>
11:10 am - Tuesday March 21, 2023

ምስጋና ለአገር ጠባቂው ፋኖ!!! (ቀለብ ስዩም)

ምስጋና ለአገር ጠባቂው ፋኖ!!!

ቀለብ ስዩም

በግፍ ከተጋዝንበት የቃሊቲው ወህኒ ከወጣን ሳምንት እንኳ በቅጡ ሳይሞላን፣ የ“ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ” ፕሬዚዳንት አቶ እስክንድር ነጋ ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት፣ አንድ የልዑካን ቡድን ሕወሓት ጥቃት ባደረሰባቸው አፋር እና ዐማራ ክልሎች ከጥር 6 እስከ 19/2014 ዓ.ም ተዘዋውሮ፣ በጦርነቱ ክፉኛ የተጎዳውን ሕዝብ አፅናንቷል፡፡ የአገሪቱን ህላዊነት ለማስቀጠል ከፍተኛ ተጋድሎ ላደረጉት ደግሞ፣ ልባዊ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
እኔም፣ የዚህ የታሪካዊው ቡድን አባል ሆኜ በመጓዜ፣ በአንድ በኩል የወገኖቼን፡- መስዋዕትነት፣ መከራ፣ የሃብት-ንብረት ውድመት፣ የአካልና ሥነ-ልቦናዊ ድቀት፤ በሌላ በኩል፣ ከአባቶቻቸው የወረሱትን ጀግንነት የመመልከት እድሉን አግኝቻለሁ፡፡ መቼም፣ የዐማራ እና አፋር ሕዝብ አይበገሬነት፣ የሞራልና የሥነ-ልቦና ጥንካሬ ‹አጃኢብ› ያሰኛል፡፡ ‹የሰው ልጅን መከራ ያጠነክረዋል› ሲባል የሰማሁትንም በተግባር ያረጋገጥኩበት ነበር፡፡
ይህም ሆኖ፣ ሁለት ጉዳዮችን በቅድሚያ መግለጽ ያለብኝ ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያው፣ በእዚህ ጽሑፍ ከማስታወሻ ደብተሬ ያስነበብኩት፣ የግል እይታዬና ድምዳሜዎቼ ብቻ ከመሆናቸው በተጨማሪ፤ በጉብኝቱ ወቅት ካየሁት ጥቂት ክስተቶችን ቀንጭቤ አቀረብኩ እንጂ፤ የተፈጸመውን ጥቃትና  ውድመት በልኩ የሚገልጽ አለመሆኑን ነው፡፡ ሁለተኛው፣ በዚህ እትም የማቀርበው ከአዲስ አበባ ተነስተን ዐባይን ተሻግረን፡- ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ አዳርቃይ ጨው በር፣ ወልደያ፣ ደሴ እና ሸዋሮቢትን ያዳረስንበትን ብቻ ሲሆን፤ የአፋር ምልከታዬን በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡
አሁን ማስታወሻዬ እንለፍ፡፡
የጉዞ ዘገባዬን፣ እብሪተኛው የሕወሓት ወራሪ ኃይል በዐማራና አፋር ሕዝብ ላይ የፈጸመው ግፍ ተነግሮ የማያልቅ በመሆኑ፤ ጥቃቱን ለመመከት የተዋደቁ የዐማራ ሕዝባዊ ኃይሎችንና ፋኖዎችን በማመስገን እጀምራለሁ፡፡ በርግጥ፣ እንዳለመታደል ሆኖ እንጂ፣ ወያኔ “እወክለዋለሁ” በሚለው ማኀበረሰብ ላይ የሚፈጽመውን አረመኔያዊ ደርጊትንም በአካል ተገኝተን ብንጎበኝና ሕዝቡን ብናፅናና እወድ ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው! የሽብር ቡድኑ ወደ ትግራይ መግባትን የማይቻል አደረገው እንጂ፡፡
  1)  ባህር ዳር የውበት ምድር
                ******************
የመጀመሪያችን መዳረሻ በሆነችው ውቢቷ ባህር ዳርና አካባቢው፣ ከዐማራ ፋኖዎች በቅድሚያ ያገኘነው ታላቅ ተጋድሎ በፈጸሙት ዘመነ ካሤ እና ካፒቴን ማስረሻ ሰጠኝ የሚመራውን ሲሆን፤ አባላቶቻቸው ዐባይ ማዶ ድረስ መተው ደማቅ አቀባበል አድርገውልናል፡፡ የከተማዋ የወጣቶች ማኀበርም ከፍተኛ አቀባበል እንዳደረገልን ሳልገልጽ አላልፍም፡፡ የተለያዩ ስጦታዎችንም አበርክተውልናል፡፡ ካማረው የምሳ ፕሮግራም በተጨማሪ፤ በጀግንነት የተሰው ፋኖዎችን ፎቶ-ግራፍ ለማስታወሻ ሰጥተውልናል፡፡ እኛም፣ የተሰዉትን ጀግኖች ፋኖ ሞላ ደስየ እና ፋኖ ማንደፍሮ አድማስ ቤተሰቦችን ጎብኝተን፣ ከጎናቸው እንደሆንን በመግለጽ አበረታተናቸዋል፡፡ የጀግኖች ታሪክ እንዲዘከርም የበኩላችንን አስተዋጽኦ አድርገናል፡፡ ቤተሰቦቻቸው እርዳታ እንዲያገኙም አድራሻቸውን አብረውን ለነበሩ ሚዲያዎች ሰጥተናል፡፡ በፈለገ ሕይወት ሆስፒታልም ተገኝተን የጦር ቁስለኞችን ጎብኝተን፣ በቶሎ እንዲያገግሙ መልካም ምኞታችንን ገልጸንላቸዋል፡፡
በነገራችን ላይ፣ በያዝነው ዐመት ከእስር ቤት ሁኜ ባዘጋጀሁት “የመሪዎች ሴራ በኢትዮጵያ፣ የተከዳው አማራና አዲስ አበቤ” በሚለው መጽሐፌ በገጽ 66 ላይ የፋኖ አስቻለው ደሴን ገድል፣ በሕወሓት-ብአዴን ኢሕአዴግ አፋኝ ኃይሎች የደረሰበትን መከራና ስቃይ ለንባብ ማብቃቴን አስታውሳለሁ፡፡ በእዚህ ታሪካዊ የጉዞ ወቅትም፣ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅና የዐማራ አለኝታ የነበረው የአስቻለው ደሴ ምስል፣ ከፋኖው ማኀበረሰብ በእነ ዘመነ ካሴ አማካኝነት በስጦታ ሲበረከትልኝ የተሰማኝ የደስታ ስሜት እጥፍ ድርብ እንደነበረ፣ መመስከር ያለብኝ ይመስለኛል፡፡ በእዚህ ደግ፣ ኩሩና አይበገሬ ሕዝብ መሃል ተወልጄ በማደጌም ፈጣሪዬን በልቦናዬ አመስገንኩት፡፡ በታሪክ አጋጣሚም፣ የወደቀበትን የግፍ ውርጅብኝ በፈርጣማ ክንዱ ባስወገደ ማግስት፣ ከእስር ተፈትቼ በመሃሉ መገኘት መቻሌ በራሱ መታደል እንደሆነ ተሰምቶኛል፡፡
2) “ጎንደር ጎንደር – የቴዎድሮስ አገር!”
