>

ማዕቀብ  መንግስትን ከማንበርከኩ በፊት ሀገርና ሕዝብን እንደሚያንበረክክ ከኢራቅ፣ ከሶርያ፣ ከየመን መማር አለብን....!!! (አቶ ሙሼ ሰሙ)

ማዕቀብ  መንግስትን ከማንበርከኩ በፊት ሀገርና ሕዝብን እንደሚያንበረክክ ከኢራቅ፣ ከሶርያ፣ ከየመን መማር አለብን….!!!
አቶ ሙሼ ሰሙ

አሁን የት እንደገቡ ባላውቅም “ጣሊያን ቅኝ ገዝታን” ቢሆን ኖሮ ችግሮቻችን ሁሉ ጠፍተው ሀገራችን ትለማ ነበር ብለው ከልባቸው የሚያምኑ፣ የአባቶቻችን እምቢኝ አሻፈረኝ አልገዛም ባይነት ለዛሬ ምቾታቸው አለመሳካትና ተንደላቆ ላለመኖራቸው እንደ ደንቃራ የሚወስዱ “ዜጎች” እንደነበሩን አስታውሳለሁ፡፡
ዛሬ ደግሞ የሕዝቤን መብትና ጥቅም ለማስከበር ተደራጅቼና አደራጅቼ አማራጭ ያልኩትን የትግል ስልት ተጠቅሜ እታገላለሁ፣ ታስሬ፣ ተሰድጄና ተሰውቼ የሕዝቤን መከራና ስቃይ እካፈላለሁ ፤ ነጻነቱንም አረጋግጣለሁ ከሚል ሕዝባዊ ጽናትና ቁርጠኛነት ይልቅ የልዕለ ኋያላን አውዳሚ ማዕቀብ እንዲሰብረን መማጸን የሚያኮራ ተግባር ሆኗል።
ሉዕላዊነት ትርጉም ከማጣቱ የተነሳ አማራጫችን ሁላ አንድ ጊዜ የቻይና መንግስት ይድረስልን፣ ሌላ ጊዜ የራሻ መንግስት ከጉድ ያውጣን አሊያም የአሜሪካ ሴኔት መንግስታችንን ያንበርክክልን የሚል ነው። ማዕቀብ  መንግስትን ከማንበርከኩ በፊት ሀገርና ሕዝብን እንደሚያንበረክክ ከኢራቅ፣ ከሶርያ፣ ከየመን መማር አልፈለግንም።
በዚህ ላይ አሳዛኙ ጉዳይ መርህ አልባነቱ ነው። ትናንት አሜሪካ እጅግ የለዘበ ሪዞልዮሽን ልታጸድቅ ስታቅድ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ መግባት ነው ሲሉ የነበሩ ሁላ፣ ዛሬ መለስ ብለው አሜሪካ አውዳሚ ሪዞሉሽን በማጽደቅ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ትግባልን እያሉ ሲማጸኑ ማየት እኛን አይደለም አሜሪካኖቹንም ቢሆኑ “መርህ” የሚባለው ቃል በመዝገበ ቃላታችን ውስጥ መኖሩን እንዲጠራጠሩ የሚያደርግ ነው
መንግስት ላይስማማን ይችላል። እንዲለወጥ መታገል የዜግነት መብትና የውዴታ ግዴታችን ነው። ዘለቄታ ያለው መንገድ ከታሰበም፤ ውድ ዋጋ ቢያስከፍልም ብቸኛው መንገድ በሕዝብ መፍትሔ ሰጭነት ላይ መተማመን ብቻ ነው።
ፈተናና ችግር ባጋጠመን ቁጥር የአሜሪካ መንግስት ማዕቀብ ጥሎ ሕዝብ አዋርዶ፣ ሀገር አዳክሞ፣ መንግስት ገልብጦ የሚመሰርትልን ቅምጥ መንግስት መፍትሔ ከመሰለን ፍጹም ተሳስተናል። ይህ መንገድ ከውድቀት ባሻገር ማቆምያ ወደ ሌለው የግጭት አዙሪት ይወስደን እንደሁ እንጂ የታሪክችን አኩሪ ምዕራፍ ሊሆን አይችልም።
Filed in: Amharic