>

የአምንስቲ የወልቃይት ዘገባ፤ አሁን ለምን? (መስፍን አረጋ)

የአምንስቲ የወልቃይት ዘገባ፤ አሁን ለምን?

 

መስፍን አረጋ


ምዕራባውያን ቅኝናፋቂወች (neocolonialists) በተለየም ደግሞ እንግሊዞች የአማራ ሕዝብ መሠረታዊና ዘላለማዊ ጠላቶች የመሆናቸውን ጉልህ ሐቅ የአማራ ሕዝብ እያነቀውም ቢሆን ውጦ፣ ከነዚህ ፀራማራ ምዕራባውያን የሚመነጭን ማናቸውንም ነገር በዚህ ሐቅ መሠረት ማስተናገድ አለበት፡፡  ዋና መሠረቱ እንግሊዝ ላይ የሆነው (በሰበአዊ መብት ሰበብ የምዕራባውያን ቅኝናፋቂወችን አጀንዳወች ለማራመድ የተቋቋመው) አምንስቲ ኢንተርናሽናል (Amnesty Internatioal) የሚባለው የቅኝናፋቂወች ድርጅት በወልቃይት ላይ ያቀረበው ፀራማራ ዘገባም ሌላ ምንም ሳይሆን የዚህ ጉልህ ሐቅ ጉልህ ነጸብራቅ ነው፡፡ 

ከአድዋ ድል በኋላ የምዐራባውያን ዋና ዓላማ ነጭን ነጫጭባ የሚሉትን፣ በማንነታቸው የሚኮሩትን አማሮችን ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ጨዋታ ሙሉ በሙሉ በማስወጣት፣ ለነጭ የማጎብደድ ዝንባሌ በተጸናወታቸው የትግሬና የኦሮሞ ጎጠኛ ሎሌወቻቸው አማካኝነት አገሪቱን በበላይነት መቆጣጠር ነው፡፡  አሁን ላይ ደግሞ ወያኔ በአማራ ሕዝብ ላይ ይፈጽመው የነበረውን ዘርተኮር ጭፍጨፋ ከማስቀጠል አልፎ እጅግ የከፋ ባደረገው በኦነጋዊ ሎሌያቸው በዐብይ አሕመድ አማካኝነት ዘመናት ያስቆጠረውን ፀራማራ ዓላማቸውን ለማሳካት ከጫፍ ላይ ደርሰዋል፡፡  ስለዚህም (ቢያንስ ቢያንስ ፀራማራ ዓላማቸውን ባሽከራቸው በዐብይ አሕመድ ጉዳይ ፈጻሚነት ሙሉ በሙሉ እስከሚያሳኩ ድረስ) አማሮች ለዐብይ አሕመድ ፀራማራ መንግስት ሥጋት እንዳይሆኑ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ዲንጋይ፣ የማይፈጥሩት ትርክት የለም፡፡  

አማሮች የዐብይ አሕመድን ኦነጋዊ ፀራማራ መንግስት እንዳይገዳደሩ ለማድረግ ከሚጠቀሙባቸው ዘዴወች ውስጥ አንዱና ዋናው ደግሞ የወያኔ ተዋናዮችን ቀጥረው የዘር ጭፍጨፋ ተውኔት በመተወን፣ ተጨፍጫፊወቹን አማሮች በጨፍጫፊነት እየሳሉ ማሸማቀቅና፣ በጦር ወንጀለኝነት ትጠየቃላችሁ እያሉ ማስፈራራት ነው፡፡  አምንስቲ ኢንተርናሽናል በየጊዜው የሚዘግባቸው ዘገባወች፣ የአሜሪቃ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በየጊዜው የሚያወጣቸው ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው መግለጫወች፣ እንዲሁም ቢቢሲ (BBC) እና ሲኤንኤን (CNN) ሳያሰልሱ የሚነዟቸው “ትግሬወች ባማሮች ተጨፈጨፉ” እያሉ ያዞ እንባ የሚያነቡባቸው አጭቤ ዜናወች (fake news) ዓላማቸው አንድና አንድ ሲሆን፣ እሱም አማሮችን በጦር ወንጀለኝነት በማሸማቀቅና በማስፈራራት የዐብይ አሕመድን ፀራማራ መንግስት እንዳይገረስሱት ማድረግ ነው፡፡  ለዚህ ማስረጃው ደግሞ እነዚህ ዘገባወቸ፣ መግለጫወችና አጭቤ ዜናወች ሁልጊዜም ሆነ ብለው የሚለቀቁት አማሮች ሆ ብለው ለመነሳት ፍንጭ ባሳዩ ቁጥር መሆኑ ነው፡፡     

ለምሳሌ ያህል አምንስቲ ኢንተርናሽናል የአማራን ሕዝባዊ ሠራዊት (ፋኖ) “ትግሬ ጨፍጫፊ” በማለት የከሰሰበትን አጭቤ ዘገባውን (fake report) የለቀቀው፣ ይሄው የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት የዐብይ አሕመድን ወራሪ የኦነግ ሠራዊት ሚንጃር ላይ ድባቅ በመታው በጥቂት ቀናት ውስጥ ነው፡፡  የዚህ የአምንስቲ መግለጫ ዋና ዓላማ ግን ባሜሪቃ መንግሥት አደራዳሪነት ዐብይ አሕመድና ደብረጺዮን የአማራን ክልል ለመቀራመት (scramble) የተስማሙትን በቅርብ ቅን ይፋ የሚሆን ስምምነት፣ በትግሬ ጨፍጫፊነት ተከሶ አንገቱን እንዲደፋ የተደረገው የአማራ ሕዝብ ያለ ምንም ማቅማማት አሚን ብሎ እንዲቀበል ማድረግ ነው፡፡  ባጭሩ ለመናገር የአምንስቲ መግለጫ አሁን ላይ የተለቀቀበት ዓላማ አንድና አንድ ሲሆን እሱም የወያኔና የኦነግ ስምምነት በቅርቡ ይፋ ሲደረግ የአማራ ሕዝብ መቃወም ቀርቶ እንዳያጉረመርም ለማድረግ ነው፡፡  

ረዥም ዘመን ካስቆጠረው ፀራማራ አጀንዳቸው በተጨማሪ፣ አማሮች የሩሲያን ባንዲራ ይዘው አድዋን ማክበራቸው፣ አማረኛ ጥርት አድርገው የሚናገሩት የሩሲያ አምባሳደር የአማራን ክልል መጎብኘታቸውና ፋኖወች ባጠቃላይ የአፍሪቃ በተለይም ደግሞ ያገራቸው የጦበያ ዘላለማዊ ጠላት የሆኑትን ምዕራባውያንን ከሩሲያ ጎን ሁነው ለመዋጋት የሚዘምቱበት ዕድል ሊፈጠር የመቻሉ ጉዳይ ምዕራባውያንን ከማስቆጣት አልፎ አብግኗቸዋል፡፡  በዚህም ምክኒያት ሰርብያ (Serbia) እና ሰርቦች ላይ እንዳደረጉት በአማራ ክልልና በአማሮች ላይ የቦንብ ዶፍ ለማውረድ ቋምጠዋል፡፡  አምንስቲ ኢንተርናሽናልና መሰሎቹ እያደረጉ ያሉት ለዚህ ከኔቶ ጀቶች ለሚወርድ የቦንብ ዶፍ የዘር ጭፍጨፋ ሰበቦችን መፍጠር ነው፡፡  

Email; mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic