ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
*…. አደጋውን በጋራ ለመቀልበስ የሽግግር መንግስት – በአስቸኳይ…!!!
ሃገራችን ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ፣የተጋረጠብን ምስቅልቅልና ውስብስብ ማኅበረ-ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ፈተና ገዢው ፓርቲ- የትናንቱ ህወኃት/ኢህአዴግ፣ የዛሬው ኦዴፓ/ብልጽግና በተለመደው የሰጎን ፖለቲካ ሲያልፍም የሸፍጥና ሴራ የተረኝነት ፖለቲካ ሊሻገርና ዕድሜውን ሊያራዝም ከማይችልበት ደረጃ መድረሱ ሊደበቅ የማይችል የአደባባይ ምስጢር ሆኗል፡፡ሃገራችን የምትገኝበት ሁኔታ እጅግ፣በጣም አስቸጋሪና ተመጋጋቢ በሆኑ ችግሮች የተሞላ ነው፡፡
እርግጥ ነው፤ዛሬ መከራችንና ፈተናችን ከለመድነውም በተለየ መንገድ፣ገዢው ፓርቲ እንደ ፓርቲም ሆነ መንግስት እንደለመደው ‹‹የአስተሳሰብና ተግባር አንድነት መስርተናል፤በስብሰን ታድሰናል›› በማለት የተደቀነብንን ፈተና ሊሸፍነው ከማይችልበት ደረጃ ደርሷል:: ጽንፈኛ፣አሸባሪ፣ጁንታ…ብሎ ከፈረጃቸውና የአገራችን ሥጋት እያለ ፕሮፖጋንዳ ከሚሰራባቸው ባልተናነሰ በጉባኤው ማግስት በውስጥ በተፈጠረው የሥልጣንና የ‹ፖለቲካ ሽኩቻና በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል ሊባል በሚችል ማንነት ተኮር ግጭቶች የአገራችን ህልውና፣ሉዓላዊነትና አንድነት ከፍተኛ ሥጋት ሆኗል፡፡
ሃገራችን በታሪኳ ገጥሟት ከማያውቅ የፖለቲካና ዲፕሎማሲ ክስረት፣የኢኮኖሚና ማኅበራዊ በተለይም ሠላምና መረጋጋት ቀውስ ውስጥ ወድቃለች፡፡ በአራቱም አቅጣጫ ካሉ ጎረቤቶቻችን /ድንበርተኞቻችን ጋር ያለን ግንኙነት ጤናማ አይደለም፣ ድንበር ዘልቀው የጦርነት ቢያንስ የትንኮሳ ሙከራ እያሳዩን ነው፡፡ በዚህ ላይ የቅርብና የሩቅ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እጃቸውን ለማስገባት የውስጥ ቅራኔዎቻችን ሊጠቀሙበት ዕድል ያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሮ በተግባር እያየን ነው፡፡ የህግ የበላይነት አለመከበርና የመንደር ጎበዝ አለቆችና በህዝብ ሥም የጥቅም ነጋዴዎች ያስከተሉት ቀውስና እያስከተሉ ያሉት ጥፋት መንግስት አለ? ብሎ ከሚያስጠይቅ ደረጃ አልፎ ህዝብ ተስፋ ቆርጦ ለመሰደድ የተገደደበት ሁኔታ ከአራቱም አቅጣጫ እየተደመጠ ነው፡፡ መንግስት ቀዳሚና ዋና ተግባሩን የዜጎችን ሰላምና ደህንነት፣መብትና ክብር ማክበርና ማስከበር ያለመቻሉን የሰሞኑ የጠቅላይ ሚ/ሩ ከጄነራል መኮንኖች ጋር ያደረጉት ስብሰባ፣በብልጽግና ፓርቲዎች መካከል የምንሰማው ሰጥ-አገባ፣ከሰሜን ጫፍ ትግራይና አማራ እስከ ደቡብ ጫፍ ደቡብ ኦሞና አማሮ፣ከምዕራብ ቤኒሻንጉል ክልል እስከ ምስራቅ አፋር ክልል …በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሱት ማንነት ተኮር ጥቃቶች፣ማፈናቀልና መፈናቀል፣ከቁጥጥር ውጪ የሆነው ሙስናና የዋጋ ግሽበት፣ዜጎች በምትሃት ነው የሚኖሩት የሚያስብለው ከመቼውም ጊዜ የከፋው የኑሮ ውድነት- በወጣቱ ሥራ አጥነትና የትምህርት ሥርዓቱን ጨምሮ ተስፋ መቁረጥ፣የሥጋታችን ግልጽ መገለጫዎችና ማስረጃዎች ናቸው፡፡
መፍትሄው እጅግ ከባድ ቢመስልም፤በሌላ በኩል ከቂም በቀልና ጥላቻ፣ የተረኝነት አግላይና ጠቅላይ የፖለቲካ አስተሳሰብ ተላቀን፣የተጋረጠብንን ሃገራዊ አደጋ በትክክል ተረድተን ሥልጣንም ሆነ የፖለቲካ ፉክክር ከአገር ኅልውና ሉዓላዊነትና ከህዝብ ክብርና ጥቅም ውጪ የሚታሰብ ያለመሆኑን ተቀብለን፣ ለአገርና ህዝብ፣ለሠላምና ልማት እንዲሁም ፖለቲካ መረጋጋት ቅድሚያ ሰጥተን በሽግግር መንግስት እየተመራን በግልጽ በቅን ልቡና ተኣማኒና አሳታፊ አካታች ዲሞክራሲያዊ ሂደት የብሄራዊ መግባባትና ሃገራዊ ዕርቅ መድረክ ፈጥረን ከተመካከርን፣ ከተወያየንና ከተደራደርን የማንፈታው ችግር አይኖርም፡፡
