>
10:13 am - Wednesday March 29, 2023

 የባልደራስ እና የአዲስ አበባ ወጣቶች በሙሉ ለ14 ቀን ታስረው እንዲቆዩ ተበየነ ...!!! (ባልደራስ)

 የባልደራስ እና የአዲስ አበባ ወጣቶች በሙሉ ለ14 ቀን ታስረው እንዲቆዩ ተበየነ …!!!
ባልደራስ

 

*…. በመርካቶ የ32 ቀበሌ ነዋሪዎች “ተጨማሪ ልጆቻችንን ለእስር አሳልፈን አንሰጥም” በማለት ፖሊስን ተቃወመ…!!!
 
 *…  በአባ ሳሙኤል እስር ቤት “በቂ ምግብ፣ በቂ ውሃ፣ በቂ መፀዳጃ ” እንደሌለ እስረኞች ተናገሩ …!!!
/
የባልደራስ እና የአዲስ አበባ ወጣቶች በተያዘላቸው ቀጠሮ መሠረት ዛሬ በአራዳ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ አስቀድመው የቀረቡት በናትናኤል የአለምዘውድ መዝገብ የተከሰሱት 11 ወጣቶች ሲሆኑ፣ ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች የታሰሩ ናቸው፡፡
 
# የፖሊስ ክርክር
ብይን ለመስጠት ቀጠሮ የያዘው ፍርድ ቤቱ፣ በባለፈው ቀጠሮ የተነሳውን የተከሳሽና እና የከሳሽ ክርክር በንባብ ያሰማ ሲሆን፣ ፖሊስ ባቀረበው ክስ፣ “ባለሥልጣናትን ልክስክስ፣ ከሃዲዎች፣ ከሥልጣን ውረዱ ብለው ተከሳሾቹ ሕዝብን ለአመጽ አነሳስተዋል፡፡ ሕገ ወጥ ባንዲራ ይዘዋል፣ ከፀጥታ አካላት ጋር ተጋጭተው ረብሻ ፈጥረዋል” ማለቱን አስታውሷል፡፡
 
# የተከሳሾች ጠበቆች ክርክር
የተከሳሾች ጠበቆች ደግሞ፣ “ ተከሳሾች የተያዙት በልደታ ክፍለ ከተማ ስለሆነ፣  የአራዳ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለመመልከት ሥልጣን የለውም፣ ባለሥልጣናት ከተሰደቡ የግል አቤቱታ ሳያቀርቡ ክስ ሊመሰረት አይችልም፣ በልደታ ፍርድ  ቤት የጊዜ ቀጠሮ ስለተሰጠ፣ አሁን ሌላ ሁለተኛ ቀጠሮ ሊሰጥ አይገባም” ማለታቸውን ፍርድ ቤቱ አስታውሷል፡፡
 
# የፍርድ ቤቱ ብይን 
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን መዝኜ ሰጠሁት ባለው ብይን፣ “ባለሥልጣናት  ሲሰደቡ ፖሊስ በደላቸውን ሊያጣራላቸው ይችላል፣ ተከሳሾቹ ቀደም ብለው የቀረቡት የከተማ ነክ ፍርድ ቤት ሲሆን፣ የከተማ ነክ ፍርድ ቤት ተከሳሾቹ የተጠረጠሩበትን ከባድ ወንጀሎች ለመመልከት ሥልጣን የሌለው በመሆኑ የጊዜ ቀጠሮ መስጠቱ ትክክል አልነበረም፡፡ ስለዚህም፣ ተከሳሾቹ በአንድ ጉዳይ ሁለቴ የጊዜ ቀጠሮ እንደተሰጣቸው ሊቆጠር አይችልም፡፡ እንዲሁም፣ የተከሰሱበትን አመጽ የማነሳሳት ከባድ ወንጀል የማየት ሥልጣን ያለው የፌደራል ፍርድ ቤት በመሆኑ ይህ ችሎት ጉዳዩን መመልከቱ አግባብ ነው” ብሏል፡፡
# ቀጣዩ ቀጠሮ
ፍርድ ቤቱ ከሰዓት በቀረቡት የእነ ወግደረስ ጤናው መዝገብ፣ የእነ ጌጥዬ ያለው መዝገብ፣ የእነ መአዛ ታደሰ መዝገብን አስመልክቶ በሰጠው ሀተታ እና ብይን ጠዋት ያነበበውን ቃል በቃል ደግሞታል፡፡ በዚህም መሠረት፣ ተከሳሾቹ ሁሉ የተጠረጠሩት በከባድ ወንጀል እንደሆነ በመግለጽ፣ የእነ ናትናኤልን ለመጋቢት 19/2014 ዓ.ም ሲቀጥር፣ ሌሎቹን ደግሞ ለመጋቢት 14/2014 ዓ.ም ቀጥሯቸዋል፡፡ ሁሉም ጠዋት 4፡00 ሰዓት እንዲቀርቡ አዟል፡፡
# ተከሳሾቹ በእስር ቤት ያሉበት ሁኔታ
ተከሳሾቹ ያሉበትን ሁኔታ አስመልክቶ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ፣ “በታሰርንበት ቦታ በቂ ምግብ፣ በቂ ውሃ፣ በቂ መፀዳጃ የለም ” ብለዋል፡፡ ሆኖም፣ ጉዳዩን የሚመለከተው ዳኛ በዛሬው ችሎት እንዳልተሰየሙና ብይኑን ያነበቡት ዳኛ በጊዜያዊነት መምጣታቸውን አስታውቀው፣ አቤቱታውን በጽሁፍ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ ከተከሳሾች መካከል አሌክስ ሸገር እንደታመመ የታወቀ ሲሆን፣ በጥቅሉ በአባ ሳሙኤል ያሉት እስረኞች በረሃብ ጭምር እየተሰቃዩ መሆናቸውን ለቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።
በመርካቶ የ32 ቀበሌ ነዋሪዎች “ተጨማሪ ልጆቻችንን ለእስር አሳልፈን አንሰጥም” በማለት ፖሊስን ተቃወመ
# ቅዳሜ ዕለት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ፖሊስ በሰፈሩ ተሰማርቶ፤ ህብረተሰቡ ላይ መሳሪያ በመምዘዝ ሽብር ሲስፍጥር ውሏል
/
በተለምዶ 32 ቀበሌ ተብሎ በሚታወቀው የመርካቶ አካባቢ /ፋሲል ፋርማሲ አካባቢ/ ያሉ ነዋሪዎች፣ ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 3/2014 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ፣ “ተጨማሪ ልጆቻችንን ለፖሊስ አሳልፈን አንሰጥም”በማለት ከፖሊስ አባላት ጋር ግብግብ ውስጥ ገብተዋል፡፡  ከሰፈሩ በርካታ ወጣቶች ሰሞኑን ታስረዋል።
ቅዳሜ ከሰዓት አንድ ተጨማሪ ወጣት በመያዝ ወደ ሰፈሩ የገባው የፖሊስ ኃይል፣ ሲቪል ለብሶ የነበረ ሲሆን፣ ወጣቱን ለመያዝ ሲሞክር ነዋሪው ጣልቃ ገብቶ፣ “ወጣቱን አሳልፈን አንሰጥም” በማለታቸው ግብግብ ተፈጥሮ፣ በጊዜው የነበሩት 4 ሲቪል የለበሱ ፖሊሶች  ሽጉጥ አውጥተው ምንም መሳሪያ ያልያዘውን ነዋሪ እያስፈራሩ ልጁን ይዘው ከአካባቢው ወጥተዋል፡፡ ፖሊሶቹ መሳሪያ ሲያወጡ የአካባቢው ሽማግሌዎች ነገሮችን ለማብረድ ጣልቃ ባይገቡ ኖሮ፣ ጉዳት ሊደርስ ይችል እንደነበር በቦታው የነበሩት ታዛቢዎች ተናግረዋል፡፡
ወጣቱ ፖሊስ ጣቢያ ከደረሰ በኋላ ድብደባ የደረሰበት ሲሆን፣ ወደተያዘበት አና ተቃውሞ ወደተነሳበት አካባቢ በርካታ ክላሽ የታጠቀ ፖሊስ ተልኮ አካባቢው ላይ ከፍተኛ ውጥረት ሰፍኗል፡፡ በዚህ ሳቢያ ተጨማሪ ወጣቶች ከሰፈሩ እየለቀቁ ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ ተገደዋል፡፡ ቅዳሜ ዕለት በፖሊስ በኩል የነበረው ፍላጎት ከአንድ በላይ ወጣት ለመያዝ እንደነበር እና ነዋሪው ባስነሳው ተቃውሞ እንደከሸፈ በበሰፈር ውስጥ እየተነገረ ይገኛል፡፡
Filed in: Amharic