>

የኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎትና በስሙ የሚነግዱት የጐሣ ፖለቲከኞች ፍላጎት አይገናኝም (ከይኄይስ እውነቱ)

የኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎትና በስሙ የሚነግዱት የጐሣ ፖለቲከኞች ፍላጎት አይገናኝም!

ከይኄይስ እውነቱ


የኦሮሞ ሕዝብ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ በርካታ ነገዶችና ጐሣዎች አንዱ ነው፡፡ የጐሣ ፖለቲከኞች ለፖለቲካ ፍጆታ በፈጠራ እንደሚያወሩት ባይሆንም በቊጥሩም ብዙ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ትክክለኛና ሙያዊ የሕዝብ ቈጠራ ቢደረግ የተደባለቀው ወይም ቅይጡ ሕዝብ ቀዳሚ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ በተለይም የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ከማናቸውም የኢትዮጵያ ነገዶችና ጐሣዎች በላቀ በታሪክ ሂደት በግዴታም ሆነ በውዴታ ተዋሕደዋል፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ሳይንሳዊ ምርመራ ቢደረግ ቦረናን ጨምሮ ንጹሕ የኦሮሞ ደም አለኝ የሚል ኢትዮጵያዊ የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ ይህ ለሌሎች ነገዶችና ጐሣዎችም የሚሠራ ይመስለኛል፡፡ ለዘር ፖለቲከኞቹ ለመናገር እንጂ ተውሕዶ፣ ተደባልቆ፣ ታጋምዶ ኢትዮጵያዊነት በሚባለው ብሔራዊ ማንነት ቀልጦ ለኖረው ኢትዮጵያዊ ይህ የማንነት ፖለቲካ ትርጕም የለውም፡፡

ኢትዮጵያ በሀገረ-መንግሥትነት ባሳለፈቻቸው በሺዎች የሚቈጠሩ ዓመታት እንደማናቸውም አገሮች በጎም ሆኑ መጥፎ ታሪኮች ተመዝገበውባታል፡፡ በጎውን የበለጠ አጎልብተንና አሁን ላለንበትም ጊዜ እንደሚጠቅመን አድርገን እየመነዘርን፤ መጥፎውን ደግሞ በማመንዠክና ለጥልና ልዩነት ምክንያት ሳናደርግ አርመንና አስተካክለን ዛሬን አዲስና እና ነገን የተሻለ አድርጎ ለመራመድ መጣር የትውልዱ ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡ ይህ የሠለጠነና የሺህ ዓመታት አኩሪ ታሪክ ያለው ሕዝብ መገለጫ ሊሆን ይገባል፡፡ አለመታደል ሆኖ ግን ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ባጠቃላይ፣ በሠላሳ አንድ ዓመታቱ በተለይ በሕዝባችን ውስጥ የበቀሉ እንክርዳዶች የሠለጠነውን፣ ጨዋውን፣ ርስ በርሱ ተከባብሮና ተደጋግፎ የኖረውን ሕዝብ አብሮነት ማናጋት ብቻ ሳይሆን በጥርጣሬና በጠላትነት እንዲተያይ ከማድረግ አልፎ የሕዝብ ደኅንነት እና የአገር ህልውና ከመቼውም ጊዜ በከፋ አደጋ ላይ እንዲወድቁ አድርገዋል፡፡ በዓለሙ ፊት አገራችንን እና ሕዝባችንን አዋርደዋል፡፡ ወሮበሎችና አላዋቆች በአገር ላይ ሲሠለጥኑ ከዚህ የተለየ ውጤት አይጠበቅም፡፡

