ዘጋቢ፡-ዘመኑ ይርጋ-ከፍኖተ ሰላም
ፍኖተሰላም: የካቲት 30/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በማንነታቸው ምክንያት ከኦሮሚያ እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ በርካታ ወገኖች በፍኖተ ሰላም ከተማና በዙሪያ ወረዳዎች ይገኛሉ፡፡
እድሜ ዘመናቸውን ሃብት አፍርተው እና ልጅ ወልደው በኖሩበት ቀያቸው በማንነታቸው ብቻ በግፍ እየተጨፈጨፉ ሀብት ንብረታቸው ወድሞ ህይዎታቸውን ለማዳን በፍኖተ ሰላም ከተማና አካባቢው የተጠለሉት እነዚህ ወገኖች ከመጠለያ ጀምሮ በቂ የዕለት ደራሽ ምግብ ባለማግኘታቸው ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
መንግሥት ችግራቸውን አይቶ የመጠለያና የዕለት ደራሽ ምግብ ከማቅረብ ባሻገር በአጭር ጊዜ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።
ከኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው የመጡ 300 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች በዞኑ እንደሚገኙ የምዕራብ ጎጃም ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተዋቸው ዓለማየሁ ተናግረዋል።
አሁንም በአዲስ የሚፈናቀሉ ወገኖች መኖራቸውን የገለጹት ኀላፊው ዞኑ ከክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የሚቀርበውን በነፍስ ወከፍ 15 ኪሎ ስንዴ የዕለት ደራሽ ምግብ እያሠራጨ ቢሆንም ከተፈናቃዩ ቁጥር መብዛትና በክልልና ሀገር አቀፍ ደረጃ እጥረት በመኖሩ ሁሉንም ተደራሽ ማድረግ አልተቻለም ብለዋል።
ተፈናቃዮች ያነሱትን የመጠለያ ችግርም ለመፍታት ለክልሉ መንግሥት ጥያቄ መቅረቡን አንስተዋል፡፡
የተፈናቃዮችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ከኦሮሚያ እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ጋር በመምከር አሁን ላይ ሰላማዊ በሆኑ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖችን የማስፈር ተግባር በአጭር ጊዜ ለማከናወን እየተሠራ ነውም ብለዋል።
በአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት ከ11 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ወገኖች የዕለት ምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል ።