>

ብልፅግና አቶ ፀጋዬ አራጌ በሌሉበት አስተዳደራዊ ውሳኔ ሊወስንባቸው ተሰብስቧል...!!! (መላኩ ረታ)

ብልፅግና አቶ ፀጋዬ አራጌ በሌሉበት አስተዳደራዊ ውሳኔ ሊወስንባቸው ተሰብስቧል…!!!
መላኩ ረታ

*…. አቶ ፀጋ አራጌ ብልፅግና ፓርቲያቸዉን በህግም፣ በሞራልም ይሁን በአሰራር በግልፅ ማሸነፋቸዉን ችግሩን እንዲፈቱ ቅሬታ ከቀረበባቸዉ ተቋማት ይፋዉና ህጋዊ መልስ ባያገኙም ራሱ ብልፅግና ፓርቲ ሳይወድ ተገዶ ራሱን አጋልጦና አዋርዶ በዝምታና በመደበቅ የሂደቱን ስህተት ማስተካከል መጀመሩ ተቋማዊ ዉርደት የገጠመዉ መሆኑን ሌላ ማስረጃ አያስፈልግም፡፡
አቶ ፀጋ አራጌ ጥር 29/05/2014 ዓ.ም ለፓርቲዉ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን ባቀረቡት ክስ ፓርቲዉ በህገወጥ መንገድ የፓርቲዉን መተዳደሪያ ደንብ ባላከበረ መንገድ ጉባኤ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ ስለሆነ ሂደቱን አቋርጦ በደንቡ መሰረት እንዲጓዝ መክሰሳቸዉ ይታወቃል፡፡
ከክሶቹ ጭብጦችም አንዱና ዋንኛዉ ማአከላዊ ኮሚቴ ተሰብስቦ አዘጋጅ ኮሚቴ ባላቋቋመበት፣ ለጉባኤ የሚቀርብ የሪፖርት ሰነድ አዘጋጅቶ ባልተወያየበት፣ የጉባኤ ተሳታፊወች ስብጥርና መጠንን የሚወስን መመሪያ ባላወጣበት፣ ለኮንፈረንስ መወያያ የሚቀርብ ሰነድን ባላፀደቀበት፣ በረቂቅ መተዳደሪያ ደንብና ፕሮግራም ላይ ተወያይቶ ማሻሻያ ሀሳብ አዘጋጅቶ ባላቀረበበት ሁኔታ በአቋራጭና በቆረጣ የሚካሄድ የጉባኤ የቅድመ ዝግጅት ሂደት እንዲቆም በማለት ነበር፡፡ የኢንስቴክሽንና ቁጥጥር ኮሚሽኑ ይህንን ዝግጅት የማያስቆም ከሆነ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እንደሚከሱ ገልፀዉም ነበር፡፡
ከኮሚሽኑ መልስ ባለማግኘታቸዉም የካቲት 2/06/2014 ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንኑ ክስ አቅርበዉ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸዉንና ምርጫ ቦርድ ምንም መልስ አልሰጠኝም በማለት ከቀናት በፊት በማህበራዊ ትስስር ገፃቸዉ “አቤት ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ” በማለት  ቅሬታቸዉን ገልፀዉ ነበር፡፡ ከኮሚሽኑም ይሁን ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋዊ የሆነ መልስ ያላገኙት አቶ ፀጋ አራጌ ዛሬ ግን በይፋ ብልፅግናን ማሸነፋቸዉን የሚያረጋግጥ ዜና ተሰምቷል፡፡
ከፓርቲዉ ስራ አስፈፃሚም ይሁን ከማአከላዊ ኮሚቴዉ እዉቅና ዉጭ የመንግስትን የስራ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ለሁለት ሳምንታት ሲካሄድ የነበረዉ የጉባኤ ዝግጅትና የአባላት ኮንፈረንስ  ለአንድ ሳምንት ያህል በዝምታ ቆሞ ከቆየ በኋላ ዛሬ የካቲት 16/06/ 2014 የብልፅግና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጉባኤ ዝግጅት ላይ ተሰብስቦ መነጋገር ጀምሯል፡፡ ከየካቲት 18/06/2014  ጀምሮ ደግሞ የብልፅግና ማአከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ መጥራቱ ተረጋግጧል፡፡
የኢንስቴክሽንና የቁጥጥር ኮሚሽንም ይሁን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አቶ ፀጋ ላቀረቡት ክስ ይፋዊ የሆነ መልስ በተቋም ደረጃ መስጠት ቢሳናቸዉም ቀርቦ የነበረዉ ክስ እዉነትነት ያለዉና ተጨባጭነት ያለዉ ከመሆኑም በላይ የብልፅግና ፓርቲን የህግ ጥሰትና አጉራ ዘለልነት በግልፅ የሚያጋልጥ በመሆኑ ምክንያት በቆረጣ የካቲት 25/2014 ሊያደርግ የነበረዉን “ጠቅላላ ጉባኤ” ህጉን ጠብቆ በመሄድ በመጋቢት ወር ለማካሄድ መወሰኑን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
አቶ ፀጋ አራጌ ብልፅግና ፓርቲያቸዉን በህግም፣ በሞራልም ይሁን በአሰራር በግልፅ ማሸነፋቸዉን ችግሩን እንዲፈቱ ቅሬታ ከቀረበባቸዉ ተቋማት ይፋዉና ህጋዊ መልስ ባያገኙም ራሱ ብልፅግና ፓርቲ ሳይወድ ተገዶ ራሱን አጋልጦና አዋርዶ በዝምታና በመደበቅ የሂደቱን ስህተት ማስተካከል መጀመሩ ተቋማዊ ዉርደት የገጠመዉ መሆኑን ሌላ ማስረጃ አያስፈልግም፡፡
በተጠራዉ የማአከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ  አቶ ፀጋ አራጌ እስካሁን ጥሪ እንዳልደረሳቸዉና በስብሰባዉ ሊሳተፉ እንደማይችሉ ግን ተረጋግጧል፡፡ ለምን አልተጠሩም? ምክኒያቱስ ምን ሊሆን ይችላል? የሚለዉን የሚያዉቀዉ እራሱ ብልፅግና ብቻ ነዉ፡፡
Filed in: Amharic