ለዚህ ገዢው ፓርቲ -መንግስት እንዲሁም አመራሩ፣ሃገሪቱ ከተደቀነባት የመፈራረስ አደጋ ታድጎ፣ ለመምራትና ማስተዳደር አለመቻሉን፣ አምኖ ከተለመደው የክህደትና እብሪት አስተሳሰብና የስልጣን ጥማት ተላቆ ለሽግግር መንግስት ምስረታ ራሱን ማዘጋጀት ግድ ይላል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው አማራጭ ገዢው ፓርቲ-መንግስት እንኳን ሊያሻግረን፣ራሱም ከገባበት የመፈራረስ አደጋ ሊሻገር አይችልም፡፡
በእጅጉ የሚያሳስበን የገዢው ብልጽግና መንግስት እንዲሁም አመራራቸው መሻገርና ማሻገር አለመቻል ሳይሆን ራሳቸውን ብቻ ይዘው ያለመጥፋታቸው ነው፤ እኛም ሃገራችንም የእነርሱ እብሪትና ክህደት፣ገደብ የለሽ የሥልጣን ጉጉት ገፈት ቀማሽ መሆናችን ነው፡፡ ስለሆነም ፓርቲያችን ኅብር ኢትዮጵያ– አገራችን ካለችበት እጅግ አሳሳቢ ሁኔታና የመፍረስ አደጋ መታደግ ለነገ የማይባል ተግባር ብቻ ሳይሆን ፋታ የማይሰጥ ሃገራዊ ግዳጅ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ስለዚህ፡-
1ኛ/ ገዢው ፖርቲ-መንግስት ያለንበትን አደገኛ ሁኔታ ከአቅሙ በላይ መሆኑን ተቀብሎ ከተለመደውና ከለመደው የፖለቲካ አስተሳሰብና ተሞክሮ ተላቆ ለዘላቂ ሃቀኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ሠላም መስፈንና የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት በቅን ልቡና ለጋራ መፍትሄ ዝግጁ ነኝ በሚለው ልክ በሽግግር መንግስት እየተመራን ለችግሮቻችን የጋራ መፍትሄ እንድናበጅ የፖለቲካ ቁርጠኝነቱን እንዲያሳይ፤
2ኛ/ የዘላቂ ሠላማችን የቀጣይና ፍትሃዊ ልማታችንና የሃቀኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ባለድርሻ አካላት- የኃይማኖት ተቋማት፣ሚዲያ፣የሲቪክና የሙያ ማኅበራት፣ሃገራችን የምትገኝበት ሃቅ ተሸክሞ የመጣውን አጣብቅኝና አደጋ ተረድተው ከተለመደው የማስመሰልና የማመቻመች ሃሳብና ተግባር ተላቀው ለመፍትሄው የበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት በሽግግር መንግስት ለብቸኛው የብሄራዊ መግባባትና ሃገራዊ ዕርቅ በባለቤትነት ቆራጥ መንፈስ እንዲቆሙ፤
3ኛ/ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት በጋራ እንዲሁም ፓርቲዎች በተናጠል ለተኣማኒ፣አሳታፊና አካታች ‹‹ብሄራዊ መግባባትና ሃገራዊ ዕርቅ መድረክ መፈጠር›› የጀመሩትና ከጅምሩ የተጨናገፈው ሂደት በሽግግር መንግስት እንዲመራ፣እንዲሁም ተቀራራቢና ተመጋጋቢ የመፍትሄ ኃሳብ ያላቸው ፓርቲዎች ምክረ ሃሳባቸውን በጋራ የሚያዘጋጁበት አሰራር እንዲፈጥሩ፤
4ኛ/ አገራችን ያለችበትን መስቀለኛ መንገድና ከፍተኛ ፈታኝ ሁኔታ ከችግሩ ቀጥተኛ ገፈት ቀማሽ ህዝብ በላይ የሚረዳ የለምና ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሽግግር መንግስት ለተኣማኒ አሳታፊና አካታች ብሄራዊ መግባባትና ሃገራዊ ዕርቅ መሳካት ለሚደረገው ትግል ያልተቆጠበ ድጋፋቸውን እንድትሰጡ፤
5ኛ/ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ወዳጆች ለአገር አድን ተኣማኒ አሳታፊና አካታች ብሄራዊ መግባባትና ሃገራዊ ዕርቅ መሳካት ለምናደርገው ትግል አዎንታዊና ገንቢ የወዳጅ ተጽዕኖ እንድታሳድሩ፤ስንጠይቅ፣ፓርቲያችን ለእነዚህ ተፈጻሚነት በሽግግር መንግስት ተመርተን ተኣማኒ አካታችና አሳታፊ ብሄራዊ መግባባትና ሃገራዊ ዕርቅ እውን እንዲሆን ማንኛውንም ሰላማዊና ህጋዊ ትግል በቆራጥነት ለማድረግ፣ለመምራትና ማስተባበር ዝግጁ መሆኑን እያረጋገጥን ከላይ ጥሪ ያቀረብንለችሁ ባለድርሻዎች ሁሉ ከጎናችን እንድትቆሙ አበክረን ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ኅብር ኢትዮጵያ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣
ሚያዚያ 13/ 2014 ዓ.ም፤አዲስ አበባ ፡፡