>

‹‹ውጊያ ከአማሌቃውያን ጋር›› (ከይኄይስ እውነቱ)

‹‹ውጊያ ከአማሌቃውያን ጋር››

ከይኄይስ እውነቱ


የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለፉት ሠላሳ አንድ የግፍና የሰቈቃ ዓመታት አገርና ሕዝብን ለማጥፋት ከተነሡበት ‹‹አማሌቃውያን›› ጋር አምላኩን በመተማመን ለሰልፍ መውጣት የማይቀር ግዴታው የሆነበት የታሪክ አጋጣሚ ላይ ደርሰናል፡፡ በዚህ ጽሑፍ አግባብ ‹አማሌቃውያን› የምንላቸው የእቡዳነ አእምሮ ውጤት የሆነው ኢሕአዴግና አዋልዱ በተለይም ብአዴን የተባለው የወያኔ ትግሬና የኦነግ/ኦሕዴድ ቅጥረኛ እና የኋለኞቹ ውሉደ ዲያቢሎስን ነው፡፡ 

በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተመዘገበው እግዚአብሔር አምላክ የኤርትራን ባሕር ከፍሎ በደረቅ እንዲሻገሩ አድርጎ እሥራኤላውያን ከግብጽ ባርነት በጸናች ክንድና በብዙ ተአምራት ካወጣቸው በኋላ በመንገድ ላይ አማሌቅ የሚባል ኃይለኛ ጠላት ገጠማቸው፡፡ ክቡድ የሆነውን ጠላት በጸሎትና በጦርነት ድል ነሡት፡፡ መሪያቸው ሙሴ በአሮንና ሖር እየታገዘ፤ ኢያሱ ደግሞ ጎልማሶችን መርጦ ለጦርነት በማሰለፍና በመምራት፡፡ ዛሬም  አባቶቻችንና እናቶቻችን በጸሎትና በብዙ ተጋድሎ ከፈተና ጠበቀው ያቈዩልንን ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ወደ ልዕልና በመሻገሪያዋ ዘመን በመንገድ ላይ ቆመው መርዛማ የጥላቻና የመለያየት የዘር/ጐሣ ፖለቲካ አንግሠው ዜጎቿ ርስ በርሳቸው እንዲተላለቁ ወደ ድንቊርናና ኋላ ቀርነት ዘመን እንዲመለሱ ‹አማሌቃውያን› በመንገዳችን ላይ ቆመዋል፡፡ እኛን የሚፈታተኑን ‹አማሌቃውያን› ግን በተለይም በአገዛዙ ወገን ፈሪና ጨካኞች ናቸው፡፡ ‹ክቡድና ቁጡ› ነን የሚሉት ሽብር ፈጣሪ ወያኔዎችም ቀሊልና ጨካኞች እንደሆኑ ታይተዋል፡፡ ቦቅቧቆቹ ኦነግ/ኦሕዴድም ሆኑ ‹ክቡድ› ነን የሚሉት ወያኔዎች ጉዞአችንን እንዳይገቱ ከመንገዳችን ማስወገድ የኢትዮጵያውያን ሁሉ  ግዴታ ነው፡፡

