>

የብልፅግና የውስጥ አንድነት ትልቅ ፈተና ላይ ወድቋል! (ባልደራስ)

የብልፅግና የውስጥ አንድነት ትልቅ ፈተና ላይ ወድቋል!

ባልደራስ

 

በብልፅግና የሚመራው የኦሮሚያ ክልል  ከቤንሻንጉል፣ ሲዳማና አማራ ክልሎች ጋር ግጭት ላይ ነው!
 
በብልፅግና የሚመራው የኦሮሚያ ክልል ከሞላ ጎደል ከሁሉም አጎራባች ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ጋር አለመግባባት ያለው ሲሆን፣ በአሁኑ ግዜ ከዐማራ፣ ከቤንሻንጉልና ከሲዳማ ክልሎች ጋር ግጭት ላይ ነው፡፡
ዛሬ ቤንሻንጉል ክልል ባወጣው መግለጫ፣ የክልሉ የካሚሼ ዞን ማረሚያ ቤት አዛዥ ጨምሮ ሶስት የፀጥታ አካላት በምዕራብ ወለጋ እንደታገቱበት ገልጿል፡፡ እገታው የተፈፀመው፣ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ከአሶሳ ሁሮ ካሚሼ ዞን እየሄዱ ባለበት ግዜ ነው፡፡ ታጋቾቹ የት እንዳሉ እና በምን ምክንያት እንደታገቱ ባይታወቅም፣ ስልክ ተደውሎ በህይወት እንዳሉ መስማቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በተለይ ዐማሮች በታጣቂዎች እየታገቱ ገንዘብ መጠየቅ የተለመደ ተግባር እየሆነ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የክልሉ ፀጥታ ኃይሎች ለዚህ ዓይነት የህግ ማስከበር እርምጃ ለመተባበር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን የክልሉ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
በተያያዘ ዜና፣ በኦሮሚያና በሲዳማ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ባለፈው ምሽት በተቀሰቀሰ ግጭት ቢያንስ 5 ሰዎች መገደላቸውን የሲዳማ ክልል የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ አስታውቋል፡፡ ከአምስቱ ሰዎች መካከል ከሲዳማ ሁለት ከኦሮሚያ ሶስት ናቸው ተብሏል፡፡ እንደሚታወቀው፣ ባለፈው ሳምንት በምንጃር በነበረ ግጭት የኦሮሚያ ክልል በዐማራ ክልል አሉ ባላቸው “ፅንፈኞች” ላይ ከትላንት በስቲያ መግለጫ አውጥቷል፡፡
የብልፅግና የውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ፣ በድርጅቱ ውስጥ ያለው የውስጥ አንድነት ከመጀመሪያውም አንስቶ የጠበቀ አለመሆኑ የታወቀ ቢሆንም፣ ክፍፍሉ በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ለዘብ ብሎ ከቆዬ በኋላ፣ አሁን ጦርነቱ ጋብ በማለቱ እያገረሸ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በተለይ በኦሮሚያና በዐማራ ክልሎች መካከል ያለው ሁኔታ በእጅጉ አስጊ ከመሆኑ አኳያ፣ በመሳሪያ የታገዘ ግጭት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት አለ፡፡
Filed in: Amharic