>

መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም ና የመተማው ጦርነት....!!! (ታሪክን ወደሗላ)

መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም ና የመተማው ጦርነት….!!!

ታሪክን ወደሗላ

በዛሬዋ ዕለት 
 
ከ 133 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን ለንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛ ሕይወት ማለፍ ምክንያት የሆነው የመተማ ጦርነት የተካሄደው ዕለት ነበር፡፡
ደርቡሾች (መሐዲስቶች) በዘኪ ቱማል እየተመሩ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በመግባት ብዙ ጥፋት አደረሱ፡፡ ከጣሊያኖች ጋር ውጊያ ላይ የነበሩት ንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛም ደርቡሾች በተለይም በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ላይ ያደረሱትን ጥፋት ለመበቀልና የአገራቸውን ድንበር ለማስከበር ‹‹መጣሁ ጠብቀኝ! እንደ ሌባ አዘናግቶ ወጋኝ እንዳትል›› የሚል መልዕክት ወደ ዘኪ ቱማል ላኩና ብዛት ያለውን ጦራቸውን ይዘው ወደ መተማ ዘመቱ፡፡
መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም በዕለተ ቅዳሜ ከረፋዱ በሦስት ሰዓት ላይ ጦርነቱ ተጀመረ፡፡ ንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛ ልክ እንደ ተራ ወታደር መሐል ገብተው ሲዋጉ ዋሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን በርትተው እየተዋጉና ምርኮ በመያዝ ላይ ሳሉ አንዲት ተባራሪ ጥይት የንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛ ደረት ላይ አረፈች፡፡ የንጉሰ ነገሥቱን መቁሰል ያየው ሰራዊታቸውም ተደናግጦ መሸሽ ጀመረ፡፡
በጽኑ ቆስለው የነበሩት ንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛም በማግሥቱ፣ መጋቢት 2 ቀን 1881 ዓ.ም አረፉ፡፡ ደርቡሾችም እየተከታተሉ የንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛን አስክሬን ይዘው አትባራ ወንዝ ዳር ሰፍረው የነበሩትን ኢትዮጵያውያን መኳንንትና ወታደሮች ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ መጋቢት 3 ቀን 1881 ዓ.ም የንጉሰ ነገሥቱን ጭንቅላት ቆርጠው ወሰዱት፡፡
አፄ ዮሐንስ በመተማ ጦርነት ከተሰው በኋላ በህዝቡ የተገጠመላቸው!
በጎንደር መተኮስ
በደንቢያ መታረድ
አዝኖ ዮሐንስ:
ደሙን አፈሰሰ እንደ ክርስቶስ።
እዳያምረው ብሎ ደኻ ወዳጁን
መተማ አፈሰሰው ዮሐንስ ጠጁን።
የጎንደር ሃይማኖት ቆማ ስታለቅስ
አንገቱን ሰጠላት ዳግማይ ዮሐንስ ።
ክብርና ሞገስ ለሀገራቸው ለተሰውት ንጉሥ ዩሐንስ ፬ኛ
Filed in: Amharic