>

ማመንና የሳይንስ እውቀት ለየቅል! ማጥላላት አላዋቂነትን አይሸፍንም። ማሳረጊያ ክፍል 3 (በ አኒሳ አብዱላሂ)

ማ መንና የሳይንስ እውቀት ለየቅል!

ማጥላላት አላዋቂነትን አይሸፍንም።

ማሳረጊያ

ክፍል 3

ካለፈው የቀጠለ

በ አኒሳ አብዱላሂ


የተከበራችሁ አንባቢያን፣ 

  ክፍል 2   መጨረሻ  ለማነፃፀሪያ ያመቻችሁ ዘንድ ለአፅናፈ አለም መመስረት መነሾ የሆነውን የአሃዝ ቁጥር ከቁስ አካል መሰረት ከሆነው አቶም ውስጥ ካሉት ንጥረ ነገሮች ጋር በማየት እንዴት በእጅጉ እንደሚበላለጡ ለመጠቆም ነበር። ይህም ያለ ምክንያት አልነበረም። በጥቃቅን ንጥረ ነገሮችም ሆነ እጅግ ትላልቅ ጋላክሲዎች ስላለው ሁኔታ ለመረዳትና ግልፅ ለማድረግ በቁጥር አሃዝ ማስቀመጡ አመቺ ሆኖ በመገኘቱ ነው። እነዚህ የተጠቀሱት መረጃዎች እንደምታስተውሉት በእጅጉ አናሳ የሆነ ቁመና (ክብደት፣ እርዝማኔና እንግፍታ matter, density and length)  ቢኖራቸውም በጥቃቅኑ ንጥረ ነገሮች አለም ውስጥ ግን ልኬታቸውም ሆነ ክብደታቸው ከፍተኛ ሚዛን ያላቸው ናቸው። ይህ ስለ ቁጥር ጠቃሚነት፣ በተለይም ደግሞ አስፈላጊነቱን በሚመለከት በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል ነው። ይህ ሆኖ ሳለ ሊቃውንቶችና ተመራማሪዎች ለቁጥር ያላቸው አዎንታዊ አስተያየት በአቶ አሳፍ ላይ ከፍተኛ አግራሞትን ለምን ይጭርባቸዋል? የግንዛቤ ማነስ ይሆን? ለማንኛውም እስቲ በራሳቸው በአቶ አሳፍ አንደበት የተሰጡትን አስተያየት እንመልከታቸው።  

“አንዳንዴ” ይላሉ አቶ አሳፍ “ግን እነዚህን ቲዎረቲካል ፊዚሲስቶች ማቲማቲሽያንስ፣ እና ሌሎች ብዙ ሳይንሳዊ ኤክስፐሪመንቶቻቸውንና ትንታኔዎቻቸውን በጥቃቅን ላቦራቷሮቻቸውና በግዙፍ የኤሌክትሮን ኮልይደር ፉጋቸው ውስጥ ተቆልፈው የሚረመምሩ ያለም ሳይንቲስቶችና ሊቃውንት ግን አንድ የጋራ ነገራቸው ይገርመኛል..”  ካሉ በኋላ በመቀጠል “በቁጥር እጅግ አብዝተው ያምናሉ። በሚያዩት ናሙና እጅጉን ይንተራሳሉ። በሚሰሩት ስሌት እጅጉን እርግጠኞች ናቸው። ይህ ነገራቸው ግን ብዙ ጊዜ ይገርመኛል።” በዚህ ብቻ አያቆሙም። በማስከተልም “በቁጥር ይቀምራሉ። በቁጥር ይተውራሉ። በቁጥር ቴረም ሰርተው ያመሳክራሉ። በቃ ቁጥር ነፍሳቸው ነው። ቁጥርን እንደ እግዜር ሊያምኑት ምንም አይቀራቸውም። “ በማለት አግራሞታቸውን በተደጋጋሚ አስረግጠው ከገለፁ በኋላ “ለምንድነው ግን እንዲህ ለቁጥር የተገዙት? ለምንድንስ ነው በቁጥር ሁሉ ነገር ላይ እንደርሳለን ብለው የልብ ልብ የተሰማቸው? “ በማለት ጥያቄያቸውን አያቀረቡ በ ”ይገርመኛል” ሲያደነቁሩን ከዋሉ በኋላ ራሳቸው መረዳት ያልፈለጉትን ወይንም እንዲገባቸው ባልጣሩበት ሁናቴ የፅሁፋቸው አንባቢ እንዲመልስላቸው ይፈልጋሉ። በውነቱ አቶ አሳፍ ቁጥር የሊቃውንቶች ብቻ ሳይሆን በሰው ፍጡር የቀን ተቀን የኑሮ ሩጫ መግባቢያ መሆኑን በሚገባ የተረዱት አይመስልም። ይህ ባይሆን ኖሮ የሳቸውን ቃል ልበደርና “ቁጥርን እንደ እግዜር ሊያምኑት ምንም አይቀራቸውም።” በማለት ቀለው አይሳለቁም ነበር። ለነገሩ በፈጣሪ ማመን አለማመን ለየግለሰቡ መተው ያለበት መብት መሆኑ ደግሞ ወደጎን ማድረጉ ለማንም እንደማይበጅ እንዴት ይጠፋቸዋል? 

አቶ አሳፍ በውስጣቸው እየተብላላ ያለው “አንዳንዶቹ ሊቃውንቶች ፈጣሪ አምላክ ፍጥረተ አለሙን “ሀ” ብሎ አልጀመረም ለማለትም ይቃጣቸዋል” በሚል አረፍተ ነገር ይገልፁና እፎይታን የሚያገኙ ይመስል ረዳት ፍለጋ ከካቶሊኩ ጳጳስ ጥቅስ ጀርባ ይሸጎጣሉ። ይህ ግን ምንም አይነት ጠቀሜታ አያስገኝላቸውም። አቶ አሳፍ ያነበቡት መፅሃፍ ውስጣዊ ይዘቱ በቅጡ የገባቸው አይመስልም።  በርግጥም ስላነበቡት መፅሃፍ ሳይንሳዊ ይዘቶቹን አስመልክቶ “በዘርፉ ከሚያውቅ ሰው እንደበት ቢነገር መልካም ነው” በማለት ያቀረቡት ግንዛቤያቸው መልካም ቢሆንም ይህንን ምክራቸውን ራሳቸው ተግባራዊ ለማድረግ ግን አልፈለጉም። አለማወቅ ኃጢያት አይደለም፣ አለማወቅን ተጠይፎ አለማስወገድ እንጅ ከማለት ውጭ የምጨምረው ነገር አይኖረኝም።

ለማንኛውም በበኩሌ እንደገባኝ ስለ ቁጥር ፅንሰ ሃሳብ የሚከተለውን ላቅርብና ወደ ፅሁፌ መደምደሚያ እሸጋገራለሁ። ቁጥር ማንኛውም የሰው ፍጡር ለሚያጋጥመው ችግር መፍትሄ ለመሻት የሚፈልግ ቢኖር በቅድሚያ ስለ ትንታኔ መርህ እንዲያስብ የሚጠይቅ መሆኑን ነው። ቁጥር ለአንድ ችግር መፍትሄ ለመስጠት የተሻለ ችሎታ እንዲኖር የሚረዳ ብቻ ሳይሆን ትንታኔን በመላበስ የተሻለ የማሰብ ችሎታ እንዲኖር የሚረዳ ነው። በተፈጥሯዊ አለማችንና በሷ ዙሪያ ስላሉት ሁለመናዎች በጥልቀት እንድናስብ ችሎታን የሚያጎናፅፍ ሲሆን ያለንን ግንዛቤም ለማሳደግ መጠቀሚያ መሳሪያም ነው። ቁጥር የተወሰነ ተግባር ለማከናወንና ችግርን ለመፍታት ጠቃሚ የሆነ የትምህርት ዘርፍ ነው። ሆኖም ለሁሉም ችግሮች መፍትሄ አለው ማለት አይደለም። የቁጥር ፅንሰ ሃሳብ ስለ አንድ ችግር መፍትሄ ለመስጠት ሲታሰብ ከመጀመሪያውኑ ሥርአት ማሲያዝን፣ መፍትሄ ሰጪነትንና አስረጅነትን፣ ጠቃሚ ናቸው ለሚባሉ ሁሉ ለማሰላሰል ይረዳ ዘንድ ሆን ብሎ ዝግጁነትን ለማግኘት የሚያስችል ችሎታ ያለው ነው። ቁጥር እሳቤንና መምሪያዎችን እንዲሁም፣ መሰረታዊ ደንብን ይሰጣል፣ ያዘጋጃል። ስለሆነም ቁጥር የተወሰነ ችግርን በጣም ትክክልና እጥር ምጥን ባለ ሁናቴ የተሰላ ሂሳባዊና ተአማኒ ሊሆን የሚችል መፍትሄ ለማግኘት፣ ስለ ወደፊቱ ትንበያን ለመስጠት፣ በሌላው በኩል ደግሞ ደግሞ አማራጭ መፍትሄዎችን የሚያቀርብ ነው። አቶ አሳፍ ይህ ይጠፋቸዋል ተብሎ ለማሳብ ይከብዳል። ሆኖም በመጣጥፋቸው የተንደረደሩበት መነሺያቸውና ለማስረገጥ የፈለጉት መደምደሚያቸው በእጅጉ አወዛጋቢ ሆኖ የሚገኘው በዚሁ ስለ ቁጥር የግንዛቤ እጥረት መሆኑን የሚያመላክት ነው። 

