>

በገጠመኞች የታጀበ የህይወት ጉዞ ....!!! (ስምኦን ሩፋኤል)

በገጠመኞች የታጀበ የህይወት ጉዞ ….!!!

ስምኦን ሩፋኤል

ፀሀፊው ገና በ19 አመታቸው ነው ለኢትዮጵያ አየር ሀይል ጄት አብራሪነት የበቁት። በ1954 ዓ.ም የ12 ተኛ ክፍል የማትሪክ ፈተና ከተፈተኑት 1500 ተማሪዎች መካከል ካለፉት 50 ከማይሞሉ ተማሪዎች መካከል አንድርያስ እሸቴ፣ ብርሃነ-መስቀል ረዳ እና እሳቸው ይገኙበታል። በደርግ ውስጥ ቁልፍ ከሚባሉ አባላት መካከል ዋነኛው ናቸው።
ወህኒ ቤት የነበሩት ከፍተኛ የደርግ ባለስልጣናት ከ 20 አመታት በኋላ በምህረት በነፃ ሲለቀቁ ምህረት ለመንግስት ጥያቄ ቢያቀርቡም 20 አመታት ከነበሩበት ከጣሊያን ኤምባሲ ወደ ወህኒ ቤት መውረድ አለብዎ በመባላቸው ለተጨማሪ 10 አመታት ከጓዳቸው ሌ/ኮ ብርሃኑ ባይህ ጋር በመሆን በኤምባሲው ውስጥ “በእንግድነት” ተቀምጠዋል (በስደተኝነት ወይም በጥገኝነት ሳይሆን በእንግድነት)። በ 30 አመታት በኤምባሲ በነበረ ቆይታቸው እዛው የፃፉትን የህይወት ዳናቸውን በ 3 ክፍሎችና በ  50 ምእራፎች ከፍለው በማያሰልች መልኩ ለንባብ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት በኮሪያና በኮንጎ ካካሄደው ግዳጅ በተጨማሪ በወቅቱ ወደር የለሽ የነበረው የኢትዮጵያ አየር ሀይል ፓርቹጋልን በመጋፈጥ በታንዛኒያ ያደረገው የ 6 ወራት ስምሪት ለመጀመሪያ ጊዜ በዝርዝር ተዳሷል።
 የ ‘ያ ትውልድ’ ፀሀፊዎች በሚፅፋቸው መፅሀፎች ራሳቸውን ንፁህ የማድረግና ሌላው ላይ የማላከክ የተለመደ አባዜያቸው በፀሀፊውም ተንፀባርቋል። ኢህአፓን አብዮቱ ብላሽ እንዲሆን በማድረግ  የአብዮቱ ታሪክ ፍፁም ያልተጠበቀ መልክ እንዲይዝ ያደረገ የቀይ ሽብር ጠንሳሽ በማድረግ ሲወነጅሉት ፊዲስቶቹ (መኢሶናውያን) ደርግን ታኮ በማድረግ ለስልጣን ጥማታቸው ደርግን ለእልቂት የገፋፉ የሞት ደጋሾች አድርገዋቸዋል። ነጭ ሽብር የህዝብ ድርጅት ፅህፈት ቤትን ጠቅጥቀው የያዙት ፊዲስቶች ደርግን ቆስቁሰው ካለሀሳቡ ለአላማቸው ማስፈፀሚያ ያደረጉበት እርምጃ ነው በማለት ደርግን እንደጲላጦስ ከደሙ ንፁህ ነው ለማለት ቃጥቷቸው መኢሶን ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል።
ደርግ ስለቀይሽብር እንቅስቅሴ በተለይ በአጀንዳ ቀርቦ አንድም ጊዜ ውሳኔ ስላለመሰጠቱ አምርረው በመግለፅ ኢህአፓ በከተሞች የግድያ ሽብር ባይጀምር ኑሮ የአብዮቱ ታሪክ ከዚህ የተለየ ይሆን ነበር በማለት ለቀይ ሽብር ዋነኛ ተጠያቂ ኢህአፓ እንደሆነ በጉልህ አስምረዋል።
