ለማን አቤት ይበል?!
(በአገራቸው ምድር ላይ ፍትህና ርትዕ ተነፍገው ለሚሰቃዩ
የአገሬ ሰዎች በሙሉ)
በዚያ መልካም ዘመን – ግብረገብ ሳይተን፣
ጎበዝ ያገሬ ሰው – በእምነት የታነጸው፣
ሙስሊም፣ ክርስቲያኑ.. – የዋሁ ምስኪኑ፣
ጥቃት ሲደርስበት – ፍትህ ሲጎድልበት፣
በህግ አምላክ ካለ – በሰንደቅ ከማለ፣
አጥፊም ይታቀባል፤ – ጠላትም ይቆማል፤
••••••••••••
ዛሬ ክፉ ጊዜ – የዘመን አባዜ፣
ሰንደቁ ተረግጦ – ፍትህ ‘ድሜ’ ግጦ፣
ማተብ ተበጥሶ – እምነት ተቀንጥሶ፣
ርህራሄ ተኖ – እርኩሰቱ ገኖ፣
ጠባቂ ነኝ ባዩ – መንግስት አስገዳዩ..፣
ሆኖ ሲገኝ ከቶ – በአገር መላ ጠፍቶ፣
በተፈጠረባት በዚህች በምድሪቱ፣
ለማን አቤት ይበል? ዜጋ ለህይወቱ!
ጌታቸው አበራ
የካቲት 2014 ዓ/ም
(ፌብሯሪ 2022)