>

የፓርቲዎች ዳንስ ለምን ? (ፊዳ ቱምሳ)

የፓርቲዎች ዳንስ ለምን ?

ፊዳ ቱምሳ

የ ታዛቢዉ ማስታወሻ
ሰሞኑን ፓርቲ ተብየዎች በ ዉድ ሳይሆን ተገደዉ ጉባኤ እያደረጉ መሆኑን ተመለከትን፣ አንዳንዶቹ ተጣድፈዉ ጊዜ እንዲራዘምላቸዉ ጠየቁ፣ ሌሎች ሃገር ዉስጥ ያለዉ ሁኔታ አያስችለንም ብለዉ ማመልከቻ አስገቡ። ሁሉም ድራማ መሆኑን የተረዱት አይመስልም። የፓርቲ አላማና ምንነት የገባቸዉም አይመስሉም።
የፖለቲካ ፓርቲ፣ አላማ ላይ ተመስርቶ ፣ የፖለቲካ ቅቡልነትን ከህዝብ አግኝቶ፣ ገዥ በመሆን መንግስት የፓርቲዉን አስተሳሰብ አቅጣጫ እንዲከተል ለሚደረግ የትግል መሳሪያ ነዉ። የፓርቲ አስፈላጊነትና ተሳትፎ በመጀመርያ ደረጃ የሚወሰነዉ፣ በሃገሪቱ ዉስጥ የፓርቲዎች ዉድድር ሲኖ ርና፣ ፓርቲዎች የመንግስትን አመራር ተቀብለዉ የመንግስት አስተዳደርን መምራት የሚችሉበት ዋናዉ መንገድ ነፃና አድሎ የለሽ ምርጫ ሲሆን ነዉ። ይህ የመንግስት አመራርን የመቀበል ጉዳይ፣ የመንግስት አስተዳደር ከፓርቲዎች የተለየ መሆኑን ያገናዘበ ነዉ። የመንግስት አስተዳደርና አስተዳደሩን አቅጣጫ ለማስያዝ በምርጫ አሸናፊ በሆነው ፓርቲ የሚመደቡ የፓርቲ ባለሥልጣናት መካከል በህግ የተወሰነ ልዩነት ሲኖር ነዉ።
በዛሬዋ በኢትዮጵያ ገዢው ፓርቲ አስራ አንድ ሚልዮን አባላት አለኝ ሲል እየነገረን ያለው መላው የመንግስት አስተዳደር በፓርቲው አባላት መሞላቱን ነው። ይህ ደግሞ የሚያመላክተው በፓርቲውና በመንግስት መካከል ምንም ልዩነት ያለመኖሩን ነው። የ መንግስት አመራርና የመንግስት አስተዳደር ሙሉ በሙሉ ትናንት ኢህአደግ ነበር የተያዙት፤ ዛሬ ደግሞ ብልጽግና ነዉ። እናም በኢትዮጵያ በፓርቲዎች መካከል የሚደረግ ፉክክር፤ የመንግስትን ሥልጣን ለመያዝ ና የመንግስትን አስተዳደር አቅጣጫ ወደ አሸናፊ ፓርተ አስተሳስብ ባማመላከት
የሚደረግ ትግልና ፉክክር ሳይሆን፤ መንግስትና ፓርቲ አንድ በመሆናቸው መንግስትን ለመጣል የሚደረግ ግብ ግብ ነዉ።
በሀገሪቱ ዉስጥ ያሉ ፓርቲዎች ያልተረዱት ይሄንን ሃቅ ነዉ። ሥልጣን ለመያዝና መንግስትን በመጣል መካከል ያለዉን ልዩነት ያልተገነዘቡ “ፖለቲከኞች” የፓርቲ ጉባኤ ለማድረግ ሲሯሯጡ ማየትን ያህል የሚያስቅ ነገር የለም።
በኢትዮጵያ ለዉጥ የሚፈልግ አካል ካለ ይሄንን ሀቅ መረዳት አለበት፤ ትግሉ መሆን ያለበት መንግስትን የመጣል እናም ከፓርቲ ነፃ የሆነ የመንግስት አስተዳደር መመስረት እንጂ፤ የመንግስት ሥልጣንን ለመያዝ የሚደረግ አይደለም። የዛሬው ትግል የመንግስትን ሥልጣን ለመያዝ የሚደረግ ትግል ቢሆን ኖሮ ትግሉ ሰላማዊ ይሆን ነበር። ጉዳዩ ግን የመንግስት አስተዳደርና የመንግስት አመራር ሙሉ በሙሉ ፓርቲ በሆነበትና፤ በመንግሥትና በብልጽግና ፓርቲ መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት በ ሌለበት፤ የፖለቲካ ትግል መልኩ ወደድንም ጠላን ም፤ መንግስትን ለመጣል የሚደረግ አብዮታዊ ትግል ብቻ ነዉ።
ለዚህ ነዉ ዛሬ ሰላማዊ ትግል የሚሉትም ህዝብን ለእምብተኝነት፣ ለአልገዛም ባይነት መቀስቀስና ማደራጀት፤ ያለባቸዉና በትጥቅ ትግል ዉስጥ ያሉትን መደገፍ ባይችሉም መቃወም የሌለባቸዉ። ሌላ አማራጭ የለም የመንግስት አስተዳደርና ገዥው ፓርቲ የተለያዩ እስካልሆኑ ድረስ፤ ስለ ህጋዊነት መጨነቅ አይገባም። የፓርቲ ጉባኤ ለማድረግ ላለማደረግ መደነስም ዋጋ የለዉም።
Filed in: Amharic