>

የአዴፓ አመራሮች ጥበቃ መነሳቱ በቀጣይ ምን እንደታሰበባቸው አመላካች ነው...!!! (መስከረም አበራ)

የአዴፓ አመራሮች ጥበቃ መነሳቱ በቀጣይ ምን እንደታሰበባቸው አመላካች ነው…!!!
መስከረም አበራ

*…. ኦህዴድ በጌትነቱ ላይ የተጋረጡ እንቅፋቶች አድርጎ የቆጠራቸውን የአማራ ብልፅግና ባለስልጣናት ጥበቃቸውን ያነሳው በህዝብ ዘንድ ያለውን “Reaction”  ለመለካት ነው፡፡ ይህን ከለካ በኋላ በሰዎቹ ላይ የሚወስደው እርምጃ ቀላል ይሆናል፡፡በነዚህ ሰዎች ላይ የሚወሰደውን የበቀል እርምጃ ዝም ብለን የምናይ ከሆነ ጭራሽም ይበላቸው የምንል ከሆነ  አንድ በአንድ አስበልተን …!!!
 
*….  ስልጣን ስላጡ ህዝቤን ማለት እና ህዝቤን ስላሉ ስልጣን ማጣት እጅግ የተለያዩ ነገሮች ናቸው….!
በአሁኑ ወቅት የአማራ ህዝብ ያለበት አደጋ እስከዛሬ በተሄደበት መንገድ ተሂዶ የሚፈታ አይደለም፡፡ የቀድሞው ያዝ ለቀቅ፣የቀድሞው ቸልታ፣የኖርንበት የይሉኝታ እና ከእኔ ይቅር ጉዞ፣ በውሃ ቀጠነ መባላት፣በደልን ብቻ መቁጠር የህዝቡን መከራ ያብሳል እንጅ የሚጨምረው ነገር የለም፡፡ይህን መከረኛ ህዝብ ከተደቀነበት የህልውና ፈተና ለመታደግ የተለየ ስልት፣የተለየ አተያይ፣የተለየ ሆደሰፊነት፣ብልህነት፣አርቆ አሳቢነት ይፈልጋል፡፡አሁን ሃይል ማሰባሰቢያ እንጅ በሰበብ አስባቡ መለያያ አይደለም፡፡
አማራውን ለማድማት ሲሆን የማይታረቅ ጠበኛ እንደሌለ ራቅ ካልን በኦነግና ህወሃት ስምምነት  ፤ከሰሞኑ ደግሞ የኦህዴድ፣ኦፌኮ መግለጫ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ በሃገሪቱ ያለው ተጣላሁ ባይ የዘውግ ፖለቲካ ሃይል ሁሉ ያለ ማንገራገር የሚታረቀው አማራ ቀና ያለ ሲመስለው ነው፡፡ እነዚህ ሃይሎች የሚታረቁት፣አማራውን ወደ ማሳደዱ ዘላላማዊ የፖለቲካ ግባቸው ለመንጎድ ተጣጥመው በማያውቁት ሁኔታ የሚጣጣሙት ከዚህ በፊት ተጣልተው ስለማያውቁ ወይም ወደ ፊት በፍፁም ልንጣላ አንችልም ተባብለው ተማምለው አይደለም-ያለፈውን ጠብ የሚያስረሳ የሚመጣውንም የቢሆን ጠብ  ችላ የሚያስብልአንገብጋቢጉዳይ ገጥሞናል ብለው ስላሰቡ እንጅ! ይህ ነው በአማራው ጎራ የሌለው አማራ ጠሉ የዘውግ ፖለቲካ  ጎራ ብልሃት!  ጠላቴ የሚለውን አማራውን እየመላለሰ እንዲያሳድድ የረዳውም ይሄው ብልሃቱ ነው!
በአማራው በኩልስ? ልምዱ ግልፅ ነው! ለክለሳ ያልተዘጋጀ በደልን ቆጣሪ አካሄድ፣አምራሪነት፣በፖለቲካ ወዳጅነት/ባለጋራነት ዘላለማዊ እንዳልሆነ ያለመረዳት  ይበዛል፡፡
የአማራን ህዝብ መከራ እያባባሰ በማራዘሙ በኩል የአማራ ልሂቃን አውቀውም ሆነ ሳያውቁ  የሚጫወቱት ሚና ትልቅ ነው/ነበር፡፡ ሆኖም እነዚህ ልሂቃን ነገሩ ገብቷቸው ልመለስ ሲሉ የቆየውን ፋይል አቧራ እያራገፉ ጦር ይዞ መጠበቅ ብልህነት አይደለም፡፡ ብልሁ መንገድ እጅግም ሳይጨፍሩ ተመላሽ ወገኖችን እንኳን ደህና መጣችሁ ማለቱ ነው፡፡ በተለይ ከብአዴን ጎራ የሚያፈነግጡ መሪዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ ማለቱ ምትክ የሌለው የብልህ መንገድ ነው፡፡ ሲያደርጉን የነበሩት ምናምን የሚለውን ወቀሳ ለመነጋገር በርካታ ቀናት ከፊት አሉ፡፡ አሁን ግን የእነዚህ ሰዎች ከበአዴን ጎራ በማንኛውም መጠን ማፈንገጥ ትግሉን በከፍተኛ ሁኔታ ያግዛል፡፡