አሁን ጊዜው ፈረንጆችን መለማመጫ፣ ‹አማሌቃውያን› በጅምላ ሲፈጁን፣ ዕለት ዕለት ሲያፈናቅሉን፣ በገሃድ ሲቀጥፉንና ‹ድርድር› እያሉ ሲያጭበረብሩን፣ በኑሮ ውድነት ቁም ስቅላችንን ሲያሳዩን እጃችንን አጣጥፈን የምንቀመጥበት ጊዜ አይደለም፡፡ ሰይፍ መምዘዝ የሚከለከልበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ ‹አማሌቃውያንን› ጦርነት ለመግጠም አምላካዊ ትእዛዝ የሚሰጥበትም ጊዜ አለ፡፡ ያ ጊዜ ዘገየ ካልተባለ በቀር አሁን ይመስለኛል፡፡ በየትኛውም ቤተ እምነት የምትገኙ የአገራችሁ ህልውናና አንድነትን÷ የሕዝባችሁን ሰላምና ደኅንነት የምታስቀድሙ እውነተኛ/መንፈሳውያን አባቶችና እናቶች ወንድሞችና እኅቶች እጃችሁ ሳይዝል ለጸሎት ይዘርጋ፡፡ እርዳታው እንዳይለየን አንዱ ሲዝል ሌላው ይደግፈው፡፡ እኛ (ከአማሌቃውያን ጋር ኅብረት የሌለን የኢትዮጵያ ልጆች) ደግሞ ፈጣሪን ጥግ አድርገን በሠራዊታቸውና በመሣሪያቸው ብዛት፣ ከሕዝብ በዘረፉት ሀብትና ንብረት ተማምነው ሊያጠፉን የተነሡትን ‹አማሌቃውያን› ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተዋግተን መብትና ነፃነታችንን ማስከበር የውዴታ ግዴታችን ነው፡፡ ‹አማሌቃውያኑ› ከአንድ መራራ ፍሬ የተገኙ እንክርዳዶች ናቸው፡፡ እንገዛዋለን የሚሉትን አገርና ሕዝብ እያጠፉ በብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ ከነሱ ጋር ለመምከርና መፍትሄ ለመፈለግ ማሰብ ገራሚ እንቆቅልሽ ነው፡፡ አገዛዙ ማነው? በሸፍጥ ሥልጣን ይዞ ኃይልን የመጠቀምና ሀብትን በዝርፊያ የማጋበስ ዕድል ስላገኘ ብቻ አገር የማዳኛ ብሔራዊ አጀንዳን ማን ቀራፂና ወሳኝ አደረገው? ሕዝብ አገሩን መታደግ የሚፈልገው ከ‹አማሌቃውያን› እጅ ሆኖ ሳለ እነርሱ ሥር መርመጥመጥ ምን ይሉታል?

ለትግል ድርጅት አስፈላጊ መሆኑ ጥያቄ ውስጥ ባይገባም፤ ዛሬ ኢትዮጵያ ‹አማሌቃውያንን› በጥብዐት (ለበጎ በመጨከን) የሚዋጋላት ወይም ይህንን ውጊያ የሚያስተባብርላት እውነተኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት የላትም፡፡ ጥቂት ኢትዮጵያውያን በግለሰብ ደረጃ ነፃነታቸውን በማጣት (በወህኒ ቤት) የከፈሉትን መሥዋዕትነት መቼም አንዘነጋውም፡፡ በተልከስካሹ ኦነግ/ኦሕዴድ በግፍ የተገደሉና የተፈናቀሉ ሕፃናት፣ሴቶችና አዛውንትን እንዲሁም በቅርቡ ‹ከአማሌቃውያን› ጋር በተደረገው ጦርነት ውድ ሕይወታቸውን የሰጡትን፣ የአካል ጉድለትና የመንፈስ ጉዳት የደረሰባቸውን፣ ቤት ንብረታቸውን አጥተው ሜዳ ላይ የፈሰሱትን እና በረሃብ አለንጋ የሚጠበሱ ወገኖቻችንንም በታላቅ ክብር እናስባቸዋልን፤ ሐዘናቸውም በጥልቁ ይሰማናል፡፡ ‹መንግሥት በሌለበት› አገር ተቈርቋሪ የላቸውምና በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለን ኢትዮጵያውያን አርሰው የሚያበሉንን ወገኖች እንድረስላቸው/እናቋቁማቸው፡፡

ጦርነቱ እንደ ሰውና ኢትዮጵያዊ የመኖር/ያለመኖር፣ ባለ ሀገር/ሀገር አልባ የመሆን/ያለመሆን፣ በተፈጥሮ ያገኘነውን በሕይወት የመኖር መብትና ነፃነታችንን የማስከበር፣ ለዚህም የማይተካ ሕይወታችንን ቤዛ በማድረግ ጭምር አሁን ላለነውና ለመጪውም ትውልድ የሚዘልቅ ሉዐላዊ የሆነ ዓላማ ከግብ ለማድረስ ነው፡፡ በዚህ ዲያቢሎስና አዋልዱ በሠለጠኑበት ዓለም አንፃራዊ ሰላም፣ መብትና ነፃነት በብላሽ አይገኙም፡፡ ዋጋ ያስከፍላሉ፡፡ ርእሰ መጽሐፉ ኵሉ ጻድቅ በጊዜ ርቱዕ ይላል፡፡ አሁን በተጠቀምሁበት ዐውድ ያልተነካ ግልግል ያውቃል በሚል ወስጄዋለሁ፡፡ ሰላማዊ የምትሉትን ትግል በዚያን ጊዜ (‹በጊዜ ርቱዕ›) ለሕዝባችን እናስተምረዋለን፡፡ አሁን ግን ‹አማሌቃውያን› በደጃችን ቆመዋል፡፡ ዝም ብሎ ለዕርድ መዘጋጀትን ምድራዊውም ሆነ ሰማያዊው ሕግጋት አይፈቅዱም፡፡ 