በመሆኑም በተግባር ከሚታዩት ጠቀሜታዎች ውስጥ ለምሳሌ በቅርቡ ከሁለት አመት ጀምሮ በመቅሰፍትነቱ በርካታውን የሕዝብ ቁጥር በማሰቃየት ስላለው የኮሮና ቫይረስ እልክፍት አስመልክቶ የሂሳብ ቁጥር ሊቃውንት የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ውሳኔ ለመውሰድ የሚያስችላቸው በቁጥር ፅንሰ ሃሳብ የተሰሩና የተሰሉ ምክርና ጥቆማዎች መለገሳቸው በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል ነው።  በተፈጥሮ ሳይንስና በሌሎችም ሳይንሳዊ ነክ በሆኑ የትምህርት ዘርፎች የተለያዩ ፅንሰ ሃሳቦችን ለማመንጨት/ለማፍለቅ ቁጥር ከፍተኛ ሚና አበርክቷል አሁንም በጥልቀት እያበረከተ ይገኛል። በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስ፣ የምርት ማግኛ ሂደቶችና እድገታቸው፣ በኢንጂነሪንግ ሳይንስ፣ በሕንፃ፣ በመንገድ፣ በድልድይ ግንባታ፣ ሆነ የተለያዩ የዜና ምርቶችን በቁጥር በመተርጎምና በዲጂታሊዝም በመታገዝ  ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ በአጭር ጊዜ ማስተላለፍ ያለ ቁጥር እገዛ የማይታስቡ ናቸው። ታዲያ ሊቃውንቶች በሚያደርጉት ምርምር የቁጥርን ፅንሰ ሃሳብ መጠቀማቸው፣ ለቁጥር እጅግ ከፍተኛ ግምት ቢኖራቸው፣ መጠነ ሰፊ የሆነ እንክብካቤ ቢያደርጉለት፣ ቢሳሱለትም ለምንድን ነው በአቶ አሳፍ በአሉታዊ የሚዘለፉት? ለምንስ ነው ምሁራዊ አክብሮት የሚነፈጋቸው? ምን ባጠፉ? እውቀታቸውንና ያገኙትን የምርምር ውጤት ለሕዝብ ባካፈሉ? ወይንስ የአቶ አሳፍን ፈጣሪ ስለተፈታተኑበት? በርግጥም አግራሞትን ጫረብኝ በማለት ያነሷቸው ሂሶች በርካታ ጥያቄዎችን የሚያጭር ሆነው የሚገኙት  ያለምክንያት አይደለም።

