አገር እንዲኖረን!?
አንዱ ዓለም ተፈራ
አገራችን ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ብዙ ፈተናዎችን አስተናግዳለች። በዚህ ፈተናዋ፤ በጎና በጎ ያልሆኑ ድርጊቶች ተከስተዋል። ሁላችን ኢትዮጵያዊያን በያለንበት አጥብቀን የምንፈገው፤ አገራችን አገር ሆና እንድትቀጥል ነው። አገራችን አገር ሆና እንድትቀጥል፤ መሠረታዊ የሆኑ አገር አቀፍ ዕሴቶች በቦታው መኖር አለባቸው። ለኔ እኒህ ዕሴቶች እየተሸረሸሩና ኢትዮጵያ አገር ሆና እንዳትቀጥል የሚያስተናግዱ ሂደቶች ይታዩኛል። ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት እንደሆነ፤ የተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም እየሠጡት ነው። የኢትዮጵያ ዕሴቶች ተቦርቡረው፤ ፈላጊ እንደሌላቸው ዕቃዎች የትም እየተጣሉ ነው። እንደ አንድ ሕዝብ እና እንደ አንድ አገር የሚያስተሳስረን የአገር አንድነት እምነቱ ከሌለን፤ በምን ሂስብ ኢትዮጵያ አንድ አገር ሆና ትቀጥላለች! ኢትዮጵያዊነትስ ምን ትርጉም ያለው ግንዛቤ ነው! ይህ ነው የዚህ ጽሑፍ ትኩረት።
ኢትዮጵያዊነት፤ ባለሥልጣናትና በፖለቲካ የሚሳተፉ ሰዎች ብቻ የግል ባለቤት ሆነው የያዙትና ትርጉም የሚሠጡት ማንነት አይደለም። ኢትዮጵያዊነት፤ የርስዎ፣ ያንቺ፣ ያንተና የኔ የአገር ባለቤትነታችን መገለጫ ነው። ኢትዮጵያዊያን ግለሰቦች፤ በኢትዮጵያዊነታቸው፤ የትም የኢትዮጵያ መሬት ላይ፤ በኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ፤ መኖር፣ ሀብት ማፍራት፣ በአካባቢውና በአገር አቀፍ ደረጃ በኅብረተሰቡ ማንኛውም ክንውን የመሳተፍ መብት አላቸው። ከኢትዮጵያ ውጪ ሲሄዱም፤ የኢትዮጵያዊነት መታወቂያ ፓስፖርታቸውን ይዘው፤ በኢትዮጵያዊነታቸው ተከብረው ይስተናገዳሉ። ከዚያ ውጪ፤ የሚናገሩት ቋንቋ፣ የተወለዱበት መንደር፣ የሚያመልኩት ፈጣሪ፣ በሰውነታቸው ውስጥ የሚዘዋወረው ደም የትውልድ ሐረግ፣ ወይንም የፖለቲካ እምነታቸውን ማራመጃ ፓርቲያቸው፤ ኢትዮጵያዊነታቸውን አይወስንም። ኢትዮጵያዊያን፤ በአገራችን ኢትዮጵያና በየቦታውና በየጊዜው ኢትዮጵያዊያን በሚተገብሩት ነው የምንኮራው። ዛሬ ጠባብ በሆነ የአካባቢ አንድ ጉዳይ ተጠምደን፤ የአገርን ምንነትና ሂደት ከዚያ ጉዳያችን አንጻር ብቻ ከተረጎምን፤ ኢትዮጵያዊነታችን ይሟሽሻል፣ አብሮነቱ ይሻግታል፣ ቆይቶም ይጣላል። ለዚህ ሁሉ ማዕከል ሆኖ የሚሾፍረው፤ የአገሪቱን የፖለቲካ ሥልጣን የተረከበው ፓርቲ ነው። ይህ ፓርቲ አገራዊ አጀንዳ ያለው ሊሆን ይገባል። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የብልፅግና ፓርቲ፤ አገራዊ እምነትና ዓላማ ያለው ሆኖ አላገኘሁትም። ከአዲስነትና ከለውጥ ይልቅ፤ የትግሬዎች ነጻ አውጪ ግንባር መሪዎችን መለወጥ እንጂ፤ የነበረውን የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ የሚያጠናክር ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ለውጡ የጉልቻ ብቻ ሆኗል።
