በአድዋ በዓል ሳቢያ 3 ሰዎች ተገደሉ….!!!
ባልደራስ
•በዓሉን ተከትሎ በደረሰባቸው ጥቃት የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጫካ ገቡ….!!!
የአድዋ በዓል ዋዜማ በሆነው የካቲት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ከጎንደር ባሕር ዳር፣ ደጀን አዲስ አበባ በአውቶብስ እየመጡ የነበሩ ሰዎች ላይ አሸባሪው ኦነግ-ሸኔ በከፈተው ተኩስ ሦስት ሰዎች ተገድለዋል። ቡድኑ ተኩሱን የከፈተው ተጓዦች ገብረ ጉራቻ ከተማ ሲደርሲ አውቶብሱን በማስቆም ነበር። የግድያው ምክንያትም “ወደ
አዲስ አበባ(ፊንፊኔ) የምትሄዱት የአድዋ በዓልን ለማክበር ነው፤ ይሄን ማድረግ አትችሉም” የሚል እንደነበር ከግድያ የተረፉ የዓይን እማኝ ገልፀዋል።
በተመሳሳይ ዜና፣ ትናንት የካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም በደቡብ ኢትዮጵያ፣ ሆሳዕና የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የአድዋ ድል በዓልን በማክበር ላይ እያሉ በአንዳንድ የፌዴራል ፖሊስ አባላትና ተማሪዎች ተደብድበዋል። ሦስት የአማራ ተማሪዎችም በሆሳዕና ከተማ ታስረው አድረው ተፈተዋል።
ከስፍራው ያነጋገርናቸው የመረጃ ምንጭ፣ በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ እየተሰማ መሆኑን ነግረውናል። የዳግማዊ ምኒልክና የነገስታቱ ምስል የታተሙባቸው አልባሳትን ለብሰው የተገኙ የአማራ ተማሪዎች እየተደበደቡ መሆኑንም አረጋግጠዋል። ይህንን ተከትሎ የአማራ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ግቢ እየወጡ ወደ ጫካ ገብተዋል።
ትናንት በዓሉን ሲያከብሩ ይዘውት የነበረው ነባሩ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማም ተነጥቀዋል።