አዎ ችግራቸውን “የጥበብን ሁሉ ፈጣሪ፣ የስሌቶች የቀመሮች ሁሉ ሊቅ የሆነውን የታላቆች ታላቅ ፈጣሪንስ ማክበር ለምን ተሳነን? “ በማለት ከሌሎች በሚገባ ካልተረዱት አስተያየት ጋር በማያያዝ በውስጣቸው የያዙትን ሊቃውንቶቹን በጎሪጥ የሚያዩበትን ሂደት ሳያስቡት ሆን አስበውበት እርግፍ አደረጉት። በቃ ይኸው ነው በውስጣቸው እንዲህ ያንከተከታቸው። ታዲያ ሊቃውንቶቹ የሳቸውን ፈለግ መከተል ይገባቸዋል እንዴ? ስህተት ሆኖ ቢያገኙትስ ምን ሊያረጉ ይፈልጋሉ? ወይንም ያስባሉ? የሊቃውንቶቹ አስተያየት ካልጣማቸው እኮ ጎመን በጤና ብለው በሩቁ ቢመለከቷቸው ጤናማ በሆነ ነበር። ግን ጎሸም አድርገው ማለፉ የልባቸውን መንገሩ አላማ በመሆኑ ካልሆነ ስህተት ሊወድቁ በቁ። ያሳዝናል። “ስተፈን ሃውኪንግ ደስ ያለኝ ፈጣሪን አክብሮ ነው የሚንቀሳቀሰው” በማለት የገለፁት የመጣጥፋቸው እምብርት ይኸው ሲሆን ሌሎቹ ማሟያ ናቸው።  ታዲያ መጀመሪያውኑ ዙሪያ ጥምዝዝ መሄድ ለምን አስፈለጋቸው? 

አቶ አሳፍም ሆኑ መሰሎቻቸው ለመረዳት የሚተናነቃቸው በርግጥም ስለ አፅናፈ አለም በሳይንሳዊ ምርምር መሰረት ግልፅ ለማድረግ ይጥሩ የነበሩት ለምሳሌ እንደ አይሳክ ኒውተን ወይንም አልበርት አንሽታይን በክርስትና እንዲሁም በአይሁዳዊ አስተምሮ ያደጉና አማኝ የነበሩ ሲሆን በጊዜያቸው ፈጣሪን ለመገዳደር ሳይሆን ተግባሩን ግልፅ ለማድረግ ነበር ሲኳትኑ የነበሩት። የምርምራቸው ውጤት ይህ ድርብ ሰረዝ ይጨመርበት ግን በጅምላ እመኑት ስለሚባለው ፈጣሪን ቀስ በቀስ ወደጎን እንዲገፋ አደረጉት። ግፊቱም እየጨመረ መጥቶ ስለምርምሮቻቸው ውጤት ሳይሆን በዋናነት ስለ እምነታቸው ጥኩረት ሰጥቶ ሊቃውንቶቹን ማንጓጠጥና ባይተዋር ከማድረጉ ላይ ነበር ጥረታቸው።  የተጠቀሱት ሊቃውንቶችም ሆኑ ከነሱ በኋላ የቀረቡ ተመራማሪዎች የቁጥርን ፅንሰ ሃሳብ ለተላበሰ ለተፈጥሮ ሳይንስ መዳበርም ሆነ ለታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሃሳብን ይበልጥ ግልፅ የሚያደርግና የሚያጠናክር ምርምራቸውን  በስፋት ተያያዙት። በዚህም የተነሳ ተቃዋሚዎቻቸውም ሆኑ ተገዳዳሪዎቻቸው  እነዚህን ሊቃውንቶችን በደፈናው የራሳቸውን አፈ ታሪክ እምነት ፈጠሩ በማለት መጠነ ሰፊ የሆነ የሀሰት ዘመቻ ቢያካሂዱባቸውም የፅንሰ ሃሳባቸውን ስህተተኛነት የሚያረጋግጡ፣ አመኔታና የተላበሱ ምክንያቶችን ግን ሊያቀርቡ አልተቻላቸውም። 

