በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
ልጓም እንደሌለው ያልተገራ ፈረስ እንዲፏንን ከፌዴራል መንግስቱ ይሁንታን የተቸረው የሚመስለውና ሲሻው ሕጋዊ መዋቅርን ሲሻው ሕገ ወጥነትን ባመችው ኹኔታ እያቀያየረ የሚጠቀመው፣ ሀገርን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ያለው የ”ሸኔ” ቡድን ከአንድ ሳምንት በፊት በሸዋ ሮቢት አካባቢ ትንኮሳ የፈጸመ ቢሆንም በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ሳያደርስ በአካባቢው ማኅበረሰብ ርብርብ እንዲመለስ ተደርጓል። ይሁን እንጂ የሽብር ቡድኑ ኃይሉን በማጠናከርና በከባድ መሣሪያ ጭምር በመታገዝ በድጋሚ ሚያዝያ ፱ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም ከቀኑ ፲ ሰዓት ጀምሮ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ሸዋ ሮቢትና አካባቢው ላይ ጦርነት ከፍቷል። ይህ የሽብር ቡድን ጀጀባ ላይ በመሆን ወደ ዙጢና ሸዋ ሮቢት ከተማ ከባድ መሣሪያ በመተኮስ የሰው ሕይወት አጥፍቷል፣ በብዙ ሺዎች እንዲፈናቀሉ አድርጓል፣ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት አድርሷል፣ ከአሥር ሺህ በላይ ሰዎች የሚኖርባትን ሞላሌ ቀበሌን ሙሉ በሙሉ አውድሟል።
ፌዴራል መንግስትና የኹለቱ አጎራባች ክልሎች ተዋረድ ባለስልጣናት አካባቢው በተደጋጋሚ ሲደርስበት የነበረውን ተመሳሳይ ጦርነት በመረዳት ቅድመ ዝግጅት አድርጎ የክልሉን ሕዝብ ከሚደርስበት ግፍ መታደግ ባለመቻላቸው፣ የሽብር ቡድኑ የሚፈጽመውን ወረራ አይቶ እንዳላየ በማለፋቸው አልፎ ተርፎም በንጹሓን እልቂት የየራሳቸውን የፖለቲካ ትርፍ ለማትረፍ በመሯሯጣቸው ምክንያት ለተፈጠረው ቀውስ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በጦርነቱ ለደረሰው ጥፋት አስተዋጽዖ አድረገዋል ብለን እናምናለን።
የሀገር ትርጉምና ትእግስት የማይገባው ከጥንስሱ እስከ ውልደቱ ብሎም እስከ እድገቱ ሀገር ማፍረስ፣ እናቱንና እህቱን መድፈር፣ ንብረት ማውደምና መዝረፍ የሕይወት መርሑ የሆነው “ነውር ጌጡ” ባለዳቦ ስሙ “ሸኔ” ያለማቋረጥ የአማራን ሕዝብ ሰላም መንሳት፣ ንጹሓንን መግደሉና ማፈናቀሉ የሚቆመው እስከ አኹን ሲደረግ እንደነበረው የንጹሓን ሕይወት ከቀጠፈና ንብረት ካወደመ በኋላ የ“ተደመሰሰ” መግለጫ በማውጣት ሳይሆን ትጥቁን እስኪፈታ ድረስ “የተቀናጀ” ማጥቃት ሲውሰድበት ብቻ ነው።
በመሆኑም የአካባቢው ማኅበረሰብ በመንግስት አከላት አዘናጊ መግለጫ ሳይታለል በተለያየ አደረጃጀት ራሱንና ሀገሩን ከከፋው ጥፋት እንዲታደግ ጥሪያችን እያስተላለፈን ይህ ሽብር ቡድን የአካባቢውን መልክዓ ምድርና ሌሎች አመቺ ነባራዊ ኹነቶችን ተጠቅሞ ሕዝብን ለማንገላታት፣ አንዱ የኢትዮጵያ መውጫ መግቢያ የኾነውን መሥመር የመዝጋትና አለፍ ሲልም ወደአፋር ክልል ተሻግሮ የትሕነግን ያለተቋጨ ሕልም የማሳካት መኾኑ ታውቆ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቂ ትኩረት እንዲሰጠው እንጠይቃለን፡፡
በመጨረሻም ፓርቲያችን በጥፋት ቡድኑ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ይገልጻል።
ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!
እናት ፓርቲ
ሚያዝያ ፲፪ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