>
5:26 pm - Monday September 15, 9287

" ፍሬ ያለው ዛፍ ወርዋሪ ይበዛበታል " ...!!! (ሞገስ መኮንን)

ፍሬ ያለው ዛፍ ወርዋሪ ይበዛበታል ” …!!!

ሞገስ መኮንን

ስራ መስራትና መተቸት ይለያያሉ። ተፅዕኖ መፍጠርና በተፅዕኖ ስር መውድቅም ለየቅል ናቸው። መሪ መሆንና መንጋ ሁኖ መከተልም አይገናኙም። ወደምድር የመጣህበትን አውቀህ፣ ለመክሊትህ እውን መሆን መስዋዕትነት መክፈልና እንዲሁ ተራ (Just a number) ሆነህ ማለፍም አራምባና ቆቦ ናቸው።
እስቲ ልጠይቅህ፦ በህይወት ዘመንህ ምን ሰራህ?፤ መቼም መልስህ “ተምሬ ዩነቨርስቲ ገብቼ፣ በማዕረግ ተመርቄ፣ ተቀጥሬ እየሰራሁ ነው። መኪናና ቤትም አለኝ። ” ይሆናል። purpose of life ግን እንደዛ ነው?  የራስህን ምቾት ችላ ብለህ ለሌሎች ዋጋ የከፈልክበትን ጊዜ ታስታውሳለህ? “እንደ ሻማ ቀልጠህ ለሌሎች ብርህን የፈነጠክበት” ወቅት ትዝ ይለሃል?፤ ዓለማውን ለማሳካት የሚታትርን ሰው ደግፈኸዋል፣ ወይስ ገፍተህ ትጥለዋለህ? (መልሱን ለራስህ ያዘው)
—-
እኔ የምልህ፦ የራስህ መርህ ሳይኖርህ አቋም ያለውን ሰው ግን እስከመቼ ነቅፈህ ትዘልቀዋለህ?፤ የውስጥህን ጩኸት፣ ከልክ ያለፈው ፍርሃት፣ የማያስተኛ ጭንቀትና ሽንፈትህን ለምን ብርቱ ሰው ላይ በመዘባበት ለመሸፋፈን ትባዝናለህ?  እርግጥ ነው ከሰው foul አይጠፋም። የፈለገ ቢሆን ግን ከቅንጣት ስህተት ግዙፍ እውነት ይበልጣል።
አንዳንዴ መናገር እየፈለክ ዝም ትላለህ። ሲበዛ ግን “ሽራፊ መልዕክት” ማስተላለፉ አይከፋም። በተለይ በተለይ ለራሳቸው ህይወት ቁብ ሳይሰጡ ለእውነትና ለፍትሕ ሲሉ ዋጋ የከፈሉ ሰዎች በህቡዕና በሀላል አላግባብ ሲነቀፉ ስታይ ዝም ማለት የአራዳ ፀባይ አይደለም። እናልህ ለአቋማቸው የሚሞቱ ሰዎች ይመቹኛል። ላመኑበት ነፍሳቸውን ለመስጠት የማያንገራግሩት ልቤን ይገዙታል።
ባለፈው የምወደውና የማደንቀው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን “መንግስትን ለምን ይተቻል?” ብሎ ያ! አዛውንት ነው ‘መልካም ወጣት’ በሚል የሚንቀሳቀሰው ግለሰብ፣ ብርቱውን ሰው ለመተቸት ሲሞክር፣ ፅሁፉን share እያደረክ አንተም ጋዜጠኛውን ፀያፍ ለማድረግ ስትዋትት አይቼ ብግን ብያለሁ። እውነት የተመስገንን ሀሳብ ታቅርነህ ነው? ወይስ መንጋ ስለሆንክ?
ያንተ አላዋቂነትና ድንቁርና እኮ ለቴዲ አፍሮም አልተመለሰም። ጭራሽ በትምህርት ደረጃው ሙድ ልትይዝበት ሞከርክ። በእርግጥ እነዚህን አይበገሬ ሰዎች ለመተቸት ሀሳባቸውን ማወቅ ሳይሆን ደፋር መሆን በቂ ነው። ያው መሃይም ደፋር ነዋ።
እስክንድርንም የምትተችበት መንገድ ቆሽቴን ያሳርረዋል። ለምን እሱን ሳይሆን ሀሳቦቹን ነጥለህ አትደግፍም ወይ አትነቅፍም?! የእርድና ሀሁ’ን ስናጠና ሙድ የሚያዝበትና የማያዝበትን ነገር ጠንቀቅን ተምረናል። “ኩርቱ ፌስታሉን ይዞ፣ ታስሮ መግለጫ ላውጣ አለ….ወዘተ” የሚሉት ግን እውነት እልሃለሁ በአራዳ ህግ ያስጠይቁሃል።
ይህን የምፅፍልህ አዲስ አበባ ተወልዶ፣ እንዳደገና እንደሚኖር ሰው ነው (የግል አቋሜ ነው)። እስቲ ወደ ኃላ መለስ ብለህ ባልደራስ ስለአዲስ አበባና አዲስ አበቤ ጥብቅና ከመቆሙ በፊትና በኃላ ያሉትን ድርጊቶች ተመልከት።  ለውጥ የለም?! መታወቂያ በድብቅ ሲታደል ትዝ ይለሃል?፤ ልዩ ጥቅም የምትባለው ነገርስ?፤ የኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም ጉዳይን ረሳኸው?፤ ተወልደህ ባደክበት ቀበሌ ውስጥ ሌላው እየሰራ አንተ ስራ አጥ የሆንክውስ?፤ …..መዓት ሁነቶችን መዘርዘር ይቻላል። ስለምታውቀው አልደግመውም። look brother “እስክንድርን ለምን በጭፍን አትደግፈውም?” እያልኩህ አይደለም። በጭፍን ስትነቅፈው ግን ዝም አልልህም። እስቲ ሀሳቡን በሀሳብ አሸንፈው?
ሁልጊዜም የሚሰራ ሰው ይተቻል። የተግባር ሰው ይነቀፋል። ከግለሰብ እስከ ተቋም ያምፁባሃል። አንድ እውነት ግን አለ። “ፍሬ ያለው ዛፍ ወርዋሪ ይበዛበታል።” ፍሬውን ለማውረድና ለመብላት ድንጋይ የሚወረውረው እልፍ ነው። ግዙፍ ግብ ሲኖርህ በሚወረውሩት ድንጋይ ሊጥሉህ የሚሞክሩት ነፍ ናቸው።
[የዛሬ ሁለት April 26 2020 የተፃፈ 
Filed in: Amharic