ኢትዮጵያዊነትን ካላጠበቅን፤ ከፊሎችን ብቻ የያዘ የ“እኔ”ና የ“ሌሎች” የምንለው ማንነት ላይ ከተጠመድን፤ ንቁ የአገር ተቆርቋሪነታችንና የፖለቲካ ተሳትፏችን ፋይዳ ቢስ ይሆናል። ኢትዮጵያዊነት፤ ኢትዮጵያዊያን በትጋት የምንጠብቀው የየግል ማንነታችን ነው። ንቁ ሆነን ኢትዮጵያዊነታችንን ካላከበርነውና ሌሎች እንዲተረጉሙልን አሳልፈን ከሠጠናቸው፤ የኛ ኢትዮጵያዊነት ዋጋ ያጣል። እኔ አገር ቤት ውስጥ ኖርኩም ከአገሬ ውጪ፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ። በኢትዮጵያዊነቴ ኢትዮጵያዊ ግዴታ አለብኝ። ኢትዮጵያዊ መብትም አለኝ። የመጣ የሄደ ባለሥልጣን አይወስንልኝም። ይህ እንግዲህ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚካሄደው የፖለቲካ፣ የአስተዳደር፣ የፍትኅ፣ የረሃብም ሆነ የሥልጣኔ ክንውን፤ የምችለውን እንዳደርግ ይገፋፋኛል። በአንጻሩ ደግሞ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው አገር አፍራሽ ክንውን እንድቃወም ያሳስበኛል። የምነሳው ከዚህ ነው።
በየጊዜው የተለያዩ የፖለቲካ አካላት መንግሥታዊ ሥልጣኑን በመጨበጥ፤ የየራሳቸውን እምነትና የግል ፍላጎት ማሟያ ፍልስፍናና መመሪያ አስቀምጠው፤ የቡድንና የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም ገፍተዋል። ይሄ ሂደት አሁን ካለንበት ቦታ ጥሎናል። ያለንበት ቦታ ቀዝቃዛና አደገኛ ነው። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ጥሎልን የሂደው ከፋፋይና አገር አፍራሽ የፖለቲካ ሥርዓት አሁንም አፈርጥሞ እግሩን እንደሰደደ ነው። አገር አፍራሹ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የፖለቲካ ፍልስፍና፤ እንዳለ ነው። አገር የማፈራረስ ሂደቱ ቀጥሏል። ይሄ ባለበት፤ ነገ አገር አይኖረንም። ይሄ ግምት ሳይሆን፤ አይቀሬ እውነታ ነው። እንዲህ አርቀን ማየትና ማሰብ ካቃተን፤ ለነገ ተኪ ኢትዮጵያዊያን አይኖሩንም። ነገ ኢትዮጵያዊያን ከሌሉ፤ ነገ ኢትዮጵያ የለችም! ይሄን የአገር ጉዳይ በተደጋጋሚ የምቆረቆርለትና እያደመቅሁ የማዜምለት፤ ከትናንቶቹ የተረከብኩት ኢትዮጵያዊነት፤ ለነገዎቹ ይሄንኑ እንዳስረክባቸው ሳያሰልስ ስለሚጎተጉተኝ ነው።
የአገር ጉዳይ እንቅልፍ ይነሳል! ሕይወት ይጠይቃል! ገንቢም ሆነ አፍራሽ፤ የትናንቱ ሥርዓት አለፈ። ዛሬ በአገራችን ላይ ያለውን የመንግሥት ሥልጣን ባለቤት የፖለቲካ ፍልስፍና መጠየቅ ግዴታችን ነው! ምን ያህል የአገራችንን የነገ ሕልውና ጥበቃ እያካሄደ ነው? ይሄን መጠየቁ አስፈላጊ የሚሆነው፤ ነገ ምን ዓይነት አገር እንደምትኖረን ስለሚነግረን ነው። የትናንቱ አገር አፍራሾች፤ ነገ በታሪክ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን፤ ዛሬም በሕግ ፊት መቅረብ አለባቸው! ይህ ደግሞ በግለሰቦች ማንነት ሳይሆን፤ በአድራጎታቸው ነው። ታዲያ ዛሬ ያንኑ የሚያከናውኑስ መጠየቅ የለባቸውም? አሁን በአገራችን ላይ ያለው የመንግሥቱ ሥልጣን ባለቤቶች የፖለቲካ አካሄድ፤ አገራዊ ጉዳይ ተቆርቋሪነቱ እንዲጠፋና የአካባቢ ጉዳይ ተቆርቋሪነት እንዲለመልም አድራጊ ነው። እንዳለፉት ሁሉ! የማንኛውም የብልፅግና ፓርቲ ባለሥልጣን ጥረት፤ ለኢትዮጵያውያን የሚጠቅምና የሚረዳ ሳይሆን፣ ለግል በሆነ ጉዳይ ላይ ብቻ ማተኮር ሆኗል። በዚህ ሂሳብ፤ ቀጣዩን ትውልድ በኢትዮጵያዊነቱ እንዲኮራና ኢትዮጵያን ከተቀበላት አበልጥጎና አዘምኖ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲያስተላልፈፍ እያደረገ አይደለም።