አቶ አሳፍ ከነዚህ ተርታ በመሰለፍና በሚያምኑበት አስተያየት ተመርኩዘውም ደስተኛ የማያደርጓቸውን ሊቃውንቶች  መሞገትና ለእምነታቸው ጥብቅና መቆም  በግላቸው የመረጡት ስለሚሆን ምርጫቸውን ማንም ቅን አስተዋይ አንባቢ የሚያከብርላቸው እንጂ ያለ ፍላጎት ወደ እንካ ሰላንቲያ ለምን ሊጎትቱ እንደፈለጉ ግራ የሚያጋባ ነው። ለማንኛውም ቀና ምክርን ለመለገስ ያህል በመረጡት ጎዳና ለመሄድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልዎ ማለት አግባብነት ይኖረዋልና በፅኑ ይመቻቸው እላለሁ።

አፅናፈ አለም ከብርሃን ፍጥነት እጅግ በበለጠ ሁናቴ እየሰፋ በመሄድ የተጀመረው ክስተት አሁንም ድረስ በመቀጠል ላይ የሚገኝ ነው። በመሆኑም ከዚህ ከተረጋገጠ መረጃ በመነሳት ስፋቱ የተጀመረበት ሥረምንጩን ምን ያህል እርዝማኔ እንዳለው ለመገመት በምናባችን ወደኋላ በመጓዝና የተፈጥሮ ሕግን በማይቃረን መልኩ ለምሳሌ በሊቃውንቱ ፕላንክ የምርምር ውጤት በስሙ ተሰይሞለት የሚጠቀሰው 1.61 10-33cm  እንደሆነ የተረጋገጠበት ሁናቴ ይገኛል። ይህንን እርዝማኔ በአመታዊ የብርሃን ፍጥነት (በተፈጥሮ ቋሚ ቁጥር ማለት ነው) ስናካፍለው 5,38.10-44s ፍርስራሽ ደቂቃ እናገኛለን። በዚሁ ስሌት በመቀጠል የሥረ መነሾውን ክብደት ደግሞ በስበቱ (ቋሚ ቁጥር) ስናካፍለው 2,18.10-5 g ያበስረናል። በማስከተልም ከክብደቱ ተነስተን ደግሞ የአንሽታይን ቀመር (E = mc2) E = 1.22 10 19 GeV  የእምቅ ኃይሉን ጉልበት እንዲሁም ደግሞ በውስጡ  የታመቀውን የኃይል ሙቀት  T = mc2/k = 1,41 . 1032K ከዚያም ከላይ የተጠቀሰውን እርዝማኔውን በመጠቀም  p = m/l3 = 5,2.10 93.cm3 (እንፍግታውን density) የሂሳብ ፅንሰ ሃሳብ ምስጋና ይግባውና በተጠቀሱት ቀመሮች በመመርኮዝ ተሰልቶ በመገኘቱ ሊቃውንቶቹንና ተመራማሪዎችን ስለሁናቴው በጥልቀት  ለማወቅና ለመረዳት አስችሏቸዋል።  ይህቺን ሥረምንጭ/መነሾ ትንሿ አፅናፈ አለም የሚል ስያሜ ብንሰጣት በአሁኑ ወቅት ከሚገኘው ትልቁ አፅናፈ አለም ቀጥተኛ የዝምድና ግንኙነት በመካከላቸው ሊኖር እንደሚችል ደግሞ የኳንት ፅንሰ ሃሳብ(Quantentheory) ያሳያል። ተተንብዮም በምርምር የተረጋገጠው ይኸው በመሆኑ የታላቁን ፍንዳታ ሂደትና በሂደቱ ስለተከሰቱት ጥቃቅን ንጥረ ነገሮች መፀነስና ወደ ቁስ አካል ብሎም ወደ ከዋክብትና ጋላክሲ መዳበር በዚሁ ፅንሰ ሃሳብ ግልጥልጥ አድርጎ ማሳየትና ግንዛቤ ማስጨበጥ ተችሏል። 

