው በማንነታቸው ሳይሆን እየተጓዙበት ባለው አድሏዊ አካሔድ ምክንያት ነውና ላያዋጣቸው ስሕተታቸውን በብሔርና በሃይማኖት ምሽግ ተደብቀው ለማምለጥ የሚያደርጉትን ሙከራ ትተው፣ ጥፋትዎን አምነው አድሏዊነትን በእኩልነት፣ ኢፍትሐዊ አሠራራቸውን በፍትሐዊነት ያርሙ።  ይህን ሲያደርጉ ብቻ ነገሮች ይስተካከላሉ።
Filed in: Amharic