>
5:13 pm - Sunday April 19, 5767

"በህይወት “አለን” የሚሉትንና የ “ተበደልኩ” ሙሾ የሚያወርዱትን ኩርማናውያን ምኒልክ ሞቶም በጸጥታው ይበልጣቸዋል...!!! (ታደለ ጥበቡ)

“በህይወት “አለን” የሚሉትንና የ “ተበደልኩ” ሙሾ የሚያወርዱትን ኩርማናውያን ምኒልክ ሞቶም በጸጥታው ይበልጣቸዋል…!!!

ታደለ ጥበቡ

 

*…. አድዋን ያለ ምኒልክ መዘከር ክርስትናን አለክርስቶስ እንደማሰብ ነው!
  *….  አድዋን ያለ ምኒልክ ማሳብ ዘጸአትን ያለ ሙሴ እንደ ማሰብ ነው! 
*….  አድዋን ያለ ምኒልክ ማሰብ የድሉን አንገት መቁረጥ ነው!
ንጉሰ ነገስት ምኒልክን ዛሬም ከክፍለ ዘመን በኋላ፣ ከኢትዮጵያዊነት ማማ ላይ  የወደቁት፣ ከኢትዮጵያዊነት መዓርግ የቀለሉትና ከሰፊው ራእዩ ያዘቀዘቁትና ያነሱት ጠባቦችና መንደረኞች፣ በህይወት ከሚንቀሳቀሰው ይልቅ እሱን  ይፈሩታል፤ አርፎም ይደነግጣሉ፡፡ በህይወት “አለን” የሚሉትንና የ “ተበደልኩ” ሙሾ የሚያወርዱትን ኩርማናውያን ምኒልክ ሞቶም በጸጥታው ይልቃቸዋል።
ከእነርሱ በቁም መሞት ይልቅ የምኒልክ አልፎም ህያው መሆን በእጅጉ ይመረጣል፡፡ በህይወት ሳለ የፈጸመው ገድልና አልፎ የተወልን ታሪክ፣ በየዘውጋቸው ለጠበቡት ስጋት፣ ለእኛ ለዳናው ተከታዮች  ግን ኩራት ነው፡፡
ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን የካዱትና እንቁ ታሪካቸውን የጣሉት ምኒልክን ያጎሳቁሉታል፡፡ ምክንያቱም፣ እነርሱ እጅ ካለ ሜንጫ፣  ጠብመንጃ፣ ገንዘብና ሚድያ ይልቅ፣ የምኒልክ መንፈስ፣ የምኒልክ ኢትዮጵያዊ ራእይ ተአምር እንደሚሰራ ያውቃሉ፡፡ ከስረ መሰረታቸው ተመንግለዋልና፤ ከደመቀ ታሪካቸው እራሳቸውን ነጥለዋልና፤ ስሙ ያስደነብራቸዋል፡፡ ሙያውም የቁም ቅዠታቸው ነው፡፡ በዘለፉት ቁጥር ይብስ እንደሚከበር፣ ባንኳሰሱት ቁጥር ይበልጥ እንደሚደምቅ አላወቁም፡፡ በሰደቡት ቁጥር እንደሚገን፣ ያዋረዱት ሲመስላቸው ይበልጥ እንደሚሰራፋ አይገነዘቡም፡፡
እኛ ምኒሊካውያን ግን ፈለጉን እንከተላለን፡፡ ዘመኑን በዋጀ መልኩ አገራችንን እናቀናለን፡፡ ስሙን ስንጠራ ደስ እያለን ነው፡፡ ጀብዱን ስንተርክ እንኮራለን እንጂ ከቶ አንሸማቀቅም፡፡ ሰንደቅዓላማውን  ስናነሳም በታላቅ የመንፈስና የሞራል ልእልና ነው፡፡
Filed in: Amharic