       ***************************
ጥር 9/2014 ዓ.ም ከባህር ዳር ማልደን በመነሳት፣ የሥልጣኔ መናገሻ ወደ ሆነችው ጥንታዊቷ የዐፄዎቹ ከተማ ጎንደር አቀናን፡፡ አዘዞ ከተማ ስንደርስ በፋኖ ሰለሞን አጠና የሚመራው ሠራዊት፣ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ምሁራን፣ የጎንደር ወጣቶች፣ የጠዳ ፋኖዎች፣ በሻለቃ ዋሴ ተኮላና በሻለቃ መዝናቸው ዘውዱ የሚመራ የፋኖ ጦር፤ እንዲሁም ቤተሰቦቼ ፋኖ ዘለቀ አሰማራው እና ባድማው ስዩም የአበባ ጉንጉን ማጥለቅን የጨመረ የጀግና አቀባባል አድረጉልን፡፡ እኛም ከልባችን ካመሰገናቸው በኋላ፤ በሱዳን፡- በሽንፋ እና መተማ፤ በትግራይ፡- በአደርቃይ፣ ዳባት ጭና፤ እንዲሁም በወልቃይት… ወያኔ የሰነዘረውን ትንኮሳ ድባቅ የመቱበትን ጀግንነት በማስታወስ፣ ከወገባችን ዝቅ ብለን ልባዊ ምስጋናችን አቀረብንላቸው፡፡
ከዚህ በኋላም፣ በቀጥታ ጎንደር ዳባት ወረዳ “አጅሬ” በምትባለው ስፍራ ወደሚገኘው የሻለቃ መሳፍንት ተስፉ የፋኖ ጦር አመራን፡፡ ይዘነው ከተነሳነው ዓላማ አኳያ፣ የመንገዱ እጅግ ጠመዝማዛና አስቸጋሪነት ሳይበግረን፤ ከ30 ዐመት በላይ ወያኔን ሲያርበደበደ የኖሩትን፣ አሁንም ተረኛውን ኦሕዴድ ‹እምቢኝ› ያሉትን ጀግናውን ሻለቃ መሳፍንት ከእነ ሙሉ ጦራቸው አግኝተን፣ አገር ለማስቀጠል ላደረጉት ተጋድሎ ከጉልበታችን በርከክ ብለን አመሰገንን፡፡ እነሱም፣ እኛ በግፍ ከታሰርንበት ተፈተንና አስቸጋሪውን ጠመዝማዛ መንገድ አቋርጠን በመምጣታችን፣ በቅድሚያ “እንኳንም ከእስር ተፈታችሁ!” ብለው መልካም ምኞታቸውን ገለጹልን፡፡ ቀጥለውም፣ የትግላቸውን ፍሬ ማየታቸውን ጠቅሰው፤ በመገናኘታችን ልባዊ ደስታ እንደተስማቸው ነገሩን፡፡
በተመሳሳይ አደርቃይ ግንባር “ጨው በር” ወደሚባለው ቦታ አምርተን፣ በሻለቃ ሰፈር መለሰ የሚመራውን የፋኖ አባላት አግኝተናል፡፡ ሻለቃ ሰፈር፣ እንደ ሻለቃ መሳፍንት እድሜ ዘመናቸውን በትግልና በአርበኝነት የሚታወቁ ሲሆን፤ ረጅም ጊዜም ለአገር እና ለሕዝብ ከፍተኛ ተጋድሎ ፈጽመዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ፡- በ1991 ዓ.ም ለስለላ የመጣች የወያኔ ሄሌኮፍተርን መትተው መጣላቸውንና ፓይለቱን ጨምሮ 4 የጦር ባለሙያዎችን መማረካቸውን ነግረውናል፡፡ ወያኔም በቤተሰባቸው ላይ በፈጸመው የበቀል እርምጃ፡- ወንድማቸውን ገድሎ አስክሬኑን ከሊማሊሞ ገደል ወርውሮ ወደ ድብ ባህር ጥሎት ሄዷል፡፡ እሳቸውንም ከ7 ጊዜ በላይ አቁስሏቸዋል፡፡ እኛም፣ አገር ለማስቀጠል ለፈጸሙት ጀግንነት በኢትዮጵያዊ ትህትና ከወገባችን ጎንበስ ብለን አመስግነን ስናበቃ፤ የደብረ ታቦር-ጋይንትና ወልድያ መንገድን ያዝን፡፡
3)  የደብረ ታቦር-ጋይንት ፋኖ ተጋድሎ
       ***************************
ደብረ ታቦር ስንደርስ፡- በፀዳሉ እና ዳንኤል የሚመሩትን ፋኖዎችን ጨምሮ፤ የወጣቶች ማኀበር እና የከተማው ሕዝብ በዐፄ ቴዎድሮስ ዐደባባይ በመገኘት ከፍተኛ አቀባበል አድርገውልናል፡፡ እኛም፣ ሕዝባዊ ኃይሉ፣ ፋኖዎችና በአጠቃላይ የአካባቢው ሕዝብ አገር ለማስቀጠል ላደረጉት ተጋድሎ በተለመደው መልክ ልባዊ ምስጋናችንን አቅረብን፡፡ መቼም፣ እነዚህ የዐፄ ቴዎድሮስ ልጆች ወደ አካባቢያቸው ተጠግቶ የነበረውን የወያኔ መንጋ ድባቅ ሲመቱት ጊዜ እንዳልፈጀባቸው በኩራት ሲነግሩን፣ ደስታችን ወደር አልነበረውም፡፡ ለዚህ ጀግንነታቸው የሚገባቸውን ያህል ማመስገን ባንችልም፤ በጦርነቱ የተሰው ቤተሰቦችን አጽናንተናል፡፡ በመጨረሻም፣ “እንኳን ከጨለማው እስር ቤት ወጥታችሁ ተገናኘን” ብለው ደስታቸውን ከገለጹልን በኋላ፣ የዘመናይቷን ኢትዮጵያ ጠንሳሻ ንጉሥ ዐፄ ቴዎድሮስን ምስል ሸልመውናል፡፡
ከዚህ ቀጥሎ፣ ጋይንት ንፋስ መውጫ ወደሚገኘው የሻለቃ ከፍያለው ደሴ የፋኖ ጦር አምርተን፣ አገር አደጋ ውስጥ በገባችበት ጊዜ ለከፍሉት መስዋዕትነት ከፍተኛ ምስጋና አቅረብን፡፡ እዚህ ጋ፣ በጉብኝቱ ወቅት ከደቡብ ጎንደር ዞን ጋይንት ንፋስ መውጫ ከፋኖ ጦር የተመለከትኳቸውን ሁለት ለየት ያሉ ነገሮችን ጠቅሼ አልፋለሁ፡፡ የመጀመሪያው፣ ሦስት ወንድማማቾች፡- ሻምበል መላኩ ዋለልኝ፣ ተመስገን ዋለልኝ እና ሻለቃ ሰሎሞን ዋለልኝ በተናበበ ጀግንነት ትሕነግን ፊት-ለፊት በመተናነቅ የማረኩትን የቡድን መሳሪያ ታጥቀው ለአገራቸው ለወገናቸው ሲፋለሙ ማየቴ፣ ለፋኖ ያለኝን ክብር በእጅጉ ከፍ አድርጎታል፡፡ የራሳቸውም ሆነ የቤተሰቦቻቸው ህይወት ሳያሳሳቸው መታገላቸውም፣ የፋኖን ሕዝባዊነትም አስረግጦልኛል፡፡
ሁለተኛው፣ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሰባት ቤተሰቦቻቸውን በአንድ ጊዜ የተነጠቁት አቶ ድረስ ነጋን አግኝተን ማጽናናታችን ነው፡፡ አደጋው በደረሰበት ወቅት አምስት የቤተሰባቸው አባላትን ጨምሮ፤ አንድ ተከራይቶ የሚኖር መምህር እና አንድ የልጆቻቸው ጓደኛ በግቢው ውስጥ ነበሩ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ፣ ከሕወሓት ወንበዴ ወደ ግቢያቸው የተተኮሱ የመድፍ ቅንቡላዎች ሰባቱንም በጭካኔ ቀጠፏቸው፡፡ ቤት-ንብረታቸውንም ሙሉ-በሙሉ አወደሙት፡፡
በአሁኑ ወቅት አቶ ድረስ፣ ቤተሰቦቻቸውንም ሆነ ንብረታቸውን አጥተው፣ በከባድ ሀዘንና ትካዜ ቆዝመው መመልከት ልብ ይሰብራል፤ ህሊናን ያሳምማል፡፡  እንደ አቶ ድረስ ነጋም የህይወትና የንብረት ውድመት ዋጋ የከፈሉ እጅግ በጣም ብዙ ሰለባዎች በከተማዋ እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ በጥቅሉ፣ የሕወሓት ወንበዴዎች ደብረ ታቦር እና ጋይንትን አውድመውታል፤ የቻሉትንም ያህል ዘርፈዋል፡፡
4)  የጋሸና ምሽግ እና ጨጨሆ መድሃኒዓለም
       ***************************
የሽብር ቡድኑ፣ በየትኛውም ጦርነት የሃይማኖት ቦታዎች ላይ ጥቃት እንዳይሰነዘር የሚከለከለውን ዓለም ዐቀፍ ስምምነት ጥሶ፣ የጨጨሆ መድሃኒዓለምን ቤተ-ክርስቲያን ግንባታ በመድፍ አፍርሷል፡፡ በዚህም፣ እስካሁኑ ምንም ዐይነት ሃይማኖታዊ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን ተመልክተናል፡፡ መቼም፣ ወያኔ፣ ከአገር እና ሕዝብ ጠላትነቱ ባሻገር፤ እምነት-የለሽ ለመሆኑ ከዚህ በላይ አስረጂ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡
በጋሸና ግንባርም፣ የቆፈረውን ከስድስት ኪ.ሜ በላይ የሚረዝም ምሽግ ተመልክተናል፡፡ ምሽጉ ውስጥ የሰዎች ሬሳ ይታያል፡፡ ሁኔታው በጣም ይሰቀጥጣል፡፡ በዚሁ አካባቢ የሚገኝ የመንግሥት ጤና ጣቢያ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ወድሟል፡፡ በርካታ እናቶችም ልጆቻቸውን ይዘው አገልግሎት ለማግኘት ተሰልፈው አይተናል፡፡ የጤና ጣቢያው ኃላፊ አቶ መሐመድንም ስናነጋግራቸው፣ ባለሙያዎቹ ህብረተሰቡን ለማገዝ ቢፈልጉም፣ ተቋሙ ከደረሰበት ከባድ ጉዳት አኳያ፣ ምንም ዐይነት አቅርቦት ባለመኖሩ መቸገራቸውን ገልጸውልናል፡፡ ይህም ሆኖ፣ የሚችሉትን ያህል እያገለገሉ እንደሆነ ግን ጠቅሰውልናል፡፡
መንግሥታዊው “ገረገራ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት”ም ሙሉ በሙሉ መውደሙን ተመልክተን አዝነናል፡፡ በደብረ ዘቢጥ አካባቢም፣ በጣም ብዙ ታይቶ የማየታወቅ መከራ በህብረተሰቡ ላይ እንደደረሰ ታዝበናል፡፡ የተደፈሩ ህፃንናትንና እናቶችን ሰቆቃ መስማት፣ መፈጠርን እስከመጥላት የደረሰ ስሜት ይፈጥራል፡፡ እጅግ ብዙ የንብረት ውድመቶች ተከስተዋል፡፡ በርካታ ቤቶች ፈርሰዋል፤ ተቃጥለዋል፡፡ ከሰለባዎቹ ውስጥ የመምህር ብሩክ ታመነን ጉዳት ጎብኝተን ነበር፡፡ “ቤቱን ከገነባሁት ዐሥራ አምስት ዐመት ሆኖታል፡፡ ልጆችም አሉኝ፤ መምህር ነኝ፡፡ ይሁን እንጂ፣ ከባለቤቴ ጋር ሆነን በብዙ ድካም የገነባነውን ቤታችን ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡ መልሶ ለመገንባት ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅብኝ አላውቅም፡፡ በዚህ ላይ፣ ኑሮ እጅግ ከባድ ሆኗል፤” ሲሉ ሀዘናቸውን በሰተበረ ድምጽ ነግረውናል፡፡
ደብረ ዘቢጥ ላይ የመምህሩን ጉዳት እንደ አብነት አነሳነው እንጂ፤ ወንበዴው መላ ከተማዋን የከባድ መሳሪያና የመድፍ መለማመጃ አድርጓት እንደቆየ ከተማዋን የረገጠ ሁሉ በቀላሉ የሚረዳው ነው፡፡ በዚህ በጋሸና ጤና ጣቢያም አካባቢ በተፈጸመው ግፍና በደል ቤት ንብረታቸው የወደመባቸው በርካታ ነዋሪዎች ለእርዳታ ተሰልፈው ተመልክተናል፡፡
   5)  በፍቅር ምድር የወሎ ሕዝብ ሰቆቃ
         ***************************
በወልዲያ በሻለቃ ምሬ ወዳጁ የሚመራው የፋኖ ሠራዊት “የጀኔራል አሳምነው ፅጌ ጦር” በሚል ሥያሜ እንደሚጠራ ሰምተናል፡፡ እኛንም፣ ከፍተኛ ዝግጅት አድርገው በወታደራዊ ሥነ-ሥርዐት ነበር የተቀበሉን፡፡ እነዚህን የቁርጥ ቀን ደራሾችም፣ ከጉልበታችን ጎንበስ ብለን አመስግነናል፡፡ ወያኔ፣ ወልዲያን በተደጋጋሚ ጊዜ ብትወርም፤ በፋኖዎችና በወጣቶች ተጋድሎ አይቀጡ ቅጣት እየተቀጣች መመለሷ ይታወቃል፡፡ በእዚህም፣ ከተማዋ “ደም መላሿ ወልዲያ” የሚል ቅጽል ስም አግኝታለች፡፡
በዚሁ መድረክ፣ የፋኖው መሪ ሻለቃ ምሬ ወዳጁ፡- “ወራሪው ወያኔ ከዐማራ ምድር ጨርሶ ሳይወጣና የተዘረፍነው ንብረቶችም ሆኑ ታፍነው የተወሰዱ ወገኖቻችን ሳይመለሱ፣ ውጊያው እንዲቆም መደረጉ አግባብነት የለውም፡፡ እንዲሁም ፋኖ በአንድነት መቆም አለበት፡፡ ‘ይህ ፋኖ እስላም ነው’፣ ‘ይህ ፋኖ ክርስቲያን ነው’ እያላችሁ ለመከፋፈል ያሰባችሁ ሆድ ዐደሮች ከዚህ ተግባራችሁ ብትቆጠቡ መልካም ነው…፤” የሚል ጠንከር ያለ መልዕክት ለከፋፋዮች አስተላልፈዋል፡፡
ከዚህ በኋላ፣ ወደ ደሴ ለመሄድ እየተጓዝን ሃይቅ ከተማ ስንገባ፣ የደሴው የዐማራ ሕዝባዊ ኃይል የልዑካን ቡድን ሃይቅ ድረስ መጥቶ ተቀብሎን፣ ደሴ መሃል ከተማ ድረስ አጅቦ ወሰደን፡፡ በርግጥ፣ ሃይቅን ከመርገጣችን በፊት መርሳ ከተማ ላይ አንድ ትልቅ መስጊድ፣ ልክ እንደ ጨጨሆው በወያኔ መድፍ መመታቱን ተመልክተናል፡፡ የመስጊዱን ኃላፊና አገልጋይ ሸኽንም አግኝተናቸው እጅግ ባዘነ አንደበት፣ ሃይማኖታዊ እሴቶችን እንዳዋረዱና ቅዱስ ቁራንን ሳይታጠቡ እንዳቆሸሹ፣ እስከ ጫማቸው መስጊዱ ውስጥ ድረስ እንደገቡ፣ ‹የተደበቀ መሳሪያ አለ፤ አምጡ?!› እያሉ እንዳስጨነቋቸው ነግረውናል፡፡ በመጨረሻም ሸኹ “ይህ ቡድን ካልጠፋ ሰላም የለም፤” ሲሉ አስተያየተቸውን ቢቋጩም፤ እርዳታ እንደሚያስፈልግ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በፍቅር አገር ወሎ፣ ደሴ በፋኖ ሰለሞን አሊ እና በፋኖ ኤርሚያስ አያሌው የሚመራው ሠራዊት አቀባበል አድርገውልናል፡፡ በባህር ዳር ከተማ በነበረን ውይይት እነ ዘመነ ካሴን እና ካፕቴን ማስረሻ ሰጤን “የሴት ፋኖ የሉም እንዴ?” ብዬ ስጠይቃቸው፣ መኖራቸውን ጠቅሰው ‹በአሁኑ ወቅት ግን ጦር ግንባር ላይ ስለሆኑ በዚሁ ቦታ አልተገኙም› የሚል መልስ ሰጥተውኝ ነበር፡፡ በደሴ አቀባበል ላይ፣ ሴት ፋኖዎችን በማግኘቴ ከፍተኛና ለየት ያለ የደስታ ስሜት ተሰማኝ፡፡
የአባቶቻቸውን የአርበኝነት ውርስ ተቀብለው ኢትዮጵያ በግፈኞች ስትወጋ ለተዋደቁት ለእነዚህ ፋኖዎችም፣ የሚገባቸውን ክብር ከቃል በላይ በተግባር ለመግለጽ አንዳች ስሜት አነሳሳኝ፡፡ የሉዑካኑን አቶ እስክንድር ነጋን በመድረኩ ፊት ለፊት እነዚህን ጀግኖች የማደንቅበት ቃል ስላጣሁ ተንበርክኬ እንዳመሰግናቸው ፍቃዳቸውን ጠየኳቸው፡፡ እሳቸውም፣ “አንቺ ብቻ ሳትሆኚ፣ እኛም ከአንቺ ጋር ተንበርክከን እናመሰግናለን፤” በማለት ልባዊ ምስጋናችንን ተንበርክከን አቅርበናል፡፡