መንጌን በብዙ ቦታ ላይ በአዎንታዊ መልኩ ያነሷቸው ቢሆንም አመራሩ በጠቅላላ በተለይም የፕ/ት መንግስቱ ግትርነትና “እኛ እናውቅልሃለን” የሚለው አስተሳሰባቸው ለሀገሪቱም ሆነ ለደርግ መንኮታኮት ዋነኛ መንስኤ እንደሆነ ጠቁመዋል። በተለይም የኤርትራን ችግር ከመፍታት አኳያ ፕ/ት መንግስቱ ከፓለቲካዊ ይልቅ ለወታደራዊ መፍትሄ ማድላታቸውና ለሰላማዊ ድርድር ዝግጁ አለመሆናቸው ትልቅ ዋጋ ማስከፈሉን ሞግተዋል።
ክፍል ሶስት የመፅሀፉ አስኳል ነው። ፀሀፊው ከደርግ ውድቀት በኋላ ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር ለ 30 ዓመታት አዲስ አበባ በሚገኘው ጣሊያን ኤምባሲ ያሳለፉትን ልብ የሚነካ “የእንግድነት” ታሪካቸውን ተርከውበታል። የጂኔራል ተስፍዬ ገ/ኪዳን አስገራሚና አሳዛኝ አሟሟት በዝርዝር ገልፀውታል። በኤምባሲው ለሚገኙ የደርግ ባለስልጣናት ምህረት አላደርግም ብለው  27 አመት ሲፎክሩ የነበሩት መለስ ዜናዊ በህመማቸው የመጨረሻ ወቅት በፓትሪያርኩ አቡነ ጳውሎስ የቀረበላቸውን የእነ ሌ/ጄ አዲስ ተድላን በምህረት እንፈታ ማመልከቻ በመቀበል ለሚመለከተው አካል ቢመሩትም ሁለቱም በተከታታይ በሞት በመለየታቸው ፍቺያቸው በእንጥልጥል ቀርቷል።
ከጠሚው እልፈት በኋላ ባለስልጣናቱ እንዲፈቱ የተጠየቁት ዶ/ር ደብረ ፂዮን ከኤምባሲው ከወጡ በኋላ “እነሱ ምን ያህል በእስር ቤት ለመቆየት ዝግጁ ናቸው? በዚህ ላይ እንደራደር” ብለው በተለመደው የወያኔ ልማዳቸው ማላጋጣቸውንና መለስ ዜናዊ የፈቀዱት የፍቺያቸው ጉዳይ በደፂ መልስ እንደተከረቸመ ገልፀዋል። አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ የእኛን ጉዳይ ለመመልከት ወቅቱም ሁኔታውም የሚፈቅድለት አልነበረም በማለት የገለፁት ፀሀፊው የህውሃት ፀሀይ ጠልቃ አዲስ ጮራ ሲወጣ በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር አርትሮ ለዊዚ ከዶ/ር ጌዲዎን ጢሞቴዎስ ጋር ባደረጉት ያላሰለሰ ውይይት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በፌስቡክና በተለያዩ ሚዲያዎች ባደረላቸው የይፈቱ ድጋፍ እና በዶ/ር አብይ አህመድ ቅንነት ታህሳስ 26/2013 ከኤምባሲው በመውጣት ነፃነትን መጎናፀፋቸውን አትተዋል።
በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ውሳኔ  ከኤምባሲው ከወጡ በኋላ እስከ 3 ቀናት ድረስ በወህኒ ቤት እንዲቆዩ የሚያስገድድ የህግ ምክንያት ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን ፀሀፊው በዚህ ተስማምተው ፍቃደኛ ቢሆኑም ጓዳቸው ሌ/ኮ ብርሃኑ ባይህ ለአንድ ደቂቃ ቢሆን ወህኒ ቤት አልወርድም ብለው ወይ ፍንክች በማለታቸው መጠነኛ ችግር መፈጠሩን በመግለፅ መፅሀፋቸውን ደምደመዋል።
ፀሀፊ: ሌ/ጄ አዲስ ተድላ
የገፅ ብዛት: 686
የመፅሀፉ አይነት: ግለ ታሪክ
Attachments area
Filed in: Amharic