በደመኛ የኢትዮጵያ ጠላት – ወያኔ ትግሬ ቤት – ከአንቀልባ እስከ ጉርምስና ዘረኝነትን እየተጋተ በኢትዮጵያ (በአማራው ሕዝብ) ጥላቻ ያደገው እና  ኦነግነትን በውስጡ ሸሽጎ የጎለመሰው ኦሕዴድ እንደ መንፈስና ግብር አባቱ ወያኔ (የትግራይን ሕዝብ ከአማራ ወንድሙና ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኑ እንዳቃቃረው ሁሉ) የኦሮሞን ሕዝብ ከኢትዮጵያዊ ማንነቱ ሊነጥለው ደፋ ቀናውን ከጀመረ እነሆ አራት የሰቈቃ ዓመታት ተቈጥረዋል፡፡ 

በነገራችን ላይ ‹ኦሮሙማ› በሚባለውና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አጥፍቶ ኦሮምያዊ አዲስ አገር ለመፍጠር በነ ዐቢይና ጀዋር በሚመራው ፕሮጀክት ውስጥ ቊጥራቸው ቀላል የማይባል የኦሮሞ ተወላጆች ተቀላቅለዋል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ የትግራይ ሕዝብን ዓይነት ዕጣ ፈንታ እንዳይገጥመው የሚለው ሥጋታችን ከዚህና ከተረኝነቱ አሰላለፍ በመነሳት ነው፡፡ ክፋትና ጥፋት በራሳችን ምርጫና ውሳኔ የሚመጡ እንጂ በስንፍናችን እግዚአብሔርን የምናማርርባቸው ጉዳዮች አለመሆናቸውን ማስተዋል ይገባል፡፡

በውኑ የኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ከቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኑ የተለየ ነውን? ታሪኩ፣ ባህሉ፣ ቋንቋው፣ ሃይማኖቱ፣ ማንነቱ እንዳይከበርና እንዳያድግ የሚፈልግ ማኅበረሰብ አለ ወይ? ነፃነቱ ተጠብቆ፣ መብቱ ተከብሮ፣ ፍትሕ አግኝቶ፣ በእኩልነት ታይቶ፣ ራሱን በራሱ አስተዳድሮ፣ ባንድ ኢትዮጵያ ጥላ ስር በጋራ ማደግና መልማት የማይፈልግ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አለ ወይ? ይህ እንዳይሆን እንቅፋት የሆኑ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም መሠረታዊ የምንላቸው፣ 1ኛ/ ግራ ገብቶአቸው ትውልዱን ግራ ያጋቡት፣ ባልገባቸው የተውሶ ርእዮተ ዓለም፣ በኢትዮጵያ የነገድ/የጐሣ ጭቆና ነበር (አንዱ ጐሣ ሌላውን ይጨቁነው ነበር) ‹‹ኢትዮጵያ የጐሣዎች እስር ቤት ናት›› የሚለውና  መሠረት የሌለው የተማሪ ፖለቲከኞች ወይም ‹ያ ትውልድ› የሚባለው የሐሰት ትርክት/አስተሳሰብ አንዱ ሲሆን፤ 2ኛ/ ላለፉት ሠላሳ አንድ ዓመታት ይህንን የውሸት ትርክት ሕጋዊና አስተዳደራዊ መዋቅር ሰጥተውት አጥብቀው እየሠሩ ያሉት ወያኔ ትግሬ – በመልኩና በአምሳሉ የፈጠራቸው ኢሕአዴግ በሚባለው የአጋንንት ማደሪያ ውስጥ የተሰባሰቡ ድርጅቶች – እና አሁን ደግሞ ወራሽ ተረኛው ኦሕዴድ-ኦነግ መሆኑ ከኦሮሞ ወገናችንም ሆነ ከቀረው ኢትዮጵያዊ የተሰወረ ነውን? ነፍሳቸውን በገነት በመንግሥተ ሰማያት ያኑርልንና ጋሼ መሥፍን ወ/ማርያም የጥላቻ ፖለቲካ በኢትዮጵያ እንዲነግሥ ያደረጉትን እነዚህን ጉዶች አሁንም እያመሱን ያሉና ‹‹በሽምግልና ውስጥ የተደበቁ ሸፍጠኛ ጎረምሶች›› ይሏቸዋል፡፡ እነሱ የገነቡት የጐሣ ሥርዓት እና ‹ክልል› የተባለ የጥል ግድግዳ አይደለም እንዴ አንዱ ማኅበረሰብ ሌላውን አትድረስብኝ ለማለት ያበቃው? በትክክል ለማስቀመጥ የአትድረሱብኝ አጥር የበገሩት ማኅበረሰቦች ሳይሆኑ በማኅበረሰቡ ውስጥ የመለያየት፣ የጥላቻና ቂም በቀል ትርክት ዘርተው እንክርዳዱን እያጨዱ ያሉት የጐሣ ሥርዓቱ ካድሬዎችና ሆዳም አድርባዮች ናቸው፡፡ የጐሣ አገዛዙ አለቆችም ሆናችሁ በኢትዮጵያና በተዋለደው ማኅብረሰብ ላይ ጥላቻ እንዲኖራቸው ኮትኩታችሁ ካሳደጋችኋቸው ጋጠ ወጥ ልጆች በስተቀር መላው የኦሮሞ ሕዝብ ዘረኝነትና ላገሩ ለኢትዮጵያ ጥላቻ የለውም፡፡ ከሌሎች ወንድሞችና እኅቶቹ ኢትዮጵያውያን ጋር በሰላምና በፍቅር አብሮ መኖር ነው የሚፈልገው፡፡ 

