>

አምንስቲ ላይ መወሰድ ያለበት ቀጣይ እርምጃ (መስፍን አረጋ)

አምንስቲ ላይ  መወሰድ ያለበት  ቀጣይ እርምጃ

መስፍን አረጋ


አምንስቲ ኢንተርናሽናል (Amnesty International) በወልቃይት ላይ ያቀረበው ከወያኔወች የበለጠ ወያኔያዊ አጭቤ ዘገባ (fake report) የአማራን ሕዝብ ክፉኛ እንዳስቆጣ ተገንዝቧል፡፡  ስለዚህም፣ ዓላማውን ሳይሆን ዘዴውን ይለውጣል፡፡  የአንግሊዝን መሠሪነት በደንብ ማወቅ የሚገባው እዚህ ላይ ነው፡፡  እንግሊዝ ኃይል ስታሳየው የሚጥመለመል፣ የተዳከምክ ስትመስለው የሚናደፍ ዕባብ ነው፡፡  

የእንግሊዙ አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ በዘገባው የተቆጣውን የአማራ ሕዝብ ለመደለል ሲል ወያኔና ኦነግ በአማራ ሕዝብ ላይ ስለፈጸሙት ወንጀል በገደምዳሜ የሚጠቅስ ዘገባ ቢጤ በቅርብ ቀን ውስጥ እንደሚያወጣ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡  ይህ የሚያደርገው ግን በአማራ ሕዝብ ላይ ስለተፈጸመው ዘርተኮር ጭፍጨፋ ለማውሳት አስቦ ሳይሆን፣ ሚዛናዊ በመምሰል በወልቃይት ላይ ያወጣውን ዘገባ የበለጠ ክብደት ለመስጠት ነው፡፡   

ስለዚህም የአማራ ክልል አመራሮች፣ ለአማራ ሕዝብ ብለው ሳይሆን፣ ለራሳቸው ቆዳ ሲሉ የአምንስቲን ቀጣይ ሴራ ከወዲሁ ማክሸፍ አለባቸው፡፡  በአማራ ላይ ስለተፈጸሙ ጥቃቶች መረጃወችን ስጡኝ ሲላቸው፣ እኛ የራሳችን የሰብኣዊ መብት ድርጅት አለን፣ አንተ ምን ቤት ነህ፣ የአፍሪቃውያን የሰብኣዊ መብት ጠበቃ አድርጎ የሾመህ ማነው፣ …. በማለት አብጠልጥለው መመለስ አለባቸው፡፡  (ይህን ስል ግን የአምንስቲን ፀራማራ ዓላማ ለማክሸፍ እንጅ፣ ኦነጋውያን በበላይነት የሚቆጣጠሩትን የጦቢያን ሰብዓዊ መብት ድርጅት በማመን እንዳልሆነ አንባቢ እንዲረዳልኝ እፈልጋለሁ፡፡)

 አምንስቲ እና አምንስቲን የመሰሉ በሰበኣዊ መብትና በዲሞክራሲ ሰበብ የምዕራባውያንን አጀንዳ ለማራመድ የተቋቋሙ ድርጅቶች የሚያቀርቧቸው ዘገባወች ተዓማኒነት ሊኖራቸው የቻለው፣ መዋሸት በሚፈልጉት ውሸት ላይ ከአፍሪቃውያን መንግሥታት የሚያገኟቸውን መረጃወች እዚህም እዚያም ጣል፣ ጣል በማድረግ ውሸታቸውን ወደ ግማሽ ውነት (half-truth) ስለሚለውጡት ነው፡፡  ስለዚህም እነዚህን መሠሪ ድርጅቶች እርቃናቸውን ማውጣት የሚቻለው ከነሱ ጋር አለመተባበር ብቻ ሳይሆን ጭራሹንም አናውቃችሁም በማለት ነው፡፡       

መስፍን አረጋ mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic