በኢትዮጵያችን ላይ የተዘራው (እና ፍሬ ያፈራው) ታላቁ ሴራ!
አሳፍ ሀይሉ
ይህን የኢትዮጵያችንን አበሳ የሚያሳይ ካርታ ያገኘሁት የዓለም የትምህርትና ሳይንስ መርጃ ድርጅት (ዩኔስኮ) ካሳተመው «UNESCO – Africa under Domination» ከሚል መጽሐፍ ላይ ከተካተተ የምርምር ፅሑፍ ነው፡፡ በክፍለዘመኑ ማገባደጃ አካባቢ (ከአድዋ 12 ዓመት በፊት) ጉልበት ያላቸው አውሮፓውያን ሀገሮች በርሊን ላይ ተሰብስበው አፍሪካን ሲቀራመቱ፣ ኢትዮጵያችን ብቻ አልበላ፣ አልዋጥ ብላቸው ተቸግረዋል፡፡ በዚህ መልኩ ዙሪያዋን ከበዋት ሊበሏት አሰፍስፈው ነበር፡፡
ከላይ እንግሊዞችና ጣሊያኖች ከግብጾችና ሱዳኖች ጋር ሆነው፡፡ በምዕራብ በኩል ፈረንሳዮችና እንግሊዞች ከግብጾች ጋር ተቀናጅተው፡፡ በደቡብ እንግሊዝ በዩጋንዳና ኬንያ ያሏትን ቅኝ ግዛቶች አስተባብራ፡፡ በደቡብ ምስራቅ ጣልያኖችና እንግሊዞች ከሶማሊያ ያሏቸውን ይዞታዎች አስታጥቀው እየገሰገሱ፡፡ ከምስራቅ ፈረንሳዮች በጂቡቲ በኩል፣ ከሰሜን ምስራቅ ቱርኮች የኤደንን ባህረሰላጤ ተሻግረው እያኮበኮቡ፣ እንግሊዞች፣ ጣልያኖችና ግብጾች ከምፅዋ በኩል መጣንባችሁ እያሉ፡፡ እንዴ!
ይቺ ኢትዮጵያ የሚሏትን የጉድ ሀገር፣ አያት ቅድመ-አያቶቻችን በምን ተዓምር በጉልበተኛ አውሮፓውያንና ሌሎች ከባቢዎቿ ከመበላት እንዳዳኗት እንቆቅልሽ ይሆንብኛል፡፡ በካርታው ላይ ያለውን ቀይ መስመር ያሰመርኩት እኔ ነኝ፡፤ ካርታው የከበቡንን ኃይሎች ከነሚያሳዩት ቀስቶቹ በዩኔስኮ ህትመት የተካተተ ነው፡፡ በ1950ዎቹ የተሠራ ካርታ፡፡ ይህን ጉድ እያየሁ – ጉድ ነው የምለው፡፡ ምን ዓይነት ዓለምን ገትረው የያዙ ንቁ፣ አይበገሬ፣ አይነኬ፣ አያት-ቅድመ-አያቶች ነበሩን?! ያኮራሉ በእውነት!
በሌላ በኩል የዚያ ተጋድሎና ዙሪያችንን ከበባ ውጤቱ እጅግ ሲያሳዝነኝ ይኖራል፡፡ ዙሪያችንን ከበው፣ ሌላ ቀርቶ አራት ቦታ ተቆራርጣ በየጉልበተኛው እንደ ቅርጫ ተዘነጣጥላ ስትገዛ የኖረችው ሀገር-አልባዋ ሶማሊያ – ዙሪያዋ ወደ ውቅያኖስና ባህር የሚያዋስኗት መተንፈሻ ስትከበብ፣ ሁሉም በየፊናው የባህርና የውቅያኖስ መውጫ ሲኖረው፣ ኢትዮጵያችን ግን በጉልበተኞቹ ከበባ ልትደፈር ያልቻለች ደሴት ሆና በመገኘቷ የተጣለባት ቅጣት – ወደ ባህርና ውቅያኖስ ውልፍት ለማለት እንዳትችል ተደርጋ መከርቸም ነው!
ሶማሊያና ኤርትራ ሳይቀር እንደ ሀረግ እየተጥመለመሉና እየተሳቡ ዙሪያችንን ባህርና ውቅያኖስ የተባለ እንዳናይ አንዲት ቁራጭ መሬት እንዳይኖረን ሲያደርጉን፣ ኢትዮጵያችን በመሬት የምትላወስ የተጎመደች ዱሽ፣ ጉንድሽ ፍጡር ሆና እንድትቀር ተደርጋለች፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል ጉልበተኞቹ የዓለም መንግሥታት የቻሉትን ሁሉ የተጋጋጡት – ያንኑ ኢትዮጵያ ላይ የተጫነውን እርግማን ለማስፈጸም ነው፡፡ እንጂ የኤርትራን ህዝብ ለመጥቀም በፍጹም አይደለም!
ጂቡቲን ብንወስድ፣ በሥነስርዓት በተፈረመ የሊዝ (ኮንትራት) ውል ለፈረንሳዮች ተላልፋ የተሰጠችው የኢትዮ-ጂቡቲ የምድር ባቡርን ለኢትዮጵያ ሲገነቡልን፣ በምትኩ የጂቡቲን ወደብ ይዘው እንዲጠቀሙበት ነበር፡፡ በ1977 ዓመተ ምህረት ላይ ያ ውል ያበቃ ነበር፡፡
በዚያን ወቅት ከሶማሌ በኩል ያስወረሩንን ወረራ መክተን እንደ ሀገር ቀና ማለት ስንጀምር፣ ደግሞ በሰሜን በኩል ኤርትራማ ትግራይን ተጠግተው ጦርነትን በእጃዙር በማጋጋልና የጀርባ አጥንት ሆነው በመደገፍ፣ ኢትዮጵያ ትንፋሽ አግኝታ ጂቡቲን በውሏ መሠረት እንዳትረከብ የቻሉትን ሁሉ ሽብርና ግርግር ፈጠሩ፡፡ ተሳክቶላቸዋልም፡፡
ምክንያቱም ኢትዮጵያ የተከበረችና የተረጋጋች ጠንካራ ሀገር ብትሆን ኖሮ፣ ሳይወዱ በግዳቸው፣ እንግሊዝ ለቻይና ሆንግኮንግን በስምምነቷ መሠረት አስረክባ ውልቅ ብላ እንደወጣችው ውልቅ ብለው ከጂቡቲ ይወጡ ነበር፡፡ ግን ያ አልሆነም፡፡ ሸፍጣቸው ያዘላቸው፡፡ ስለዚህ አንድ ዓመት ጠብቅ በ1978 ላይ በጂቡቲ ህዝበ-ውሳኔ አደረጉ፡፡
እና የጂቡቲ ህዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ወስኗል ብለው፣ ፈረንሳዮች በእጃዙር የሚያዙት የጂቡቲ መንግሥት አቋቋሙ፡፡ ዓለም እንደዛሬ በፈጣን ንግድ ሳትተሳሰር፣ የጂቡቲዎቹን ከቲማቲም እስከ ብርቱካንና ጫት ድረስ የምንቀልበው እኛ ነበርን፡፡ ከእኛ በሚሄድላቸው እህል፡፡ እንጂ በበረሃ ጠኔ ያልቁ ነበር፡፡
የሆነ ሆኖ የኤርትራንም ታሪክ የምናውቀው ነው፡፡ በአንድ የ30 ዓመት ዕድሜ ባለው ወጣት ዕድሜ የሆነ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነውና አላነሳውም፡፡ ኤርትራንም ከነህዝቧ፣ ከኢትዮጵያ ጋር በታሪክ፣ በደም፣ በአስተዳደር፣ በህግም ሆነ በሁሉ ነገር ከነተሳሰረች ከኢትዮጵያ ጋር በጉልበት አሸንፈው አስገነጠሉ፡፡
ያን ሁሉ ሲያደርጉ ዋና ዓላማቸው ለባርነት አላመች ያለቻቸውን ኢትዮጵያን አሽመድምዶ ማስቀረት ነበር፡፡ በአፍሪካ ያሉ ግዛቶቻቸውን ሁሉ ምሳሌ ሆናና ከጎን ሆና እየረዳች ያስወሰደችባቸውን ኢትዮጵያን አይቀጡ ቅጣት መቅጣት ነበር ዓላማቸው፡፡ ዓላማቸው በዓለም ያሉ በቅኝ የተገዙ ህዝቦች ሁሉ ብቻቸውን ቢኖሩ ምን ዓይነት ክፉ አበሳ እንደሚጠብቃቸው የተገነዳደሸችው ኢትዮጵያ ላይ እየጠቆሙ መዘባበቻ ማድረግ ነበር፡፡
ይህ ሁሉ ዕቅዳቸው በዘዴና በማባበል፣ በዲፕሎማሲና በስልት፣ በከባድ መቋቋምና መስዋዕትነትም፣ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አማካይነት እየከሸፈባቸው ነበር፡፡ ወይም የነበረ ይመስለኛል፡፡
የራሳችን የድሆች እንባ የወለደው፣ በዓለም የተቀጣጠለው የጭቁን ህዝቦች ሶሻሊስታዊ አብዮት የወለደው አመጽና የዙፋን ነጠቃ፣ የሥርዓት መደምሰስ፣ ኢትዮጵያ በወዛደራዊ ሶሻሊስት ርዕዮተዓለም አራማጆች እጅ መውደቅ፣ የጉልበተኞቹን አሜሪካኖችና አውሮፓውያን የሚቀናቀን ወታደራዊ ሶሻሊስታዊ አምባገነን መመስረት፣ እነዚህ ሁሉ ተደማመሩና፣ የምሥራቁ የሶሻሊስት ጎራ ሲፈራርስ፣ የኢትዮጵያም ለክፍለዘመን የተሰራባት የከበባና የማድቀቅ ታላቁ ሴራ ታላቁን ድሉን ተቀዳጀ፡፡
የኢትዮጵያ ከበባ ተሰበረ፡፡ ተበታተነች፡፡ የባህር ድንበሮቿን ተነጠቀች፡፡ ውስጧ በዘር፣ በቋንቋ፣ በቀለም፣ በፆታ እየተመተረ – ገና ለወደፊቱ 500 ዓመት ከራሷ ጉያ ከሚመጣባት መበጣጠስና መተላለቅ እንዳታገግም ተደርጎ ውስጧ ተገዘገዘ፣ ተሰነጣጠቀ፡፡ ይህን የሚያውቅ ትውልድም እንደሻማ ቀልጦ ጠፋ፡፡
የእኛ የኢትዮጵያውያን ታሪክ፣ በእንዲህ ያለ የመቶ ዓመት ሸፍጥና የበቀል በትር – በእኛ ኢትዮጵያውያን አያቶች ቅድመ-አያቶች አጥንት ላይ ቆመን – በቁማችን መሸነፋችን ብቻ ያስቆጨኛል፡፡ ለዘለዓለም እንዳንነቃ ሆነን ከክብራችን ወርደን ዝቅ ብለን መገኘታችን ብቻ ያስቆጨኛል፡፡ እነዚያ ማንነታቸውን የሚያውቁ አይበገሬ ትውልዶቻችን አልፈው፣ ታሪኩን የማያውቅ፣ እርስበርሱ የሚጫረስ፣ የታሪካዊ ጠላቶቻችን ዓላማ አስፈጻሚ አንበጣ ትውልድ ሀገሩን መውረሩ ያሳዝነኛል፡፡