የእናቴ ልጅ ርኅሩኅ እናትህ፣ ግርማ ሞገስ አባትህ፣ አፍቃሪ ሚሽትህ፣ ዞሮ መግቢያ ቤትህ፣ መጠጊያ አምባህ፣ ማምለኪያ ቤተመቅደስህ/መስጂድህ የሆነችው አገርህ ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በተለየ አሁን ትፈልግሃለች፡፡ ስለ ጋራ ቤታችን ኢትዮጵየ ብለህ፣ ነግ በኔን አስበህ፣ የእምነት ልዩነት ሳይዝህ፣ ጐሣ/ዘር ሳትቈጥር የአንዱ ማኅበረሰብ መጠቃት የኔ ነው ብለህ ለወገንህ ድረስለት፡፡ በሰንደቅህ፣ በእምነትህ ምክንያት የሚያርዱህን እምነት አልባ ከሀዲዎችን እምቢኝ በቃ ልትላቸው ይገባል፡፡ 

እሥራኤላውያንን ከአማሌቅ የታደገ አምላከ ሙሴ የእናቱ ርስት የሆነችውን ኢትዮጵያንም ከዘመኑ ‹አማሌቃውያን› ይታደግልን፡፡ የርኵሰት ኃይሎች ከሆኑት ‹አማሌቃውያን› ጋር ለሚዋጉት ኢትዮጵያውያን ኃይሉን፣ ጽንዑን፣ ብርታቱንና ድል መንሣቱን ይስጥልን፡

ማሳሰቢያ፤ 

የአገራችን ጉዳይ እንቅልፍ ነሥቷችሁ በዐውደ ውጊያ የምትገኙ ዜጎች፣ ለወገን አስተያየታችሁንና ምክራችሁን የምታካፍሉ ጸሐፍት፣ በጦርነትና አገዛዝ ወለድ በሆኑ ችግሮች ለሚሰቃይ ወገናችን ያላችሁን የምታካፍሉ ባገር ውስጥና በውጭ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ላገዛዙ ያላደራችሁ መደበኛም ሆናችሁ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃኖች፣ ላገዛዙ ያላደራችሁ ዐቅሙም ባይኖራችሁ የተቻላችሁን ያህል የምትፍጨረጨሩ ‹ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች› ካላችሁ፤ ሥርቻ ለሥርቻ እየተርመጠመጠና እየተልከሰከሰ በሕፃናት፣ በሴቶችና አዛውንቶች ላይ የፈሪ ዱላውን የሚሰነዝረውን ጨካኙን ኦነግ/ኦሕዴድ፣ ‹ሸኔ› በሚል መጥራታችሁን እንድታቆሙ በወላዲተ አምላክ ስም እማፀናችኋለሁ፡፡ ‹ሸኔ› የሚባል አካል የለም፡፡ አገዛዙ ከተጠያቂነት ያመለጠ መስሎት የፈጠረው በተግባርም በሕግም የሌለ ‹ማስፈራርቾ› (ghost) ነው፡፡ ይህንን ስም በመጥራት ግፍ የደረሰባቸውን ወገኖቻችንን ዳግም እየበደልንና አገዛዙንም እየተባበርን ነው፡፡ ላለፉት አራት ዓመት የሚጠጋ ጊዜ በወለጋ፣ በጎጃሙ መተከል፣ ወያኔ ‹ኦሮሚያ› ብሎ በፈጠረው ግዛት፣ በኮንሶ፣ በአማሮ፣ በጋምቤላና በሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍሎች ታይቶ ተሰምቶ የማያውቅ ግፍ እየፈጸመ ያለው ሽብርተኛው ኦነግ ወይም ታናሽ ወንድሙ ኦሕዴድ ነው፡፡

Filed in: Amharic