>
5:28 pm - Friday October 9, 0685

የሕብረተሰባዊነት ኢትዮጵያ የጀግና ሜደይ/ወደር የሌለው ጀግንነ  ተሸላሚ ብ/ጀነራል ተስፋዬ ሀብተማርያም ....!!! (ቤንጁ ማን)

የሕብረተሰባዊነት ኢትዮጵያ የጀግና ሜደይ/ወደር የሌለው ጀግንነ  ተሸላሚ ብ/ጀነራል ተስፋዬ ሀብተማርያም ….!!!
ቤንጁ ማን

ሁለት ግዜ እስከ ጨበጣ ውጊያ ይደርሳሉ ፤ በነብስ ወከፍ መሳሪያ ሱማሌን ወደመጣችበት ይመልሳሉ። 8 ሠዓት ላይ ሁሉም ነገር በቁጥጥር ሥር ዋለ። አልፎ አልፎ የጠላት ከባድ መሳሪያ ተኩስ ከመስማት በስተቀር የቀላል መሣሪያ ተኩስ ቆመ። እኔም ከምሽጌ ወጥቼ አካባቢውን እየቃኘሁ << የሻለቃ አዛዦች ውጊያው አለቀ ብለው እንዳይዘናጉ ፤ ቁስለኞች ባስቸኳይ ተነስተው ወደ ሆስፒታል እንዲላኩ ፤ የተሰዉ ጓዶች የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው ማታ እንዲፈፀም ፤ አካባቢያቸውን አጥብቀው እንዲጠብቁ>> እያልኩ ትዕዛዝ ሳስተላልፍ በግምት 5 ሜትር ላይ የመድፍ ሼል(ጥይት) ፈነዳ።
ቲ.ኤን.ቲ በተባለ ፈንጂ ቅመም የተሞላው ፈንጂ ፤ ሽፋኑ በመቶ የሚቆጠሩ ቁርጥራጮች በሁለቱም በኩል መቁረጥ የሚችል መጋዞች አሉት። ጫፋቸውም በሙቀት የተሞሉና ወደ ጎን ከ50-100 ሜትር እርቀት ይወረወራሉ ፤ በሙቀታቸው ያቃጥላሉ ፣ በስለታቸው ይቆርጣሉ ፣ በሹል ጫፋቸው ሰውነት ላይ ጉዳት ያደርሳሉ። በፍንዳታው የሚፈጠረው ድምፅ የመብረቅ ይመስላል ፤ መሬቱ ይንቀጠቀጣል ፤ በቅርብ እርቀት ድንጋይም ቢሆን ያከስላል። ዛፍ ይቆርጣል ፣ ይሰነጥቃል ፣ ይሰባብራል።
ይሄ መድፍ አጠገቤ ሲያርፍ እኔን ብድግ አድርጎ ዓየር ላይ ጭንቅላቴ ወደ ታች እግሮቼን ወደ ላይ ምሽግ ውስጥ ወረወረኝ። ምሽጉም ተደርምሶ ቀባሪና አፈር አልባሽ ሳያስፈልገኝ እላዬ ላይ ተደረመሰና አፈር አለበሰኝ።
ከዚህ ቀጥሎ የሆነውን እኔ እራሴን ስቼ ስለነበር አላውቅም።በሁዋላ ላይ ነፍስ ስዘራ ሲነግሩኝ << ሞተሀል ብለን ተስፋ ቆርጠን ትተንህ ውጊያችንን ቀጠልን። መሞትህንም ለምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥና በተዋረድ ለም/ጦርና ለመከላከያ መምሪያ ሪፖርት አደርግን። እያለ የዕዝ ጠገጉን ተከትሎ ለሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማርያም ሪፖርት ተደረገ>> አሉኝና በግምት በመቀጠልም << በግምት ከሁለት ከሶስት ሠዓት በኋላ ጦርነቱ በረድ ሲልና ግዜ/ፋታ ስናገኝ ቤተሰብህ ቅሪት አፅምህን ወስደው ለመቅበር ቢፈልጉ በቀላሉ ማግኘት በሚችሉበት ታዋቂና ቋሚ ምልክቶች ያሉበት ቦታ መርጠን ፣ ጉድጓድ ቆፍረን አዘጋጀን። ከተቀበርክበት ምሽግ ቆፍረን አውጥተን ለመቅበሪያ ወደ ተዘጋጀው ጉድጓድ ይዘንህ ስንሄድ ፣ አንድ ሰው << ሰውነቱ ሙቀትና ትንሽ ትንሽ ትንፋሽም አለው>> አለ። መተንፈስህን ስናይ ትተርፋለህ ብለን ሳይሆን ሆስፒታል ደርሰህ ሙት ብለን በአስቸኳይ ወደ ሀረር 3ኛ ክ/ጦር ሆስፒታል እንድትወሰድ አደርግን >> ብለው አጫወቱኝ።
ይህን የሚሉን በሰራዊቱ ውስጥ የመጨረሻ ከፍተኛ የሆነውን #የሕብረተሰባዊነት_ኢትዮጵያ_የጀግና_ሜደይ/ወደር_የሌለው_ጀግንነት/ ተሸላሚ የሆኑት ብ/ጀነራል ተስፋዬ ሀብተማርያም በ የጦር ሜዳ ውሎ በሚለው መፀሀፋቸው ነው።
የካራማራ ድል በዋዛ የተገኘ አይደለም  ጎበዝ የተሰዉትን እንዘክር እናስብ!!
Filed in: Amharic