>

"ብልፅግና ፓርቲ ወደ ትግራይ ከሚገባ ህወሓት ለዘላለሙ ቢገዛን እመርጣለሁ...!!!" (አብርሀ ደስታ)

“ብልፅግና ፓርቲ ወደ ትግራይ ከሚገባ ህወሓት ለዘላለሙ ቢገዛን እመርጣለሁ…!!!”
አብርሀ ደስታ

የህወሓት ተቃዋሚ ነበርኩ፤ ምክንያቱ ህዝባችን የተሻለ መሪነት ያስፈልገዋል ብዬ ስለማምን። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን ህወሓትን ስቃወም አልታይም። በዚህ ምክንያት የፒፒ ሰዎች “አብርሃ የህወሓት ደጋፊ ሆኗል” እያሉ ያሙኛል።
የህወሓት ደጋፊ እንኳ አይደለሁም። ግን የትግራይ ህዝብ ደጋፊ ነኝ። የትግራይ ህዝብ በጠላቶች በተወረረ፣ በተከበበ፣ በተገደለ ግዜ ህወሓትን መቃወም ልክ አይደለም። በዚህ ፈታኝ ወቅት በትግራይ ሐይሎች መካከል ምንም ልዩነት መኖር የለበትም። (እርግጥ ነው ህወሓት ወደ አማራ እና ዓፋር መግባቱ አልደግፍም)
ህወሓትን ስቃወም የነበረው የትግራይ ህዝብ በተሻሉ ልጆቹ እንዲተዳደር እንጂ የብልፅግና ፓርቲ መጫወቻ እንዲሆን አይደለም። የኔን ህወሓትን መቃወም ብልፅግናን የሚጠቅም ከሆነ ህወሓትን መቃወም እተዋለሁ። ምክንያቱም ከትግራይ ህዝብ ጥቅም አንፃር ሳየው ብልፅግና ከህወሓት ይብሳል። ህወሓት የትግራይ ህዝብ ጨቋኝ ነው፤ ብልፅግና ግን የትግራይ ህዝብ ጠላት ነው።
ህወሓት መብት ቢነፍገን ነው። ብልፅግና ግን ገድሎናል። ህወሓት መጥፎ ቢሆንም የኛ ነው። ብልፅግና ግን ባዕድ ነው፤ ዕድል ካገኘ ያጠፋናል። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ በልጆቹ እንዲተዳደር እፈልጋለሁ። ብልፅግና ፓርቲ ወደ ትግራይ ከሚገባ ግን ህወሓት ለዘላለሙ ቢገዛን እመርጣለሁ።
ለዚህ ነው ህወሓት ላይ ለዘብተኛ የሆንኩት!
Filed in: Amharic