>

የአፄ ምኒልክ የልብ ወዳጅ፣ ምስጢረኛ ፣ ልዩ አማካሪ እና መሀንዲስ ፤  አልፍሬድ ኢልግ (ታሪክን ወደኋላ)

የአፄ ምኒልክ የልብ ወዳጅ፣ ምስጢረኛ ፣ ልዩ አማካሪ እና መሀንዲስ ፤  አልፍሬድ ኢልግ
ታሪክን ወደኋላ

አልፍሬድ ኢልግ የተወለደው በስዊዘርላንድ ፍራዩንፌልድ እ.ኤ.አ.1854 ሲሆን በዙሪክ በሚገኘው የፌዴራል ፖሊ ቴክኒካል ምህንድስና የተማረው አልፍሬድ በወቅቱ የሸዋ ንጉሥ የነበሩት በኋላም ላይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ አገራቸውን ለማዘመን እና አዲስ ዋና ከተማ ለመገንባት በጣም ጉጉት ስላደረባቸው ከአውሮፓ የመጡ ሰራተኞችን፣ ቴክኒሻኖችን እና የጦር አማካሪዎችን ቀጥረው ነበር።
የውጭ አገር ቴክኒሻኖችንና የእጅ ባለሙያዎችን በቤተ መንግሥት እንዲያገለግሉ ሲጠሩ አልፍሬድ ኢልግ ይህን ዕድል ተጠቅሞ በ 1878 ዓ.ም በሃያ አምስት ዓመቱ ከስዊዘርላንድ በመውጣት ከአስቸጋሪ የስምንት ወር ጉዞ በኋላ በ 1879 ኢትዮጵያ ደረሰ።  በሀገራችን ከሩብ ክፍለ ዘመናት በላይ በመቆየቱና በሰራው አያሌ ስራዎች በሚኒስትር ዴኤታነት ማዕረግ የተሸለመ አንጋፋ ቴክኒሺያን ነበር።  በ 25 ዓመቱ ከኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ጋር ወደ አገልግሎት እንደገባ እና በሀገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካደረባቸው ሰዎች መካከል አንዱ ለመሆን የቻለውን አስደናቂ ታሪክ የሰራ ሠው ነበር።
በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ዘመን ለአገራችን ዕድገትና በተለይም ለአዲስ አበባ ከተማ መቆርቆር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ፣ የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ቤተ መንግስት ፣ መንገዶች ፣ ድልድዮች ፣ የመጀመሪያውን የቧንቧ ውሃ አቅርቦት ስርዓት ዲዛይን እንዲገነባ ያደረገ ፣ የጥይት ፋብሪካ በኢትዮጵያ ተገንብቶ ለሕዝብ አዳዲስ የጦር መሣሪያዎችን እንዴት መጠቀም እንዳለበት ያስተማረ ፣ በአዲስ አበባ በነበረው ቆይታው ወደ 1,000  ያህል የሚጠጉ ምስሎችን ፎቶግራፎችን ያነሳ ፣ በ 1905 በንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል በመትከል እንዲሁም በመቆጣጠር ሃላፊነት የነበረው ፣ የተዋሃደ ብሄራዊ ምንዛሪ ስርዓት እና የፖስታ ስርዓት የዘረጋ ፣ ዘመናዊ መሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ የልብ ወዳጅና ምሥጢረኛ፣ ልዩ አማካሪ የነበረው ስዊዘርላንዳዊው አልፍሬድ ኢልግ።
አልፍሬድ ኢልግ የአገሬውን ቋንቋ አማርኛ መናገርና መጻፍ የቻለ ሲሆን ለንጉሠ ነገሥቱ ያለውን ታማኝነት በተለያዩ አጋጣሚዎች አስመስክሯል።
አልፍሬድ ኢልግ ኢትዮጵያ የነበረውን ቆይታ አጠናቅቆ ወደ ሀገሩ ስዊዘርላንድ ተመልሶ ዙሪክ ኑሮውን በዚያ አድርጎ በተወለደ በ 61 አመቱ እ.ኤ.አ 1915 ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።
Filed in: Amharic