ለመሆኑ የኦሮሞ ሕዝብ፣

  • መቼ ነው ኢትዮጵያን አፍርሳችሁ በኢትዮጵያ መቃብር ላይ የኦሮሞ ግዛታዊ መንግሥት አቋቁሙልኝ ያላችሁ? ኢትዮጵያን ወያኔ ትናንት በፈጠረው ‹ኦሮሚያ› በሚባል ግዛት መልክና አምሳል በኦነጋዊ አስተሳሰብና ስሌት ፍጠሩልኝ ያላችሁ?
  • መቼ ነው አብሮ የገነባውን የኢትዮጵያን ታሪክ በሐሰት የፈጠራ ትርክት ለውጣችሁ አዲስ ታሪክ ጻፉልኝ ያላችሁ?
  • መቼ ነው ኢትዮጵያዊ እሤቶችን ሁሉ ንቅስ አድርጋችሁ አጥፍታችሁ በገዳ ሥርዓት ተኩልኝ ያላችሁ?
  • መቼ ነው ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማችንን ንቃችሁ፣ ቀድዳችሁና አቃጥላችሁ ከግብጽ በውሰት በመጣ ዓርማ ተኩልኝ፤ አረንጓዴ÷ ቢጫ÷ ቀዩን ሰንደቅ ዓላማ ይዞ የተገኘን ወይም በልዩ ልዩ መልኩ ያጌጠበትን እሰሩልኝ ግደሉልኝ ያላችሁ? መቼ ነው ልጆቻችንን የኢትዮጵያን ሕዝብ ብሔራዊ መዝሙር ሳይሆን በጥላቻ መንፈስ በኦሮምኛ ቋንቋ የተዘጋጀውን ‹መዝሙር› በተናጥል እንዲዘምሩ አድርጉልኝ ያላችሁ?
  • መቼ ነው ብሔራዊ ቅርሶችን በማንአለብኝነት አፍርሳችሁ አኖሌ የተባለ የጥላቻ ጣዖት አቁሙልኝ ያላችሁ?
  • መቼ ነው ብሔራዊ ቋንቋ አጥፍታችሁ በምትኩ ኦሮሚፋን በሌላው ሕዝብ ላይ በግድ ጫኑበት ያላችሁ? 
  • መቼ ነው የኢትዮጵያን ርእሰ ከተማ አዲስ አበባን ስም ከመቀየር ጀምሮ መላ ከተማዋን የኦሮሚያ ርስት አድርጉ፣ ሕዝቡም በመረጣቸው ነዋሪዎች ሳይሆን ያለፍላጎቱ በጉልበት በኦሕዴድ-ኦነግ ካድሬዎች በባርነት ይገዛ፣ ከነዋሪው ባልወጣ የፖሊስና የጸታ ኃይሎች ይቀጥቀጥ፣ ባጠቃላይ መብቱና ነፃነቱ ተገፎ በሁሉም ዘርፍ የኦሕዴድ ጭሰኛ ሆኖ ይኑር ብሎ ፈቃድ የሰጣችሁ?
  • መቼ ነው አማራውን ሕዝብ እያሳደዳችሁ በገባበት ገብታችሁ አርዳችሁ ሥጋውን ብሉት፣ ስቀሉት፣ ጨፍጭፉት፤ የዘር ማጽዳት፣ በሰብአዊ ክብር ላይ የሚፈጸምና የጦር ወንጀሎች ፈጽሙበት፤ በረሃብ አለንጋ ግረፉት፣ ተቅበዝባዥ አድርጉት፣ አዋርዱት፣ ከኢትዮጵያ ምድር አጥፉት ያላችሁ? መቼ ነው ህልውናውን ለማስጠበቅ፣ ራሱን ከጠላትና ከጥቃት ለመከላከል የያዘውን መሣሪያ ገድላችሁ ንጠቁት ያላችሁ?
  • ከአርባጉጉ፣ በደኖ፣ ወተር፣ ጉራ ፈርዳ አንሥቶ፤ በቡራዩ፣ በአ.አ.፣ በዝዋይ፣ በሻሸመኔ፣ በሲዳማ፣ ወላይታ፣ በጉራጌ፣ በአዋሳ፣ በጌድዎ፣ በድሬደዋ፣ በሐረር፣ በኮንሶ፣ በአማሮ፣ በባሌ፣ በወለጋ፣ በመተከል፣ ወዘተ የተፈጸሙትን ዘርና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ሰቅጣጭ ጭፍጨፋዎቸን የእኔን ጥቅም ለማስጠበቅ ስትሉ የፈጸማችሁት ነውና እሰየው እንኳን አደረጋችሁት ብሎአችኋል?