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አሃዞች ለአፅናፈ አለም መፀነስ በሥረምንጭነት የሚጠቀሰው እምቅ ኃይልን ስናጤን እጅግ በጣም ከፍተኛ ሙቀት ያለው መሆኑን እንመለከታለን። በዚህ እጅግ ከፍተኛ ሙቀት የተነሳ ስለ እምቅ ኃይሉ ውስጣዊ ይዘትና ምንነት ከተለያዩ የምርምር ውጤቶች ለማወቅ እንደተቻለው እንደ ውሃ ሳይሆን ከሱ በጥቂቱ የወፈረ ገንፎ እሳት ሲነካው የሚንከተከት አይነት አድርጎ አለበለዚያም እንደ እሳተ ጎመራ ማሰብ ይቻላል። እሳተ ጎመራ ከመሬት ውስጥ ፈንድቶ ከወጣ በኋላ እንደ ወንዝ ውሃ መፍሰስ ባይቻለውም እያዘገመ ባለው ፍጥነት ከፊቱ የሚገኙትን ማናቸውንም እፀዋትንም ሆነ ፍጡራንን በፍርስራሽ ሰከንድ ውስጥ ትን አድርጎ እንደሚያጠፋቸው ከተመክሮ የሚታወቅ ነው። ከዚህ በመነሳት እምቅ ኃይሉ ከእሳተ ጎመራው በብዙ ሚሊያርድ ተመን የሚበልጥ ሙቀትና ጉልበት ያለው መሆኑን ለመገመት አያዳግትም። ከዚህ በተጨማሪ ደልዳላነት(symmetry) ቅርፅ ወይንም ይዘት ያለው ሲሆን ያለማቋረጥ በውስጡ የታቀፉት ጥቃቅን ንጥረ ነገሮች ከተቃራኒዎቻቸው ጋር በሚያደርጉት የርስ በርስ ተፅዕኖ ወደ ቁስ አካልና ኃይል (Matter  Energy/Energy Matter) እየተቀያየሩ ብቻ ሳይሆን በፍጥነት ጉዟቸው በሚያደርጉት ግጭት ለሙቀት መጨመር የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። የአንሽታይን ቀመርን ማሰላሰሉ ይመረጣል። ይህ ሁናቴ ያለምንም ሳንካ እስከ ቀጠለ ድረስ አዲስ የሚፈጠር ወይንም የሚከሰት ነገር አይኖርም። ነገር ግን የእምቁ ኃይል ደልዳናነት ከተቀየረ ግን ሁናቴው ፍፁም ይለወጣል፤ የተከሰተውና በበርካታ ጥናታዊ ምርምሮች የተረጋገጠውም  ይኸው ነው። 

የእምቁ ኃይል ደልዳላነቱ ሲሰናከል የአፅናፈ አለም ስረምንጭ እድሜ 10– 35 አስከ 10-32 ፍርስራሽ ሰከንዶች ባለው ጊዜ ውስጥ ከብርሃን ፍጥነት እጅግ በበለጠ የራሷን ስፋት በ 1030 የሚያጥፍ የመስፋት ሁናቴ አስከተለ። በሥእላዊ መልክ ለመግለፅ አንድ 1 cm2 ስፋት ያለው መሃለቅ መሬታችን የምትገኝበትን ሚልኪ ዌይ ጋላክሲ 10 ሚሊዮን ያህል የሚያጥፍ ሂደት መከሰት ማለት ነው። ይህንን ኩነት ሊቃውንቶቹ ታች በተቀመጠው ሥዕል (በርካታ ተመሳሳይ ሥዕሎችም ይገኛሉ)ግልፅ ያደረጉበትን በጥልቀት ማየቱ ጠቃሚ እንደሆነ የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ አበክሮ ያሳስባል። 

ይህ ክስተት የአንሽታይንን የአንፃራዊ ፅንሰ ሃሳብ የሚቃረን መስሎ ቢታይም ክስተቱ የተካሄደው ቀድሞ ባለ ሕዋ ሳይሆን የሰፋው ራሱ ህዋ በመሆኑ ተከሰተ የሚባለው ቅራኔ ውሃ የማይቋጥር ሁኖ ይገኛል።  የታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሃሳብ ቢያንስ ከ 5,39106.10-44 ፍርስራሽ ጊዜያት በኋላ ያለው በተለያዩ ጥናታዊ ምርምሮች የተረጋገጡ ናቸው። ከነዚህም ውስጥ፣-

  1. አጠቃላይ የአንፃራዊነት ፅንሰ ሃሳብ፣ ፈር ቀዳጅ
  2. የህዋ አካላት እየተራራቁ መሄድ፣
  3. የፍንዳታው ቅሪት በአፅናፈ አለም መገኘት፣
  4. በፍንዳታው የተፈጠሩ ንጥረ ነገሮች በመላ ሕዋ መሰራጨት፣
  5. የከዋክብት እድሜ የተገደበ መሆኑ በምሳሌነትና የፅንሰ ሃሳቡን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ ተብለው  በማስረጃነት የሚጠቀሱ ናቸው። 

በበኩሌ በምርምር ኩነት ገና ያልተገኙና ያልተረጋገጡ በርካታ ክስተቶች ቢኖሩም ይህ ሁናቴ የወደፊቱን ጥረታችንን ሊያደናቅፍብን ጨርሶ አይገባም። በመሆኑም የምርምር ቤተ ሙከራ በየወቅቱ በሚኖረው የእውቀት ግንዛቤ  ላይ በመመስረት በየጊዜው ዘመናዊ ማድረግ የዘወትር ተግባራችን የመሆን አግባብነትን የሚያመላክት ነው። ይህ ማለት በቤተ ሙከራ የተገኙ የተፈጥሮ ህግጋት በአፅናፈ አለም ስለሚከሰቱት ክስተቶችም ሆኑ ማናቸውም ጥያቄዎች የመርመሪያ መሳሪያችን በመሆን የሚያገለግሉ ለመሆናቸው ከተመክሮ ለመገንዘብ የሚቻል ነው። የኩዋንተን ሜካኒክ ፅንሰ ሃሳብ በምሳሌነት የሚጠቀስና በተደጋጋሚ ተጠቃሚ ተደርጎ ይህ ናቸው የማይባሉ እጅግ በርካታ የምርምር ውጤቶች በመገኘታቸው በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እውቀት ለማግኛ በመደበኛ የትምህርት ዘርፍ እንዲሰጡ ሆነዋል። የዚህም መጣጥፍ መሰረቱ ይኸው ነው። በአፅናፈ አለም የምናያቸው ክስተቶችም ሆኑ እንቅስቃሴዎች፣ በመሬታችን ቤተ ሙከራ በምርምር በተገኙ የተፈጥሮ ሕግጋት ለመተንተን፣ ለማብራራትና ግልፅ ለማድረግ መሰረት ለመሆናቸው በሊቃውንቶቹ ብቻ ሳይሆን የተጠቃሚዎችም ቁጥር እየተበራከተ  መምጣቱ የሚሳየውና የሚያረጋግጠው ይህንኑ እውነታ ነው።  የጨረቃም ሆነ የከዋክብቶች እንቅስቃሴ፣ በአይሳክ ኒውተን የዛፍ ፍሬ ከመሬት መውደቅ ያስክተለው ጥያቄ፣  በበርካታ ርቀት ከሚገኙ ከዋክብቶች የሚመነጩ የብርሃን ጨረሮች፣ ወዘተ በቤት ሙከራ የምርመራ ውጤቶች ከተገኙት ጋር እስካተልቃረኑ ድረስ በወቅቱ ያሉትን የግንዛቤያችንን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ ናቸው። በኩዋንተን ሜካኒክ ላይ የተመሰረተውና በበርካታ ሥመ ገናና ሊቃውንቶች ቤተ ሙከራ ተመርምሮ የተረጋገጠው የታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሃሳብ የዛሬ 13.8 ሚሊያርድ አመት አፅናፈ አለም እንዴት እንደተመሰረተ የሚገልፅ ነው ተብሎ በብዙሃኑ ሊቃውንቶች የሚታመንበት በዚሁ ምክንያት እንጂ በሌላ አይደለም። 