ኢትዮጵያዊነት የሚበለጥገው፤ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ዕሴቶች በአገር ደረጃ ሲኖሩ ነው። እኒህ ደግሞ ሲያብቡና ሲደምቁ፣ በኒህ ላይ የኔ ባይነትና መኩራት ሲኖር ነው። በአሁኑ ሰዓት፤ የብልፅግና መሪዎች፤ ከኢትዮጵያዊነታቸው ይልቅ በአካባቢያቸው ላይ ተጠምደዋል። ከፖለቲካው ውጪ ያሉት ደግሞ፤ ፖለቲካውን ለባለሥልጣናቱ አስረክበው፤ በግል ኑሯችን ላይ እየተሯሯጡ ነው። መሪዎቹ ሥልጣናቸውን ለራሳቸውና ለሚደግፋቸው መጥቀሚያ እያደረጉት ነው። ይህ አደገኛ ጉዞ ነው።
ከወያኔ በፊት በፖለቲካው ዙሪያ የነበርን፤ ኢትዮጵያዊነት ስንል፤ በአገር ደረጃ አንድነታችን ላይ በማተኮር ነበር። ቀደም ሲል የፖለቲካ በደል አልነበረም ወይንም ጥፋት አልተሠራም የሚል የተሳሳተ ነው። አገርና ማንነት ግን፤ ያኔም ሆነ አሁን አንድ ነው። ልዩነቱ፤ አሁን ይሄንን እውነታ የሚለውጥ የፖለቲካ ሥርዓት ባገር ላይ መንገሡ ነው። ያለፈው የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት አገር አፍራሽ ድርጊቶችን ፈጽሟል። ሰዎችን ከኢትዮጵያዊነት አውጥቶ ወደ ጠባብ የአካባቢ ማንነት መንዳቱ፤ ለትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የሥልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ መንገድ ሆኖለት ነበር! በሂደቱ ሕዝቡ በሥርዓቱ ብቻ ሳይሆን፣ በወደፊቱ ኑሮው ላይ እምነት እንዲያጣ ተደርጎ ነበር። “አሁን ተረኛ እኔ ነኝና እነሱ ያደረጉትን ላድርግ!” ማለት፤ ፀረ-ኢትዮጵያዊነት እና አገር አጥፊነት ነው። አዎ! በሥልጣን ላይ የሚወጡ የፖለቲካ አካላት፤ አጀንዳቸውን ለማራመድ፣ የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ አውጥተው ይገፋሉ። የነሱ የፖለቲካ ፍላጎትና የአስተዳደር አሠራር ሂደት፤ ቀጣዩን የነገ የአገር ሕልውና ጥያቄ ላይ ማስቀመጥ የለበትም። አገርና የአገር ሕልውና፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ፍላጎትና የዕለት ተዕለት ተግባር የላቀና የበላይ ነው። የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤቶች ለአገር መቆርቆር ካቆሙ፤ ይህ የአገር ማፍረስ አደጋ እየከፋ ይሄዳል። ለፖለቲካ ተሳታፊ፤ ለአገር መቆርቆር ማለት፤ የአገር ባለቤት መሆንን አጥብቆ መያዝ ማለት ነው።
