>

ሩሲያና ኢትዮጵያ...!!!  (ዘመድኩን በቀለ)

ሩሲያና ኢትዮጵያ…!!! 

ዘመድኩን በቀለ

“…በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክርቤትን ጨምሮ ሌሎችም ተጨማምረው ከ11 ጊዜ በላይ በኢትዮጵያ ጉዳይ አስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጧል። በዓረቡም፣ በአሜሪካና በአጠቃላይ በምዕራባውያኑ በተለያዩ ጊዜያት የተጠተጠራ አስቸኳይ ስብሰባም አድርገውብናል። በዓባይ ጉዳይ ለግብፅ፣ በሥልጣን ጉዳይ ለወያኔም አግዘው ነው ኢትዮጵያን ለመጫን ሲያዋክቡን የከረሙት። በብዙ አስጨንቀውናል። አዋክበውናል። አስፈራርተውናልም።
“…ታዲያ በዚያን ጊዜ ሁሉ ሩሲያ፣ ቻይናና ህንድ አቋማቸው ሳይዋዥቅ ከኢትዮጵያ ጎን ቆመዋል። ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመውም ውሳኔዎችን ሁሉ ቀልብሰዋል። ሩሲያ፣ ቻይናና ህንድ በምዕራባውያኑ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በወያኔና በወያኔ ካድሬዎች፣ በወያኔ የጡት ልጆች በወሄና በኦኔ ጭምር ሲጠሉ፣ ሲብጠለጠሉ፣ ሲሰደቡም ከርመዋል። አሁንም እንኳ ወያኔና ኦነግ ከዩክሬን በበለጠ የሩሲያ ጠላት ለመሆን ሲላላጡ ነው የሚታዩት። እነ ሩሲያ ግን በኒዮርክ ከአምባሳደራችን ከአጽቀሥላሴ ልጅ ከልጅ ታዬ ጎን ቆመው አጋርነታቸውን አሳይተውናል። እናመሰግናለን።
“…ሩሲያ በዓድዋ ጦርነት ጊዜም ከእኛው ጋር ነበር የተሰለፈችው። የዳግማዊ ምኒልክ ወታደራዊ አማካሪ ከነበሩት መካከልም ኒኮላይ ሊዮንቲየቭ አንደኛው ነበር። በዓድዋ ጦርነት ላይ የሩሲያ ኮሳክ በጎ ፈቃደኞችም ከእኛው ጋር ነበሩ። ሞታችንን የሞቱ በምትኩም ምንም ከእኛ ያልወሰዱ ናቸው። በበርሊኑ አፍሪካን የመቀራመት ጉባኤ ላይ ሩሲያ በስብሰባቸው ላይ ነበረች። ነገር ግን ይሄ ነውር ነው። ዘርፈህ ሳይሆን ሠርተህ ብላ ብላቸው ነው ስብሰባውን ጥላ የወጣችው። ሩሲያ በአፍሪካ አህጉር አንድም ሃገር ቅኝ አልገዛችም። ባሪያም አላደረገችም። አልዘረፈችምም። በጃንሆይም፣ በደርግም ጊዜ ከኢትዮጵያ ጋር ነበረች። በወንበዴው ህወሃት ዘመንም ዕዳችንን የሰረዘች ሃገር ናት። አሁንም እንደዚያው።
“…ኢትዮጵያችን የትኛውንም ወረራ አትደግፍም። የሩሲያን ስጋት ግን ትጋራለች። ይሄን የሩሲያን ስጋት አውሮጳውያኑም ያውቁታል። ላያደርጉ የፈረሙበት አጀንዳም ነበር። እናም ሩሲያ ሳትወድ በግዷ ወደ ጦርነት ገብታለች። ይሄን ዓለሙ ሁሉ እየመሰከረ ነው። ሩሲያ አሜሪካ በኢራቅ ላይ፣ በሶሪያ በሊቢያ ላይ ከፈጸመችው ውድመት ጋር በፍጹም የማይመሳሰል ነገር ግን ከመከበብ፣ ከስጋት ነፃ የመሆን መብቷን ነው የተጠቀመችው። ነገር ግን ከስፖርቱ ዓለም፣ ከገንዘብ ሥርዓቱ፣ ከንግድ ሥርዓቱ፣ በቃ ከዓለም ካርታ መሠረዝ ሲቀራቸው ከሁሉም ነገር ነው እያገዷት ያለው። ፍጥነቱ ትዝብት ላይ እየጣላቸውም ነው።
