>

ክቡርነትዎ ሀገር ይምሩ ስንልዎ ሰፈር ካልመራሁ አይበሉን...!!!  (ሳምሶን ሚካኤሎቪች)

ክቡርነትዎ ሀገር ይምሩ ስንልዎ ሰፈር ካልመራሁ አይበሉን…!!! 
ሳምሶን ሚካኤሎቪች

በቀድሞዎቹ ገዢዎቻችን ህወሃቶችና በአሁኖች የሀገር መሪዎች ብልጽግናዎች መሀከል ካሉት ትልቅ ልዩነቶች መሀክል ህወሃቶች ከአድዋም ይምጡ አዲግራት ህልማቸው ሀገር መምራት ነበር። እንዲያውም ሰዎቹ ከሀገር አልፈው የአፍሪቃ ቀንድ መሪዎች ነበሩ። የዛሬዎቹ መሪዎቻችን ኢትዮጵያን ያህል ትልቅ ሀገር ምሩ ስንል አጨብጭበን እንካችሁ ብለን እነርሱ የለም ኦሮሚያን ካልመራን ብለው የልጅነት ህልማቸው ላይ ተቸንክረው አሉ።
ስንዴ ማሳ ሲገማሸሩ አይተን በርቱ ያልናቸው አቦ ሽመልስ አብዲሳ የእነዚህ ከቀበሌ በላይ ማሰብ ከተሰናቸው የብልጽግና አመራሮች መሀከል ዋናው ምናልባትም ጠቅላይ ሚኒስትሩም ተጨምረውበት የቡድኑ አጋፋሪ የሆኑ ይመስላል ። ሽመልስ አብዲሳ በተደጋጋሚ አዲስአበባን irrelevant እናደርጋታለን ፣ የትግል አጋሮቻቸውን የአማራ አመራሮች confuse & convince እያደረግን የኦሮሞን ጥቅም እናስጠብቃለን ሲሉ ተደምጠዋል።
የሽመልስ አብዲሳን ቃለመጠይቆች ስሰማ አንዳንድ ጉዳዮች ወደ አዕምሮዬ ይመላለሳሉ ። 
፩. ሰውየው ነገ የሚኒስትርነት አልያም የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመት ቢያገኙ ያንኑ oromia first የሚለውን ርዕዮታቸውን ሊያስቀጥሉ ነው ? የፖለቲካ ህልማቸውስ ከክልል ሊቀማንበርነት አይዘል ይሆን ? በአፍሪካ አልያም አለም አቀፍ ደረጃ ሹመት ቢያገኙ እርሳቸውም እንደ ቴዎድሮስ አድሀኖም ለብሄራቸው ጥቅም ሊሟገቱ ነውን ?
፪. የዛሬዎቹ የብልጽግና ሰዎች ወደ ስልጣን ሲመጡ ትልቅ የህዝብ ድጋፍ ያገኙት በህብረብሄራዊነት አጀንዳ ነው። የኦቦ ሸመልስን ንግግር ላደመጠ ያ የህብረ ብሄራዊነት አጀንዳ ገደል ገብቶ oromia first የመንግስቱ መሪ ርዕዮት ሆኗል ያስብላል። ብልጽግና ከህወሃት ራስ ወዳድነት ተማርኩ ቢልም ጡጦ አጥብቶ ካሳደገው ወያኔ መንደርን የማፍቀር ሀገርን የማኮስመን ፖለቲካ ብዙም አልተማረም።
፫. ኦቦ ሽመልስ ለአማራ ፣ ደቡብ ፣ ሶማሌ ወዘተ የትግል አጋሮቻቸው ከበሬታ አላቸውን ? ምን የፖለቲካ ሸፍጠኛ ብትሆን ፣ የትኛውንም ያህል ትልቁ ህልምህ መንደርን የመምራት ቢሆን በአንድ ፓርቲ ውስጥ ላሉት የትግል አጋሮችህ ከበሬታ መስጠት የድርጅት ፖለቲካ ሀ ሁ ነው። ኦቦ ሸመልስ የአማራና ሌሎች ብሄሮች የትግል አጋሮቻቸውን ገዥ እንዳጣ መናጆ እንደሚቆጥሯቸው ከቃለ መጠይቆቻቸው መረዳት ይቻላል። ይኼንንም ተራ ሸፍጠኝነት ፖለቲካ ልንለው ይሆን ?
፬. ኦቦ ሸመልስ የአዲስአበባን ህዝብ ከባዕድ ሀገር የፈለሰ የማይፈለግ ስደተኛ አድርገው እንደሚቆጥሩት ጸሀይ የሞቀው ሀቅ ነው። አዲስአበባን irrelevant እናደርጋታለን ማለት ነዋሪውን ” ሂድ አትበለው እንዲሄድ አድርገው ” በሚባለው የጭቆና ዘዴ ሀገር ፣ ከተማ አልባ እናደርገዋለን እያሉን ነው። ምን የሚሉት ዕብሪት ነው ? ወያኔ እንኳን እንዲህ አይነት እብሪት ነበረውን ?
በኦቦ ሽመልስ አብዲሳ ፣ ኦህዴድ/ብልጽግና ፖለቲካ ላይ ብዙ ማለት ይቻላል። ሰዎቹ የህዝብን አመኔታና ከበሬታ እንዳገለገለ ጫማ የሚወረውሩበት ፍጥነት እጅግ አስደማሚ ነው። ያም ባልከፋ ሀገር ምሩ ስንል እየተማጸንን ክልልና መንደር ካልመራን ሲሉ በድንክዬ ራዕይ ውስጥ ለመኖር መምረጣቸው የመሀሉን መንገድ መርጠን በጎ ሲሰሩ አበጃችሁ ላልናቸውም ዜጎች ግራ የሚያጋባ ሁነት ነው።
Filed in: Amharic