ስናወግዛቸው ለነበሩ መኳንንት ፍንገጣ የምናሳየው “Reaction” የብአዴን ጎራ እንዲሳሳ ወይ በአሽከርነቱ ተጠናክሮ ህዝባችንን በማሳረዱ እንዲቀጥል አስተዋፅኦው ትልቅ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ በብአዴን ውስጥ ያሉ እኛ የምንፈርድባቸው ግን እንደ እኛው የአማራ ህዝብ ውርደት የሚያንገበግባቸው፣ በሁለት ጦር የሚወጉ ሰዎች (ጥቂት ቢሆኑም) እንዳሉ አስረግጨ ልነግራችሁ እወዳለሁ፡፡ ትናንት ጥበቃቸውን ያነሳው ኦህዴድ በእነዚህ ሰዎች ላይ የጀመረውን ካልገዛኋችሁ አትኖሯትም የሚል አካሄድ ከቀጠለ ከሰዎቹ ጋር ለምን እዚህ ደረጃ እንደደረሰ የማውቀውን ሁሉ ለሚሰማ  ለማሳወቅ እገደዳለሁ፡፡እነዚህ አፈንጋጭ ሰዎች ወደ ቀደመው የብአዴን ባርነት አንመለስም ብለው  ስለ ህዝባቸው በሞገቱ ቁጥር “የትኛው ህዝባችሁ ይሄ እንትን የነካው እንጨት ያደረጋችሁ?” እየተባሉ ነው የኖሩት፡፡
 አሁንም እኛም ጦር ይዘን እንደምንጠብቃቸው እያወቁ ነው ከኦህዴድ ጋር እዚህ ደረጃ የተዳረሱት……. ኦህዴድ በጌትነቱ ላይ የተጋረጡ እንቅፋቶች አድርጎ የቆጠራቸውን የአማራ ብልፅግና ባለስልጣናት ጥበቃቸውን ያነሳው በህዝብ ዘንድ ያለውን “Reaction”  ለመለካት ነው፡፡ ይህን ከለካ በኋላ በሰዎቹ ላይ የሚወስደው እርምጃ ቀላል ይሆናል፡፡በነዚህ ሰዎች ላይ የሚወሰደውን የበቀል እርምጃ ዝም ብለን የምናይ ከሆነ ጭራሽም ይበላቸው የምንል ከሆነ ብአዴን ውስጥ ሆኖ ስለ አማራ ህዝብ ችግር መቃተት ከሁለት ያጣ እንደሚያደርግ  የሚሰማው ሌላ ወገን እንዳይመጣ በማድረግ ብአዴንም መድህኑ አሽከርነቱ ብቻ እንደሆነ አውቆ ያለምንም አፈንጋጭ በየቀኑ በሚጨምር የባርነት ሙላት ያገለግላል ማለት ነው፡፡
አብዛኞቻችን እንደተለመደው “ስልጣኑን ሲያጣ ነው የአማራ ህዝብ ትዝ የሚለው?” የሚለውን የተለመደ ገፍታሪ ፍርዳችንን ይዘን እንደምንጠብቅ ይታወቃል፡፡ መርሳት የሌለብን ነገር ግን የአማራ ህዝብ ስቃይ ትዝ ስላለው ስልጣን ያጣም እንደሚኖር ነው፡፡ ስልጣን ስላጡ ህዝቤን ማለት እና ህዝቤን ስላሉ ስልጣን ማጣት እጅግ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ በብአዴን እና በኦህዴድ መስተጋብር ደግሞ ብአዴኖችን ስልጣን የሚያሳጣው ብቸኛው ነገር ህዝቤን ማለት እንደሆነና በስልጣን ለመሰንበት ከፍ ከፍም ለማለት ደግሞ  ቆምኩለት ያሉትን ህዝብ ማሳደድ እንደሆነ ተመስገን ጥሩነህን ማየት በቂ ነው፡፡
Filed in: Amharic