አንባቢያን ይህንን አስመልክቶ በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ በርካታ መፅሃፍት አሉና ሊረዱ በሚችሉበት ቋንቋ የታተሙትን ወይንም ደግሞ በቅርበት ሊያገኙ የሚችሏቸውን አፈላልገው እንዲያነቧቸው የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ አጥብቆ ያሳስባል። በመሆኑም ነው በዚህ መጣጥፍ ውስጥ ከፍርስራሾቹ ሰከንዶች አንስቶ እስከ ሶስት ደቂቃ ያሉትን ክስተቶች በሚመለከት ነጥብ በነጥብና በዝርዝር ለመግለጽ የአንባቢያንን ጊዜ በከንቱ ማጥፋት ስለሆነ ተብሎ ያልተካተተው። በበኩሌ በዚህ ርዕስ የተረዳሁትንና የምችለውን ያህል ብያለሁ። የሚታከል ሊኖር እንደሚችል በእጅጉ እገነዘባለሁ። ለአሁኑ በዚሁ እናበቃለን። በሌላ ጊዜ በሌላ ርዕስ እስከምንገናኝ ድረስ መልካም ጊዜ ከመልካም ንባብ ጋር!!

ማስታወሻ

  1. በቅድሚያ ይህንን መጣጥፍ ለማዘጋጀት ምክንያት ለሆኑት ለአቶ አሳፍ ከፍተኛ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በርካታ ቁም ነገሮችን ወደኋላ ተመልሼ እንደገና ለማየትና ለመዳሰስ ብሎም የአዕምሮ ጂምናስቲክ ለመስራት ገፋፋቶኝ በርዕሱ ካለፈው ጊዜ በበለጠ ግንዛቤዬን ለማዳበር እድሉን አግኝቼበታለሁና።
  2. ከሀገሬ ፖለቲካ ቀጥሎ እየከነከነኝ ያለ አንድ ነገር አለ። ይህም በአሁኑ ወቅት በርካታ ሊቃውንቶች መሬትን የመሰሉ Exoplanet የሚል ሥያሜ የሰጧቸው ወደ 1000 (ቁጥሩ ከዚህም ሊያልፍ ይችላል) የሚጠጉ አግኝተዋል። በበኩሌ ጥረት ማድረጋቸውን ፈፅሞ አልቃወምም። ነገር ኤክሶፕላኔቶቹ ከሚገኙበት የርቀት ቦታ አንፃር፣ ወደነሱ ወደፊት ለመጓዝ የሚያስችለን የመጓጓዣ ሁናቴና የሚወስድብን ጊዜ፣ በቅርቡ ወደ ጨረቃና ማርስ ጉዞ ለማድረግ እየተደረጉ ያሉትን መሰናዶዎችና የገንዘብ ወጪ ከግንዛቤ ሲወሰዱ በጃችን ያለቺውን መሬታችንን ሕይወት የሚኖራቸው ፍጥረታት ለአንዴም ለሁሌም እንዳይኖርባት እንዳናደርጋት ከፍተኛ ስጋት አለኝ። የምንኖርባት ያለቺው መሬታችን እንደ አይን ብሌናችን ልንሳሳላት የሚገባት ነች። የተፈጥሮ አየር መዛባት እያስከተለ ያለው ጉዳት፣ በየቦታው በተለይም በታዳጊ ሀገራት እየተደረጉ ያሉ ጦርነቶች፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ በሀገርም ሆነ ወደ ውጭ መሰደድ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋትና አሉታዊ ውጤቶች  በምሳሌነት ሊወሰዱ የሚችሉ ናቸው። የአሁኑ ትውልድ ባለቤት ማወቅ ያለበት ከወደፊቱ ትውልድ የተበደራት እንጂ በግል ሞኖፖል የያዛት አይደለችምና እጅግ ልዩ ትክረት ልንሰጣት ይገባታል። በመሆኑም በጥልቀት ብናስብበት መልካም ነው እላለሁ። የማንም ጥገኛ ሳይኮን በግልም ሆነ እንደ ሕብረተሰብ ራስን በራስ የማስተዳደር ነፃነትን የመጎናፀፍን የመሰለ እሴት አለ ብዬ ስለማላምን ለዚህ መከፈል የሚገባን ሁሉ ከፍለን ተግባራዊ ለማድረግ የሁሉም ጥረት ሊሆን ይገባዋል።
Filed in: Amharic