ብልጽግና ላይ ነን ይሉናል፤ ሃገር እየፈረሰ፣ እየተቃጠለ ነው…..!!!
ምኒልክ ሳልሳዊ
* …. እውን የሃገር ስጋት እና የህዝብ ጠላት ማነው ?
የኦነግ ሰራዊትን ታንክና መድፍ ለማስታጠቅ እየደከመ ያለው የኦሕዴድ-ብልጽግና የኦነግ ሰራዊት መንግስት ሸኔ የሚለው በከፍተኛ የግብር እና ቀረጥ መሰብሰብ ላይ፣ የነዳጅና የሸቀጥ እንዲሁም የሲጋራና የማዕድን ኮንትሮባንድ ላይ እንዲሰማራ በመንግስት ባለስልጣናት ድጋፍ እየተደረገለት ነው። ከተራ ክላሽ ተነስቶ ታንክ ለመታጠቅ የግዢ ድርድር ላይ የሚገኘው የኦነግ ሰራዊት በወለጋና በሸዋ እንዲስፋፋ ሕዝብን እንዲፈጅ የመንግስት ባለስልጣናትና የኦሮሚያ ክልል አመራሮች እገዛ ቀጥሏል። ሕወሃት የልብ ልብ ተሰምቷት ወረራ የምትፈጽመው እኮ በብልጽግና ስሕተት መሆኑን ልናውቅ ግድ ይላል። ከትግራይ እስከ ሞያሌ ከጋምቤላ እስከ ደዋሌ በሃገሪቱ ግድያ መፈናቀል ስደት ረሃብ ችግር ወዘተ መንስኤው በኢሕአዴግ (ብልጽግና እና ሕወሓት ) ውስጥ ያለው የስልጣን ሽኩቻ እንጂ የፖሊሲ ወይም የለውጥ ጥያቄ አይደለም፣ የነገ የሃገር ስጋት እና የህዝብ ጠላት ማነው ? ብትለኝ በስልጣን ላይ ሆኖ ግዴታውን ካልተወጣው ከብልጽግና ውጪ የለም እልሃለሁ።
ስጋታችን ዛሬ ላይ ቆመን ለነገ ነው። ሐገርን የሚያስተዳድረው ገዢ ፓርቲ ነኝ የሚለው የኢሕአዴግ ቁራጭ ብልጽግና በአንድ በኩል፤ ሌላኛው ቁራጭ ሕወሓት በሌላ በኩል ሃገሪቱዋን እሳት ላይ ጥደው ያማስላሉ። ካድሬዎቻቸው የሰላምና የአንድነት ሃይሉን ወንጀለኛ አድርገው ቤንዚን ያርከፈክፋሉ። የሃገሪቱ የነገ ስጋትና የህዝብ ጠላት ግን በዋነኛነት ኢሕአዴግ እና ያልተቀየረው ፖሊሲው ነው። ባለፉት አራት አመታት ለውጥ ተባለ እንጂ የ 27 አመታት ውርሶችን ከማስቀጠል ውጪ ምንም አይነት ሃገሪቱን የሚበጅ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ለውጦች ይሁኑ ፖሊሲዎች አልታዩም፤ የሉም። ምንም አይነት ፕሮጀክቶችም ይሁኑ አዳዲስ ሃሳቦች የሉም። ትላንት ቃል የተገባው ዛሬ ይረሳል፤ ነገ አዲስ ነገር ይፈለጋል እያለ ይቀጥላል።
በመንግስት ሚዲያዎች ቀርበው የሚያወሩትና በመሬት ላይ የሚሰሩት የተለያየ የሆነው የብልጽግና አመራሮች በየመንገዱ አጀንዳ በማንጠባጠብ በህዝብ መሃል ችግር እንዲፈጠር የብሄርና የሃይማኖት ንትርክ ከዛም አልፎ ብጥብጥና ሁከት እንዲነሳ ተግተው ይሰራሉ፣ ሲነቃባቸው ምንም ግንኙነት ያሌላቸውን ሰዎችን ይወነጅላሉ፤ ያስራሉ፤ ያንገላታሉ፤ ሰላማዊ ሰዎችን ይገላሉ። ከሚያወሩትና ቃል ከሚገቡት አንድ ነገር አይፈጽሙም። ይህ ደግሞ ለፖለቲካውም ለኢኮኖሚውም ውድቀት አስታውፆ አድርጓል። ከእያንዳንዱ ስራቸውና ወሬያቸው ተነስተህ የነገ የሃገር ስጋት እና የህዝብ ጠላት ማነው ? ብትለኝ በስልጣን ላይ ሆኖ ግዴታውን ካልተወጣው ከብልጽግና ውጪ የለም እልሃለሁ።
ሌቦችንና የማህበራዊ ሚዲያ ሰራዊቶችን በማሰማራት ሃገርን ይዘርፋሉ፤ ህዝብን ያወናብዳሉ፤ በኑሮ የደቀቀውን ሕዝብ ይዘልፋሉ። ይህ የብልጽግና ሰዎች ሌላኛው አደገኛ መንገዳቸው ነው። የሃገር ሃብትን በዘረጉት ኔትወርክ በመዝረፍ ወደ ውጪ ያሸሻሉ። የተለያዩ መንገዶች በመጠቀም ሕንፃዎችን በመገንባት፣ ድርጅት በመክፈት፣ ቅርሶችንና ማእድናትን በመሸጥ፣ ካለቀረጥ በርካታ እቃዎችን በማስገባት በሃገር ላይ የኢኮኖሚ ክሕደት በመፈጸም ባለስልጣናትና ዘመዶቻቸው እየከበሩ ነው። የነገ የሃገር ስጋት እና የህዝብ ጠላት ማነው ? ብትለኝ በስልጣን ላይ ሆኖ ግዴታውን ካልተወጣው ከብልጽግና ውጪ የለም እልሃለሁ።
ብዙ ብዙ መዘርዘር ይቻላል። ችግሮችን በሕወሓት ለማሳበብ ወደ ተቃዋሚዎች ለመጠቆም ከመሞከር ይልቅ በስራ ሁሉንም ማኮላሸት እየተቻለ በፖለቲካ ማጭበርበርና በአለመተማመን መንፈስ መዘፈቅ አደጋው ለሁሉም ነው። ከፓርቲ እስከ መንግስት ሳቦታጅ ድረስ በፖለቲካ በኢኮኖሚ በማሕበራዊ መስክ ሃገርን እየገደሉ የሚገኙ የብልጽግና ባለስልጣናት የነገ የሃገር ስጋት እና የህዝብ ጠላት ናቸው ። ይህንን ለማረጋገጥ ደግሞ ሩቅ ሳትሄድ ዙሪያህን መመልከት ምላስና ተግባርን መመዘን በቂ ነው።