“…የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ሩሲያ አቅም እንደሌለው ሩሲያ አሳምራ ታውቃለች። ቻይናም እንኳ በጥበብ ከጎኗ መቆሟንም ትረዳለች። ከአፍሪካ ኡጋንዳ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ ሶሪያ፣ ኢራን፣ ቤላሩስ ብቻ ናቸው እስከአሁን ከሩሲያ ጎን ባይቆሙም እንኳ የሩሲያ የመከበብ ስጋት ገብቷቸው ትንሽ ግልጽ በሆነ መንገድ ሲደግፏት የታዩት። እንጂ ሌላው ዓለም የሩሲያን ችግርና ስጋት መጋራትም ማየትም ሲፈልግ አልታየም። መፍትሄው መደማመጥ ብቻ ነው።
“…የሆነው ሆኖ ዓለም ሁሉ ሩሲያ ላይ ፈርቶም፣ ሰግቶም ፊቱን ባዞረ ጊዜ ኢትዮጵያ ግን ኢትዮጵያውያን ልጆቿ በአፍሪካ መዲና፣ በአዲስ አበባ በእምዬ ምኒልክና በእቴጌ ጣይቱ ከተማ በዛሬው የዓድዋ የድል በዓል ዕለት በምኒልክ አደባባባይ ከሃውልቱ ፊት ለፊት የሩሲያን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ወጥተው በስሱም ቢሆን አጋርነታቸውን አሳይተዋል።
“…እዚህ በጦርነቱ ቅርብ ያለነው ሰዎች በአካባቢው ያለውን ስጋት እንረዳለን። ዩክሬናውያን ከምር ያሳዝናሉ። ከሃገር ለመውጣትም አይቻልም። ጦርነቱም ከባድ ነው። ውድመቱም ከባድ ነው። ሰቆቃውም ከባድ ነው። በቴሌቭዥን የሚታየው ሁሉ ይዘገንናል። ኑሮ በአውሮጳ ራሱ እየተወደደ ነው። እንደኛ በፆም እያሳበበ ቀኑን ከሚሸውደው በቀር 24 ሰዓት መብላት ለለመደ ሰው ጭንቅ ሆኗል። ነዳጅ እየተወደደ ነው። ሁሉ ነገር ደስስ አይልም። በአፍሪካም፣ በአውሮጳም፣ በዓረቢያም፣ በእስያም። በካናዳም፣ ብቻ በሁሉም ሥፍራ ስጋት ነው። ጨዋታው በኒዩልለር ነው ስለተባለም ፍርሃት ነግሧል። ቻይናም፣ ሰሜን ኮርያም ወደ ሽኩቻው ከገቡ ደግሞ ጨዋታው ይበልጥ አደገኛና ውስብስብም ይሆናል ተብሎ ተሰግቷል።
“…በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር የሆኑት ተረክሂን የዛሬውን የዓድዋ ድል በዓል በማስመልከትም ” በዓሉ የነጻነት ተምሳሌት እና ለአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች የአልገዛም ባይ መንፈስን ያወረሰ መሆኑ በመጥቀስ ለድሉ በዓል እንኳን አደረሳችሁም ብለዋል፡፡ በዓሉ የኢትዮጵያን ሃገርነት ያጸና እና በውስጥና በውጭ ፖሊሲዎቿ ጭምር አልበገር ባይነቷን ያሳየ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል፡፡ ድሉ የሁለቱን ሃገራት ግንኙነትንም በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲፀና መሰረት የጣለ መሆኑንም አምባሳደር ተረክሂን አመልክተዋል፡፡
“…ሰላም ለዓለሙ ሁሉ ይሁን !!
Filed in: Amharic