በአፍሪካ ታሪክ እንደ ኢትዮጵያ ሸፍጥ የተሰራበት፣ ካርታው የተሸለተበት፣ ሕዝቡ ለቅርጫ የተዳረገበት፣ አንድም ትውልድ፣ አንድም ሀገር የለም፡፡ በዓለምም ታሪክ የለም፡፡ እንደምናውቀው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት ጀምሮ የዓለም ካርታ የተቀየረው በኢትዮጵያና በሶሻሊስቱ ጎራ አብረው በመገኘታቸው የበቀል በትር ባረፈባቸው የምስራቅ አውሮፓና ሩሲያ ላይ ብቻ የተሠራ የግፍ ታሪክ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የማወራው የብዙ ድርሳኖች፣ የብዙ ዓመታት፣ የብዙ የተደረቱና ውጥንቅጣቸው የወጣ ታሪኮች ጠብታ ታሪክ ነው፡፡ ሁሉ ቢዘረዘር ዘመን አይበቃውም፡፡ ቦታ አይበቃውም፡፡
ከዚህ ሁሉ ቁጭትና መንገብገብ ወጥቼ እርፍ ስል የሚቀረኝ ነገር – እንጥፍጣፊ ተስፋ ብቻ ነው፡፡ ከሩቅ የሚታይ የተሟጠጠ ብሩህ ተስፋ፡፡ ደግሞም ያቺ ተስፋ ቀን ወጥቶላት መለምለሟ አይቀርም፡፡ ከታሪካችን ሊያፋቱን የውጭና የውስጥ ጠላቶቻችን የሚዳክሩት፣ ትውልዶቻችን ያቺን የተሟጠጠች ተስፋና የሚያኮራ ታሪካቸውን እንዳያዩ ለመከለል ነው፡፡ ከታሪኩ የተፋታ ብኩን ትውልድ ለመፍጠር ነው፡፡ አንድ ቀን ታሪኩን አንግቦ፣ ባንዲራውን አውለብልቦ የሚነሳ ኃያል ትውልድ እንዳይፈጠር በአካል ያደቀቋትን ኢትዮጵያችንን በመንፈስም ለመግደል ነው፡፡
ነገር ግን የዓለም ታሪክ የሚያስተምረን፣ ፍትህ እና ሀቅ ለዝንተ ዓለም ተደብቃ እንደማትቀር ነው፡፡ ታሪክ ተቀብሮ እንደማይቀር ነው፡፡ አንድ ቀን ይህቺ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት የነበረች ሀገራችን፣ ከራሷ የሆድ ቁስል አገግማ፣ አንገቷን አቃንታ፣ በዓለም ፊት ወደቀደመ ክብሯ እንድትመለስ የሚያደርጉ፣ የነቁና የሠለጠኑ ብልህ አርቆ አሳቢ ትውልዶች ከማህፀኗ እንደሚበቅሉላት በግሌ አንዳችም ጥርጥር የለኝም፡፡
መቼ ነው ያ የሚሆነው? ማናችንም የምናውቀው አይመስለኝም፡፡ የዛሬ 50 ዓመትም ይሁን! መቶ ዓመትም ይፍጅ! አምስት መቶ ዓመትም፣ ሺህ ዓመትም ይፍጅ! አንድ ቀን ግን በእርግጠኝነት መሆኑ አይቀርም! አንድ ታሪኩን ያነገበ፣ የአያት ቅድመ-አያቶቹ ተጋድሎና አጥንት ከተቀመጠበት ወግቶ የሚያስነሳው፣ አንድ ታሪክ-ሠሪ ኢትዮጵያዊ ትውልድ፣ በአንድ በፊታችን በተዘረጋው ዘመን ላይ መነሳቱ አይቀርም! ለዚህ ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም! አንድ ቀን – ይህ መሆኑ አይቀርም!
እስከዚያው በጥቃቅን አጀንዳዎቻችን እየተባላንም ቢሆን – ኢትዮጵያችንን አሰንብተን አብረናት ለመሰንበት፣ ትውልዶቻችንን ለማሰንበት ፈጣሪ አምላክ ያብቃን !
ሰናይ ሰንበት!