DW
በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን የሰገን ዙሪያ ወረዳ ገቢዎች ጽህፈት ቤት ሃላፊን ጨምሮ 9 ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ ፡፡ የሟች ቤተሰቦችና የአካባቢው ነዋሪዎች እንዳሉት ሰዎቹ ባለፈው ቅዳሜና እሁድ የተገደሉት በዞኑ ኮልሜ ክላስተርና ሰገን ዙሪያ ወረዳ ውስጥ ነው፡፡ የዲመያ መንደር ነዋሪ ነኝ ያሉ አንድ የአይን እማኝ ታጣቂዎቹ ከአጎራባች አሌ ልዩ ወረዳ በመነሳት ወደ አካባቢው የገቡት እንደመትረየስ የመሳሰሉ ለየት ያሉ የጦር መሣሪያዎችን በመያዝ ነው ሲሉ ለዶቼ ቬል / DW / በሥልክ ገልጸዋል፡፡
የኮንሶ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ሃላፊ አቶ ገረሱ ከተሌ በተባሉት አካባቢዎች 9 ሰዎች በታጣቂዎቹ መገደላቸውንና 13 ሰዎች መቁሰላቸውን ለዶቼ ቬል / DW / አረጋግጠዋል፡፡ በተጨማሪም በዞኑ ኮልሜ ክላስተር ኩርቦና ዲመያ በተባሉ መንደሮች የመኖሪያ ቤቶችን ማቃጠላቸውንም አቶ ገረሱ ተናግረዋል፡፡ ታጣቂዎቹ ቦታዎቸውን በፍጥነት በመለዋወጥ ሥለሚንቀሳቀሱ ለይቶ ለመያዝ ወይም ለመደምሰስ የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ ቢያደርገውም ከደቡብ ክልል ልዩ ሀይልና ከፌደራል የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለመያዝ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በዚሁ ኮንሶ ዞን አቶ ገረመው ገለቦ የተባሉ የሰገን ዙሪያ ወረዳ ገቢዎች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በጥይት ተደብድበው መገደላቸው የሟች ቤተሰቦች ለዶቼ ቬሌ DW ገልፀዋል፡፡ የሟች አባት አቶ ገለቦ አበራ ልጃቸው የተገደለው በአንድ ምግብ ቤት ውስጥ እራት በመብላት ላይ እንዳለ ገዳዮቹ በመስኮት በኩል በከፈቱበት የተኩስ እሩምታ መሆኑን በመጥቀስ መንግሥት ፍትህ ይሰጠን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ የሰገን ዙሪያ ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት ሃላፊ ግድያ የተፈጸመው በግል ቂም መነሻ ወይም የፖለቲካዊ እጀንዳ ባላቸው አካላት ሥለመሆኑ እስከአሁን የተረጋገጠ መረጃ እንደሌለ የጠቀሱት የኮንሶ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ሃላፊ አቶ ገረሱ ከተሌ ያም ሆኖ ሁኔታውን የሚያጣራ ቡድን ዛሬ ወደ ሥፍራው መላኩንና የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለመያዝ ግን ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የኮንሶ ዞንና ታጣቂዎች ይንቀሳቀሱበታል የተባለው የአጎራባች አሌ ልዩ ወረዳ መስተዳድር አመራሮችና የተጎራባች ቀበሌ ነዋሪዎች ተወካች ጥቃቱን ማስቆም በሚቻልበት ሁኔታ ከትናንት ጀምሮ በጋራ እየመከሩ እንደሚገኙም የመምሪያው ሃላፊ ተናግረዋል፡፡
ዘገባ ፡ ሸዋንግዛው ወጋየሁ ዶቼ ቬል / DW /
ፎቶ ፡⇑ከኮንሶ ዞን መንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያና ከኮንሶ ዜና የተወሰደ