በዚሁ መድረክ አቶ እስክንድር ነጋ፡- “ወደፊት ለሚደረገው ተጋድሎ፡- ድል ለመከላከያ ሠራዊት! ድል ለፋኖ! ድል ለሚሊሻው! ድል ለዐማራ ልዩ ኃይሉና በአጠቃላይ በጦርነቱ ቀጠና ሆነው በመዋጋት ላይ ለሚገኙ የአፋር የፀጥታ ኃይሎች!” የሚል መፈክር አሰምተዋል፡፡ አያይዘውም፣ ለአራት ኪሎው መሪ እና ለወያኔ ኢትዮጵያን ማፍረስ እንዳማይቻል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በነገራችን ላይ፣ አቶ እስክንድር በደረስንበት ቦታ ሁሉ፣ ወደዚህ የመጣነው ለፖለቲካ ሳይሆን፤ አገርን በማስቀጠል ጉዳይ ቅድሚያ ስለምንሰጥ ልናመሰግናቸው እንደሆነ እና በጀግንነት የተሰዉ የፋኖ ቤተሰቦችን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲደግፋቸው፣ ልጆቻቸውን እንዲያስተምርላቸው አጥብቀው ትኩረት በመስጠት ይናገሩ ነበር፡፡ የፋኖ የስልጠና መምሪያ ኃላፊውም ለልዑካን ቡድኑ ንግግር አድርገው ሲያበቁ፤ የጥንት የጠዋቷን በመሰዋዕትነት የከበረችውን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዴራ ሸልመውናል፡፡
 መሪው ፋኖ ሰለሞን አሊም ተንበርክከው ምስጋናቸውን ለተሰው ጓዶቻቸው አቅርበዋል፡፡
የኮምቦልቻ የፋኖ አባላት እና ወጣቱም በጋለ ስሜት አቀባበል አድርገውልናል፡፡ እኛም፣ በፋኖ ያሬድ የሚመራው ጦር አገር ለማስቀጠል ላደረገው ተጋድሎ ከወገባችን ጎንበስ ብለን ከፍተኛ ምስጋና አቅርበናል፡፡ እነዚህ የኮምቦልቻ ፋኖዎች በስልጠናቸው ወቅት በህብረ-ድምጽ የሚዘምሩት መዝሙር ታላቅ ወኔን የሚቀሰቅስና የአገር አንድነትን የሚያስረግጥ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡-
“ህይወቴን ለዐማራ፣ ስጋዬን ለአሞራ፤
ፋኖ መነሻው ዐማራ፣ መዳረሻው ኢትዮጵያ፡፡”
6)  የይፋት (ሸዋሮቢት) ፋኖ ተጋድሎ
       **************************
በፋኖ መከታው የሚመራው ጦር ከአጣዬ ጀምሮ ይፋት እስክንገባ ድረስ ከፍተኛ ወታደራዊ አቀባበል አድርጎልናል፡፡ ይህን መድረክ በማመቻቸት ደግሞ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት ደራሲ አሰግድ መኮንን ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ፣ በዚህ ጉዞ ወቅት የሕዝቡን ስሜትና ደስታ ስመለከት አንዳች ወኔ ነሽጦኝ፣ ከነበርኩበት የልዑካኑ መኪና ወርጄ፣ ፋኖዎቹ በያዙት ክፍት የቅስቀሳ መኪና ላይ ወጥቼ ንፁኋን የኢትዮጵያ ባንዴራ እያውለበለብኩ በቅስቀሳው እንደተሳተፍኩ ስገልጽ በኩራት ነው፡፡ ይህ ኹነትም ከሁሉም ጉዞዎቼ ስሜቴን በሚገባ ያንጸባረኩበት ነበር፡፡ በዚህ መድረክ ላይ ከፍተኛ የሞራልና የጀግንነት ንግግሮች ተደርገዋል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የአባቶቻቸውን ታሪክ ደግመው አገር ለማስቀጠል ለፈጸሙት ተጋድሎም ከጉልበታችን ጎንበስ ብለን ጥልቅ ምስጋናችንን አቅርበንላቸዋል፡፡ በመጨረሻም፣ በፋኖ ስም ሁላችንንም የልዑካኑ ቡድኑ አባላት ጋቢ ተሸልመናል፡፡ የፊታውራሪ አስማረ ዳኜ ምስልም ተበርክቶልናል፡፡
ሸዋ፣ ደብረ ብርሃን ላይ በፋኖ አበባው ሰለሞን የሚመራውን ጦር ጨምሮ፤ ወጣቶችና ሕዝቡ በዐፄ ዘርአ ያዕቆብ ከተማ ባዘጋጁልን ደማቅ አቀባበል ላይም፣ ወራሪው ቡድን በደብረ ብርሃን ሕዝብ ላይ የለመደውን ግፍ እንዳይፈፀም ከፍተኛውን ተጋድሎ አድርገው አገር በማስቀጠላቸው የክብር ምስጋና አቅርበናል፡፡ የዐፄ ዘርአ ያዕቆብ ምስልም በመታሰቢያነት ተሰጥቶናል፡፡
በዚሁ ከተማ ከምዕራብ ወለጋ በማንነታቸው ምክንያት የተፈናቀሉ ከዐሥር ሺሕ በላይ የዐማራ ተወላጆችን ስቃይና መከራ ተመልክተን እጅግ በጣም አዝነናል፡፡ ህፃናት በረሃብ ሲቆሉ፣ በብርድ ሲንዘፈዘፉ፣ እናቶች በመከራ ሲታመሱ ማየቴ ስሜቴን አብዝቶ ጎድቶታል፡፡ ነፍሰ-ጡር እናቶችም የእዚሁ ችግር ገፈት ቀማሽ መሆናቸው ደግሞ፣ ሰው መሆኔን እስክ ጠላ አስከፍቶኛል፡፡ ይህን እርግማን ቆጥሬ ሳልጨርስ፣ በመንገድ ላይ የወለደች የ15 ቀን አራስ ስመለከት፣ እናት እንደ መሆኔ መጠን ስቃዩ አጥንቴን ሰርስሮት አስለቅሶኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ፣ ለቅሶ መፍትሔ አይሆንምና፤ ለተፈጸመው ግፍ ተባባሪ ያልሆናችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፣ የእርዳታ እጃችሁን እንድትዘረጉላቸው በፈጣሪ ስም እማፀናለሁ፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችም ለእነዚህ ግፉእን ትደርሱላቸው ዘንድ ትለመናላችሁ፡፡
