>
5:13 pm - Sunday April 18, 0088

የከሸፈውን የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ምስረታ ህዝብ እንዲቃወም የቀረበ ጥሪ (ባልደራስ) 

የከሸፈውን የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ምስረታ ህዝብ እንዲቃወም የቀረበ ጥሪ
ባልደራስ 

አገራችን እየደረሱባት ላሉት ዘርፈ ብዙ ችግሮች እና ጦርነት ዋነኛ ምክንያቶች ህገ-መንግሥቱ፣ ህወሓት እና ብልጽግና ፓርቲ እንደየደረጃቸው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከገባንበት ጦርነት እና ምስቅልቅል ችግሮች ለመውጣት እንድንችል ብሔራዊ ምክክር አስፈላጊ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ስለሆነም፣ ሀገሪቱ በታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም ሂደት ላይ ትገኛለች፡፡
ምክክር ኮሚሽኑ ስኬታማ አገራዊ ሰላም እንዲያመጣ እና የአገር አንድነታችንን ለማስጠበቅ እንዲያግዝ ሂደቱ ቢቻል በገለልተኛ አካል እንዲመራ፣ ካልሆነም ደግሞ፣ የሚመለከታቸው ዋና ዋና አካላት በሙሉ ተሳትፈውበት አካታች በሆነ መልኩ እንዲመራ  ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ ባልደራስ መጠየቁ ይታወሳል፡፡
እንደሚታወቀው፣ ችግርን የፈጠረ አካል የመፍትሄው አካል ሊሆን ቢችልም፣ የሂደቱ ዋና መሪ ሊሆን ግን በፍፁም አይገባም፡፡ ሆኖም ግን፣ ብልጽግና ፓርቲ (መንግሥት) ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ዋና ዋና አካሎች፣ ማለትም የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪክ ተቋማትን እና የሃይማኖት ተቋማት አግልሎ ሂደቱን ብቻውን በማን አለብኝነት  ሲያስኬድ ቆይቷል፡፡ ባካሄደው ሂደትም እጩ ኮሚሽነሮችን ለማንም ዜጋ ግልጽ የሆኑ የመምረጫ መስፈርቶች ሳያስቀምጥ ለራሱ በሚመቸው መንገድ፣ በመጀመሪያ ከ632 እጬዎች 43ቱን ለይቶ በማውጣት፣ ቀጥሎም ከ43ቱ 11 እጩዎችን አውጥቶ በማውጣት በዛሬው እለት በተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸውን አፀድቋል፡፡ ይህ ሁኔታም አገራችንን ለተጨማሪ ውስብስብ ችግሮች የሚዳርጋት እንደሆነ እሙን ነው፡፡
ለመላው የአገራችን ሕዝብ ግልጽ መሆን የሚገባው ብልጽግና (መንግሥት) ይህንን ታሪካዊ የሠላም እና የአገራችን የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ በእጅጉ ይጠቅማል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን የምክክር ኮሚሽን የምስረታ ሂደት አሳታፊ ባለማድረግ፣ ኮሚሽኑ ገና ሳይመሰረት እንዲመክን ማድረጉ ነው፡፡
ስለሆነም፣ መላው የአገራችን ዜጎች ይህንን የብልጽግና (መንግሥት) በሴራ የተሞላ መንገድ በመቃወም የተበላሸውን የምስረታ ሂደት ከጎናችን በመሆን እንድትቃወሙ ታሪካዊ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ 
                                   የካቲት 14/2014 ዓ.ም
                                           አዲስ አበባ
Filed in: Amharic