አገር ከሌለ፤ እንደ ሕዝብ የመኖር ሕልውና ከፍተኛ አደጋ ይጋረጠዋል። አገር ሳይኖር ፖለቲካም ሆነ ሀብት ምንም ትርጉም እንደሌለው ከዩክሬን መማር አለብን። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በአማራውና አፋሩ ላይ ያደረገው ወረራ፤ ሩስያ በዩክሬን ላይ ካደረገችው ወረራ ጋር ብዙ የሚያመሳስሉት ነገሮች አሉበት። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ወልቃይትንና ራያን የኔ ነው እንዳለው ሁሉ፤ ሩስያ ደግሞ የሩስያ ዝርያ ያላቸው ዩክሬናዊያን ያሉበት ቦታ ሁሉ የኔ ነው አለች። ሁለቱም ኃይሎች አረመኔያዊ ተግባርን በቦታው ባሉት ነዋሪዎች ላይ ፈጽመዋል። ለመግለጥ እንኳን የሚዘገንን ጨካኝ ጭፍጨፋ አካሂደዋል።
ኢትዮጵያ የምትፈራርሰውና ኢትዮጵያዊነት የሚጠፋው፤ ኢትዮጵያዊ አጀንዳ በመንግሥት ደረጃ ባለመካሄዱ ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያዊያን ለአንድ ኢትዮጵያ ሕዝብና ለአንድ ኢትዮጵያ አገር ተቆርቋሪዎች ዝም ብለው ሲመለከቱ ነው። የኢትዮያዊያን ዝምታ ኢትዮጵያን ያፈርሳታል። ኢትዮጵያዊ ያልሆነ አጀንዳ ያለው አካል በሥልጣን ላይ ከተቀመጠ፤ ኢትዮጵያ የሚባል አገር ነገ አይኖርም። የተወሰኑት ተጠቃሚና በልጣጊ፤ ሌሎች ደግሞ ተሳታፊ ያልሆኑ የእንጀራ ልጆች በሆኑባት አገር፤ ሰላም፣ ልማት፣ ብልፅግና ይኖራል ማለት ዘበት ነው። በተለይም በአማራው ሕዝብ ላይ እየተደረገ ያለው በደል፤ ዘግናኝና አገር በታኝ ነው። ይህ በትግሬዎች ነፃ አውጪ የተቀመጠው፤ “አማራው ጨቋኝ ነበር? እናም አሁን መጨቆን አለበት!” የሚለው የፖለቲካ ፍልስፍና፤ ዛሬም ባለበት እንደቀጠለ ነው። በዚህ ሂደት አገርን አገር አድርጎ ማስቀጠል አይቻልም። “አንተ አማራ ነህና ዝም ብለህ የምንልህን አድርግ! የምንሾምልህን ተቀበል! ለምንወክልልህ ስገድ!” አገር አይገነባም።
በመሠረቱ ይሄንን የአማራ ሕዝብ አልተቀበለውም። እናም ይሄንን ሊቃወም የሚገባው ራሱ አማራው ነው። አማራነት ወንጀል አይደለም! አማራው፤ “በአማራነቴ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነቴ ነው በአገሬ የፖለቲካ ሂደት የምሳተፈው!” በማለት መቆም አለበት። በየትኛውም ክልል የሚኖር አማራ፤ በኢትዮጵያዊነቱ በማንኛውም ኅብረተሰባዊ ግንኙነቶች እኩል የመሳተፍ መብት አለው። ይሄ ግን የሚረጋገጠው፤ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ-መንግሥት ሙሉ በሙሉ ተሰርዞ፤ ኢትዮጵያዊ የሆነና ሁሉን ኢትዮጵያዊያን፤ በኢትዮጵያዊነት ብቻ፤ አንድ አድርጎ የሚያስቀምጥ ሲተካበት ነው። አማራ የሚባል የፖለቲካ አካል የለም! አማራ የትውልድ ጉዳይ ነው። ኦሮሞም፣ ትግሬም፣ አፋርም፣ ሲዳማም፣ ሶማሌም፣ አዲስ አበቤም፣ ሌላም እንዲሁ! ኢትዮጵያዊነት ደግሞ የአገር ባለቤትነት ጉዳይ ነው። አማራ፤ “በኢትዮጵያዊነቴ መከበር አለብኝ! ሰንደቅ ዓለማዬ አረንጓዴ ብጫ ቀይ ቀለም ብቻ ያለበት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ነው!” ማለት አለበት። “የአማራ ሰንደቅ ዓላማ የለም!” ማለት አለበት። ያን ጊዜ ብቻ ነው በኢትዮጵያዊነቱ በአገሩ ተከብሮ መኖር የሚችለው። ይህ ደግሞ፤ ለሌሎችም ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ነው።