በጥቅሉ፣ ‹የሰው ልጅ ነን› የምንል ከሆነ እናቶችና ህፃናትን የሚያስርብ፣ የሚያስገድል ለመከራና እንግልት የሚያጋልጥ ሥርዐትን የምናወግዝ እና ችግሮችን በዝምታ የምናልፍ መሆን የለብንም፡፡ እኔም ይህን ችግር ተመልክቼ በ“ኢትዮ 360 ሚድያ” በማጋራቴ፣ ጋዜጠኛ እየሩሳሌም የዜና ሽፋን ስለሰጠችው በዚሁ አጋጣሚ በተጎጂዎች ስም አመሰግናለሁ፡፡
   7) ፋኖ ምን አለ?
           **********
በሰሜኑ ኢትዮጵያ በነበረኝ ቆይታ እጅግ ብዙ የፋኖ አባላትን በአካል ለማግኘትና ለማነጋገር ሞክሬያለሁ፡፡ ማግኘትና ማነጋገር ብቻ ሳይሆን፤ በትክክል አድማጭም ነበርኩ፡፡ በተረዳኋዋቸው መጠንም መከራና እንግልታቸውን፣ ስሜትና ፍላጎታቸውን፣ ቅሬታና ቁጭታቸውን ለእዚህ ጽሑፍ ታዳሚዎች እና ለሚመለከታቸው ክፍሎች በአጭሩ አስነብባለሁ፡፡
ሀ.  የፋኖ ጦርም ሆነ መከላከያ ሠራዊቱ “ባለህበት ቁም” መባሉ ክፉኛ አበሳጭቷቸዋል፡፡ የወያኔ ለከት-የለሽ ግፍ ያደረሰው የዘመናት ፍዳ በቅፅበት ተረስቶ ‹ጦርነቱ ይቁም› መባሉን ፈጽሞ አልወደዱትም፡፡
ለ.  የክልሉም ሆነ የፌዴራሉ መንግሥት የትጥቅም ሆነ የስንቅ ድጋፍ አለማድረጉ በጣም እንዳሳሰባቸው ተረድቻለሁ፡፡ ፋኖ በአገር ፍቅር ተነሳስቶ፡- ከመከላከያ፣ ከሚሊሻው እና ከልዩ ኃይሉ በመንፈስም ሆነ በሞራል በማይተናነስ መልኩ ለኢትዮጵያ  ሉዓላዊነትና ለሕዝቡ ደህንነት መስዋዕትነትን ከፍሏል፡፡ በዐማራ ክልል ያለ ወርሃዊ ደመወዝና ያለ አንዳች ዋስትና ከአሸባሪው ወያኔ ጋር ሲፋለሙ የተሰው በርካታ ፋኖዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ይህንን ተከትሎ የሸመገሉ ወላጆቻቸውን የሚጦር፣ ልጆቻቸውን የሚደግፍና የሚያስተምር አለማገኘቱ፣ በህይወት ያሉ ፋኖዎቻችን በእጅጉ አሳዝኗቸዋል፡፡
ሐ.  ፋኖ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ አንድ እየሆነና እየተናበበ ቢሆንም፤ አንድነቱን የማይፈልጉ አንዳንድ አባላት “የጎንደር ፋኖ”፣ “የሸዋ ፋኖ”፣ “የወሎ ፋኖ”፣ “የጎጃም ፋኖ”… እያሉ መከፋፈል ላይ መጠመዳቸውን ታዝቢያለሁ፡፡ ይሁንና፣ ከባህር ዳር ጀምሮ ጎንደር፣ ወሎና ሸዋ ስንዘዋወር ያናጋገርናቸው ፋኖዎች በሙሉ የሚፈልጉት የፋኖን አንድነትን እንደሆነ አረጋግጠውልናል፡፡ በአንድ እዝ ስር መደራጀት እንዳለባቸውም አጥብቀው ያምናሉ፡፡
መ.  ሌላው የፋኖ ትልቁ መልእክት ‹የአፋሮች ጥቃት፣ የእኛም ጥቃት ነው፡፡ የዐማራ ጥቃት የአፋር ጥቃት ሆኖ እያለ፣ አንዳንድ ኃይሎች ግን ሊከፋፍሉት መፈለጋቸው ተገቢ ስላልሆነ እጃቸውን ከፋኖ ላይ ማንሳት አለባቸው› ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው አስጠንቅቀዋል፡፡
ሠ.  የፋኖ ዓላማ መንግሥትን መጠበቅ ሳይሆን፤ አገር እና ሕዝብን መጠበቅ መሆኑንም ግልጽ አድርገዋል፡፡ ‹ከድሮ ጀምሮ አባቶቻችን በፋኖነት የአገር አደራ እንዳስጠበቁ የኖሩ ሲሆን፤ እኛም እነሱ ያወረሱንን አገርን የማስቀጠል ሥራ ነው የምንሠራው ብለዋል፡፡ ስለዚህም፣ መንግሥትና የሚመለከተው ሁሉ መሳሪያ ሊያስታጥቀው፣ ሊያሰለጥነው፣ ሊያመሰግነውና ሊያበረታታው ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የመንግሥት ሚዲያዎች፣ ከፋኖ አገራዊና ሕዝባዊነት አቋም በተቃራኒው ቆመው፣ ‹ፋኖ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ያለው በመሆኑ መሳሪያ ማውረድ አለበት› ማለታቸው ከፍተኛ ቅሬታ እንደፈጠርባቸው ተናግረዋል፡፡
ረ.  ሌላው ቅሬታ፣ በጦርነቱ ጊዜ ለተደረገው ተጋድሎ መንግሥት እውቅና ካለመስጠቱ በተጨማሪ፤ ‹የታሪክም ሆነ የድል ሸሚያ ተፈጽሞብናል› ማለታቸው ነው፡፡ በተመሳሳይ ‹በዚሁ ጦርነት፣ ታላቅ ጀግንነት የፈጸሙና በጀግንነት የተሰው የአገርና የሕዝብ የቁርጥ ቀን ልጆች አለመዘከራቸው፣ በዐማራ ሕዝብ ላይ እንደተፈፀመ ወንጀል ይቆጠራል› ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡
ሰ.  በእዚህ ታሪካዊ ጉብኝታችን ወቅት ካነጋገርናቸው በርካታ የፋኖ ቤተሰቦች ውስጥ የዘነጋኋቸው መኖራቸው እንደተጠበቀ፤ ጥቂቶቹን እዚህ ጋ ልጥቀሳቸው፡-
__የጀግናው እሸቴ ሞገስና የልጁን ይታገስ እሽቴን ቤተሰቦች አፅናንተናል፡፡ ደማቸው ወደፈሰሰበት ቦታ ሳላይሽ ሄደንም ጎብኝተናል፡፡ የእነሱን ትግል ለማስቀጠልም፣ በቦታው ተንበርክከን ቃል ገብተናል፡፡
__ጎንደር ላይ ቻላቸው እንየው እና ፍትጉ ካሴ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው በጀግንነት ሲፋለሙ ልጆቻቸውን በትነው ተሰውተዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውን በምናጽናናበት ጊዜ ለልጆቻቸው የሚሆን ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ነግረውናል፡፡ በቦታው በነበርንበት ጊዜም በተቀበልነው አድራሻ የተወሰነ የድጋፍ ሥራ ለመሥራት ተችሏል፡፡ ደሴ ላይም ይመር ሰይድ የተባለውን የተሰዋ ጀግና ፋኖን ቤተሰቦች አጽናንተናል፡፡
__በጦርነቱ የአካል መጉደል የደረሰባቸውና የቆሰሉ አባላትን በየሆስፒታሉ እየሄድን ተዟዙረን ጠይቀናል፡፡ የየሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎችም በቂ የሕክምና መሳሪያ እንደሚያስፈልጋቸው ነግረውናል፡፡
8)  ማጠቃለያ
 
“የኋላው ከሌለ፣ የለም የፊቱ!” 
  **********************
መንግሥት፣ በአሁኑ ወቅት ምን እያደረገ እንዳለ የተረዳ አይመስልም፡፡ ‹አገሬ ከምትፈርስ፣ እኔ ቀድሜ ልፍረስ› ብሎ የሚወዳቸውን ሚስቱንና ልጆቹን አውላላ ሜዳ በትኖ፣ የሚያርስበትን በሬ ሽጦ ጠመንጃ ገዝቶ እብሪተኛውን ወራሪ የተፋለመ ሕዝብ ነው፡፡ ፋኖ፣ መንግሥት ‹ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ስለሆነ፣ መፍረስና ትጥቁን መፍታት አለበት› ሲል ምን ማለቱ ይሆን? ‹ሕወሓት፣ የትግራያን ሕዝብ ከኋላው አስከትሎ የሕዝብ ማዕበል ፈጥሮ የወረረን ስለሆነ፣ እኛም በመደበኛው የፀጥታ ኃይል መከላከል አንችልም፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ጠመንጃ ያለው ግለሰብ መሣሪያውን እየያዘ ለዘመቻው ይውጣ!› ብለው በይፋ የክተት ጥሪ ያወጁት የዐማራ ክልልና የፌዴራሉ መንግሥታት አይደሉም እንዴ? እናሳ፣ ያኔ የጭንቁ ጊዜ ‹በኢ-መደበኛ አደረጃጀት መዝመት አይቻልም› ለምን አልተባለም? ‹መሳሪያ የሌለው ጀሌ ከጠላት የማረከውን የነፍስ-ወከፍ መሳሪያ ለራሱ በመውሰድ መታጠቅ ይችላል› ተብሎ መታወጁስ እንዴት ተረሳ?! በእኔ የግል እምነትና አመለካከት በፋኖ የህይወት መስዋዕትነት ድል ከተገኘ በኋላ፤ ዛሬ ‹ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ነውና፣ ፋኖ ትጥቁን መፍታት አለበት፤› ማለት የልጆች ጨዋታ ከመሆን የዘለለ አይፈይድም፡፡
ፈጽሞ መዘንጋት የሌለበት ቁም ነገር ግን፣ እያንዳንዱ ዐማራ አገር ሠላም ሲሆን ያርሳል፣ ይነግዳል፣ ይማራል፣ ያስተምራል፡፡ አገር ችግር ላይ ስትወድቅ ደግሞ፣ ለአገሩና ለወገኑ ፋኖ መሆኑን ነው፡፡ መቼም፣ ‹ጠመንጃ በግለሰብ ደረጃ መያዝ ለዐማራ እና አፋር ለሺሕ ዐመታት የቆየ ባህላቸው ነው› ብሎ ለማስረዳት መሞከር፣ ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ ሲወርድ ሳዋረድ የቆየ ነባር ባሉ ነውና፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ወይም የኦዴፓ ብልጽግና አመራሮች (መንግሥታዊ ሥልጣኑን የያዙት እነሱ ናቸውና፤) የሕወሓትን ፈለግ እየተከተሉ ይመስላል፡፡ ሕወሓት በ27 ዐመታት የመንግሥትነት ዘመኑ፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሚኖሩ ዐማሮች ላይ ጥቃት ማድረስ የቻለውና ያስቻለው፣ በመጀመሪያ ትጥቃቸውን እያሰፈታ መሆኑ ፀሀይ የሞቀው እውነት ነው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥትም ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ፣ በወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ዐማራዎች በጅምላ የተገደሉት፣ የተዘረፉትና የተፈናቀሉት ትጥቃቸውን እንዲፈቱ ከተደረገ በኋላ ነው፡፡ አሁን ደግሞ፣ የዐማራ ሕዝብ ባላሰበውና ባልጠረጠረው ሰዓት፣ ‹ግብርና ቀረጥ የምከፍልበት፣ ሠላምና ፍትሕ ማስፈን የሚችል መንግሥት አለኝ› ብሎ ተረጋግቶ መደበኛ ሥራው ላይ እያለ፣ በሴራ ፖለቲካና በሕወሓት አሸባሪ ኃይል በከባድ መሳሪያ ተደበደበ፡፡ አገርና ሕዝብ ያገለገሉ የተከበሩ አዛውንቶች በገዛ ቀያቸው ተዋረዱ፡፡ ጠላት ሴት ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን በፊታቸው ላይ አነወረ፡፡ መንግሥት ይህ ሁሉ ሲሆን በዝምታ ተመልክቷል፡፡ “ጠላትህን ውሃ ሲወስደው፣ ጥቂት ምራቅ ጨምርበት!” የሚለውን ብሂል ተከትሏል ለማለት ቢከብደኝም፤ የሆነው ግን ከዚህ ውጭ አልነበረም፡፡
የፌዴራሉም ሆነ የክልሉ ተለጣፊ መንግሥት የዐማራን ሕዝብ መታጠቅ ስለምን ጠላው? ‹እንደ ሕወሓት አሸባሪ ይሆናል ወይም በትጥቅ ትግል የመገንጠል ጥያቄ ያነሳል በሚል ሰግተው ነው› እንዳይባል፤ ዐማራ ይሄ ሁሉ የጥቃት ውርጅብኝ የሚደርስበት ለኢትዮጵያዊነቱ ሲል በሚከፍለው ዋጋ እንደሆነ ሁለቱም አካላት ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ምናልባት ‹ዐማራ እያለ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠልን መተግበር አንችልም› በሚል ፍራቻ ከሆነ ግን፣ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ የዐማራ ሕዝብ እያለ ኢትዮጵያን መበታተን ጨርሶ አይታሰብምና፡፡ በተረፈ፣ ዐማራ ጠመንጃ ቀርቶ፣ ኒውክለር ቢታጠቅ፣ በየትኛውም አካባቢ ላለ ኢትዮጵያዊ ሥጋት መሆን አይፈልግም፡፡ ለኢትዮጵያዊነት የአብሮነት እሴቶችም ክቡድ ዋጋ የሚሰጥና ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለው ሕዝብ ነው፡፡
በጥቅሉ፣ መሬት የረገጠው እውነት ይህ ሆኖ ሳለ፤ ዐማራን ትጥቅ ለማስፈታት የሚዶልተውን የፖለቲካ ሴራ የሚያውቀው ራሱ መንግሥት በመሆኑ፣ ከዚህ በላይ ባልሄድበት ይሻላል፡፡ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር ግን፣ የዐማራን ሕዝብ ትጥቅ ለማስፈታት መፈለግ፤ ‹አንድ ካህንን ማተብህን በጥስ፣ ጥምጣምህን አውልቅ ወይም ሙስሊሙን ቅዱስ ቁራንህን ተው፣ ቆብህን አውልቅ› የማለት ያህል ነውና፣ ፈጽሞ አያግባባንም፡፡
በአሁኑ ወቅት ከመንግሥትም ሆነ ከመላው ኢትዮጵያዊ የሚጠበቀው፣ ዐማራ ጦርነቱ ባደረሰበት ውድመት ከቤት ንብረቱ በመፈናቀሉ፡- መርዳት፣ ማገዝ፣ ማበረታትና ማጽናናት ነው፡፡ በተለይ መንግሥት ይህንን ዐይነተኛ ኃላፊነቱን የመወጣት ግዴታ እንዳለበት ባይዘነጋ ይመከራል፡፡ የአገሬ ሕዝብ “የኋለው ከሌለ – የለም የፊቱ!” እንዲል፤ ዜጎች በጋለ ስሜትና ፍቅር ለአገራቸውና ለሕዝባቸው በቁርጠኝነት እንዲቆሙ፣ ጦርነቱ ወላጅ አልባ ያደረጋቸውን የፋኖ ልጆችን ሰብስቦ መርዳት፣ አስተምሮ ለወግ-ማዕረግ ማብቃትም፣ የወል ነጋችንን ያሳምረዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
Filed in: Amharic