>

H.R.6600 እና S.3199...!!! (D.W)

H.R.6600 እና S.3199…!!!

D.W

የዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) የዉጪ ግንኙነት ኮሚቴ ዛሬ ኢትዮጵያን በሚመለከተዉ S.3199 በተባለዉ ረቂቅ ሕግ ላይ ይነጋገራል።ባለፈዉ የጎርጎሪያኑ 2021 የተረቀቀዉ ሕግ የኢትዮጵያን ሠላምና ዴሞክራሲን ለመደገፍ (ለማበረታት) ያለመ እንደሆነ አርቃቂዎቹ አስታዉቀዋል።S.3199 ረቂቅ ሕግ ከዚሕ ቀደም ለዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መምሪያ ምክር ቤት ከቀረበዉና H.R.6600 በሚል መለያ ከሚታወቀዉ ጋር ተመሳሳይ ግን ተጨማሪ ነዉ።
የኒዉ ጀርሲዉ የዴሞክራቲክ ፓርቲ የምክር ቤት እንደራሴ ቶም ማሊኖቭስኪ ያቀረቡት H.R.6600ን የካሊፎርኒያዋ የሪፐብሊካን ፓርቲ እንደራሴ ዮንግ ኦአክ ኪም፣ የኒዮርኩ የዴሞክራቲክ ፓርቲ እንደራሴ ግሪጎሪይ ዳብሊዉ.ሚክስ እና የቴክሳሱ የሪፐብሊካን ፓርቲ እንደራሴ ማይክል ቲ. መክካዉል በተባባሪነት አቅርበዉታል።H.R.6600፣ «ኢትዮጵያ ዉስጥ መረጋጋት፣ ሰላምና ዴሞክራሲን ለማስፈን የሚደረገዉን ጥረት ለመደገፍ» የሚል ርዕሰ የተሰጠዉ ረቂቅ ሕግ አቅራቢዎች እንደሚሉት የኢትዮጵያ ሠላም፣መረጋጋትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን የሚያዉኩ ኃይላትን ለመቅጣት ያለመ ነዉ።
በረቂቅ ሕጉ መሰረት የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር (መንግስት) የኢትዮጵያን ሠላምና መረጋጋት የሚያሰጉ፣ የመንግስትና የተለያዩ ወገኖች (በተለይ የትግራይ ኃይላት) የገጠሙትን ጦርነት ለማስወገድ ተኩስ አቁም ዉል ለማድረግ የሚደረገዉን ሒደት የሚያዉኩ፣ሰብአዊ ርዳታ እንዳይደርስ የሚያደናቅፉ ወይም ሰብአዊ መብቶችን የሚጥሱ ወገኖችን ወይም ግለሰብን የጉዞ እገዳን ጨምሮ በተለያየ መንገድ ይቀጣል።
ከዚሕም በተጨማሪ ረቂቁ ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ ከምትሰጠዉ የዉጪ ድጋፍ ለተወሰነ መስክ የሚሰጠዉ እንዲቋረጥ የሚደነግግ ነዉ።የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ኢትዮጵያ ዉስጥ ተፈፅመዋል የተባሉ የጦር ወንጀሎች፣በሰብአዊነት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎችና የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን ለሚመረምሩና ለሚያጣሩ ወገኖች (ተቋማት ወይም ድርጅቶች) ድጋፍ እንዲሰጥ ይጠይቃል። የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ኢትዮጵያ ዉስጥ ሰላምን፣ እርቅንና ሰብአዊ መብትን ለማስፈንንና ለማስከበር የሚረዳ ስልት (ስትራቴጂ) እንዲቀርፅና ገቢር እንዲያደግ ይጠይቃልም። አስተዳደሩ በዚሕ ሕግ መሰረትና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያከናወናቸዉን ተግባራት ለምክር ቤቱ (ኮንግረስ) ዘገባ እንዲያቀርብ ይጠይቃልም።
ረቂቁን የኢትዮጵያ መንግስትና ዉጪ በተለይም ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንና ኢትዮጵያዉያን-አሜሪካዉያን በተደጋጋሚ ተቃዉመዉታል።ረቂቁ እንዳይፀድቅም በአደባባይ ሰልፍ ጭምር ከፍተኛ ግፊት እያደረጉ ነዉ።ይሁንና እዚያዉ ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ የኢትዮጵያ የመብት ተሟጋቾች ረቂቁ «ከጥንቃቄ» ጋር ቢፀድቅ ኢትዮጵያ ዉስጥ የመንግስት ባለስልጣናትም ሆኑ ከመንግሥት ዉጪ ያሉ ኃይላት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚያደርሱትን ግድያ፣ ግፍና ማፈናቀልን ለማስቀረት ይረዳል  ባዮች ናቸዉ።
Filed in: Amharic