  • መቼ ነው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ የሆነውን ምእመን፣ ካህናትና መነኰሳት አሳድዱ ግደሉ፤ አድባራትንና ገዳማትን አቃጥሉ፣ ቅርሶቻቸውን ዝረፉ፣ ሥርዓተ አምልኮት መፈጸሚያ ነባር ቦታዎችን በዕብሪት ንጠቁ ያላችሁ? መቼ ነው በቤተክርስቲያኒቱ ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ ጉዳይ ጣልቃ ገብታችሁ የሕዝብ ባልሆኑ የጸታ ሠራተኞቻችሁና ካድሬዎቻችሁ አማካይነት ውክቢያ ፍጠሩ፣ ሰለም ንሱ ያላችሁ? 
  • መከላከያውን፣ ደኅንነቱን፣ ፖሊሱን፣ መገናኛ ብዙኃኑን፣ ቊልፍ የኢኮኖሚ ተቋማትን ለኦሕዴድ-ኦነግ ባደሩ ተረኞች ይሞሉ፤ የመንግሥት መ/ቤቶች ባለሥልጣናትም ሆኑ ተራ ሠራተኞች በአብዛኛው ሙያውና ችሎታው በሌላቸው ተረኞች ወይም አድርባዮች ተሞልተው ሌላው የበዪ ተመልካች ይሁን ያላችሁ መቼ ነው?
  • ወያኔ በለኮሰውና አገዛዙ በተንኮልና በሸፍጥ በመራው ጦርነት ምክንያት ንጹሐን ኢትዮጵያውያን በተለይም የአፋርና የአማራ ተወላጆች ያለምንም ፍዳቸው እንዲያልቁ ስታደርጉ፤ መሠረተ ልማቶችና የሕዝብ ተቋማት ሲወድሙ፣ አገዛዙ ባሰማራቸው ሽብርተኞች ምክንያት ሕዝብ ሲያልቅና በሚሊዮኖች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው አውላላ ሜዳ ላይ ያለምንም ረዳት እንዲቀሩ ስታደርጉ፤ ሕዝብ አገዛዝ-ወለድ በሆነ የኑሮ ውድነት ቁም ስቅሉን እያየ እናንተ ‹‹መናፈሻ›› ስትገነቡና ድግስ እየደገሳችሁ ስትምነሸነሹ ቆመንለታል የምትሉትና በስሙ የምትነግዱበት ሕዝብ ለእኔ ጥቅም ነው ብሎ ቡራኬ ሰጥቷችኋል?
  • ለኢትዮጵያ የብሔራዊ በዓላት ሁሉ በኵር የሆነው፣ ለአፍሪቃውያንና ለመላ ጥቁር ሕዝቦች ደግሞ የነፃነት ተምሳሌት የሆነውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በአፄ ምንይልክ ዐደባባይ እንዳይከበርና እንዲደበዝዝ፣ ታሪኩንም ለማዛባት በተደጋጋሚ በአገዛዙ ኦሕዴድ የተደረጉ ሙከራዎች፤ ለበዓሉ የሚታደመውንም ሕዝብ ከዛቻ ጀምሮ ድብደባ፣ እስርና ግድያ እስከመፈጸም የደረሱ ክስተቶች ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር የታሪኩ ተካፋይ የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎት ነው?

ዝርዝሩ ማብቂያ የለውም፡፡ ባጭሩ ከፍ ብለን ለአብነት የዘረዘርናቸው በኢትዮጵያ ምድር የሚታዩ መራር እውነታዎች አገዛዙ በኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚነግድባቸው ድርጊቶች እንጂ የአብዛኛው ኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎት አይደሉም፡፡ ምንም እንኳን በባለጊዜነት ለትውልድ የሚተርፍ ቁርሾ ቢተዉም፣ ነገ የሚያልፉ አገዛዞችን ሳይሆን ዘላቂውን አገርና ሕዝብ መመልከት ዘመናትን ላስቆጠረው አብሮነታችንና አንድነታችን ጠቃሚ ይሆናል፡፡

አንዱን ወይም ሌላኛውን የኢትዮጵያ ግዛት እርሱ የተወለደባትን አነስተኛ የገጠር መንደር ‹‹ በሻሻን›› አደርጋለሁ (አውድሜ ወደ ኋላ ቀርነት እመልሳለሁ) እያለ በንቀት፣ በጥላቻና በቅጣት መንፈስ የሚፎክር አቅሉን የሳተ ግለሰብ እንኳን ዐባይ ሀገር ኢትዮጵያን፣ በጐሠኞቹ ቋንቋ በከፊል በደም እዛመደዋለሁ የሚለውን የኦሮሞን ማኅበረሰብ በፍጹም የሚመጥን አይደለም፡፡ ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ እኛ ዝኆን ነን ሌላው ‹አይጥ› ነው የሚለውን የጐሣ አለቃ አይፈልግም፡፡ የመንፈስ አባቱ እኛ ወርቅ ነን ቀሪው ….ነው እንዳለው፤ ያለ ዘረኝነትን የሚሰማ ዦሮ የለውም፡፡

እናስተውል! አንድ ሕዝብ እንደ ፈጠራ ሥራ ውጤት የ‹‹ቅጅ መብት/ኮፒ ራይት›› ወይም እንደ አእምሮአዊ ንብረት የ‹‹ፈጠራ ባለቤትነት መብት/ፓተንት›› ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት የሚሰጥ ግዑዝ ‹ንብረት› አይደለም፡፡

Filed in: Amharic