>
5:33 pm - Saturday December 5, 1035

ቢንያም ታደሰ ለምን ታሰረ?!

ቢንያም ታደሰ ለምን ታሰረ?

(ጌጥዬ ያለው)

ለወትሮው አዳዲስ መንግሥታት ሲመጡ እስር ቤቶችን ቢቻል ሙሉ በሙሉ ለመዝግጋት፤ ካልሆነም ለመቀነስ ቃል ይገባሉ። በርግጥ ሙሉ ለሙሉ መዝጋት የማይቻል መሆኑ እሙን ነው። ቢያንስ ግን በርካታ የወንጀል እስረኞችን አስተምረው  በምህረት ይለቃሉ። የፖለቲካ እስረኞችን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ይፈታሉ። ከዚህ አንፃር ደርግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ወህኒ ቤቶችን ትምህርት ቤትና የጤና ማዕከል የማድረግ ፍላጎት ነበረው። ሆኖም ፍላጎቱ አለመሳካቱን ራሳቸው መንግሥቱ ኃይለማርያም ‘ትግላችን’ በተሰኘው መፅሐፋቸው ገልፀዋል።
የእስረኞችን ካቴናዎች ከእጆቻቸው ማሰርና መፍታት የቅኔ ደብዳቤ አንብቦ እንደመረዳት ያደናገረው የኦሮሙማ መንግሥት በአዲስ አበባ እስረኛን የመቀነስ ፍላጎትም አልነበረውም። እንኳንስ የታሰሩትን ሊፈታ በየቤቱ ባለው አዲስ አበቤ ላይ ቂም ቋጥሮ ነው የመጣው። እንደማንኛውም አዲስ መንግሥት ወግ ደርሶት የወንጀል እስረኞችን በከፊልም ቢሆን አርሞና አንፆ በምህረት ይፈታል እየተባለ በቃሊቲ፣ በሸዋሮቢትና በዝዋይ ወህኒ ቤቶች በጉጉት ቢጠበቅም አላደረገውም። እዚህ ላይ ‘የፖለቲካ እስረኞችኝ ፈቷል’ የሚል ተከራካሪ ሊኖር ይችላል። ስለዚህ ከዛሬው የትግል ጡረተኛና የቤተመንግሥቱ ’85’ ተከፋይ አንዳርጋቸው ውጭ ሁሉም ኃይለማርያም ደሳለኝ በሥልጣን ላይ እያሉ የተፈቱ መሆናቸውን ላስታውስ።
ተረኛው ኦሕዴድ/ብልፅግና ገና የሥልጣን ጫፍ ላይ ሲደርስ ወያኔ ያስጀመራየውን የግንባታ ፕሮጀክቶች ሁሉ ሲያቋርጥ የወህኒ ቤት ሕንፃዎችን ግን እግር በእግር ተከታትሎ አስጨርሷል። ይህም ዛሬ ወጣቶችን በብሔርና በሃይማኖት እየመደበ በጅምላ ለማሰር አስችሎታል። በተለይ አባ ሳሙኤል  ወህኒ ቤት ለዚህ አገልግሎት የሚውል ነው። ቀደም ሲል የትግራይ ተወላጆች በጅምላ ታስረውበት ነበር። እነርሱ የስብሃት ነጋን እግር ተከትለው ከወጡ በኋላ ‘የአድዋ እና የካራማራ የድል በዓላተትን አከበራችሁ’ አማሮችና የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች እየተመረጥን ስንገባ ይህ እስር ቤት ሁለት ገፅታዎች ነበሩት፦
፩. በግድግዳው ላይ የተሳሉ ስዕላት መቀሌ ያለውን የሰማዕታት ሙዚየም አስመስለውታል።
፪. የውሃ መተላለፊያ ቱቦዎቹ፣ የመፀዳጃ ቤቶች በሮች እና ሌሎች ዕቃዎች ሁሉ ተሰባብረውና ተነቃቅለው ከጥቂት የግድግዳ  ላይ መንፈሳዊ ስዕላት ጋር ሲታዩ ግራኝ አሕመድ ያለፈበት የክርስቲያን መንደር አስመስሎታል። እንደ ፖሊስ ባልደረቦች መረጃ ትግሬዎች መፈታታየወውን ሲያውቁ ነው በቻሉት መጠን አውድመውት የሄዱት።
ያም ሆነ ይህ ተረኛው ስርዓት በብሔርና በሃይማኖታችን መድቦ እያፈራረቀ እያሰረን ነው። የቢንያም ታደሰ እስር ደግሞ ከብዙዎቻችን ይከፋል። ፖለቲካው የብሔር መካረር ሲገጥመው ይታሰራል። ይኸው ፖለቲካ የሃይማኖት  ፍጥጫ ውስጥ ሲገባም ይታሰራል። ምናልባት ነገ ፖለቲካው በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ቡድኖች ውስጥ እጁን አስገብቶ ቢያበጣብጥም ይታሰራል። ምክንያቱም ቢንያም በሦስቱም ላይ ንቁ ተሳታፊ ወጣት ነው።
ወጣቱ  የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ንቁ አባል ነው። የምርጫ ቅስቀሳዎችን ጨምሮ ፓርቲው በሚያደርጋቸው የጎዳና ላይ እንቅስቃሴዎች ግንባር ቀደም አስተባባሪ ነው። በአማራ ሕዝብ ላይ ብሔር ተኮር ጅምላ ጭፍጭፋ ሲፈፀም ያጋልጣል። አማሮች ሲፈናቀሉ የእለት ደራሽ እርዳታ ያሰባስባል፤ ያግዛል። ይህም ለአማሮች የእስር ዋራንት ሲፃፍ ስሙ እንዲካተት ምክንያት ሆነ።
ቢንያም ታደሰ በከተማው ቋንቋ ግንባሩ ላይ እንደ አራት ማዕዘን ሰፌድ የተዘረጋ ኮፍያ የሚያደርግ አራዳ፤ ፍንዳታ ነው። አምላኩን የሚፈራ ብቻ ሳይሆን ዘወትር የሚፀልይ ጨዋ ኦርቶዶክሳዊም ነው። በአባ ሳሙኤል እስር ቤት በነበርንበት ጊዜ ማታ ማታ የእስረኞችን የቤት ውስጥ የኅብረት  ጸሎት ይመራል። ቀን ቀን በጸሎት ቤት ውስጥ ብቻውን ከሰው ተገልሎ ተንበርክኮ ሲጸይይም በተደጋጋሚ አጋጥሞኛል። በንግግሮቹ መሀል “ጻድቁን! ጻድቁ አባቴን!” ማለት ይወዳል።
ከእስር ቤት ውጭ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያ የአደባባይ በዓላት በሚከበሩበት ጊዜያት የደብር አገልግሎት አስተባባሪ ነው። ጥምቀት ሲከበር ጃን ሜዳን በማፅዳት፣ መስቀል ሲከበር መስቀል አደባባይን በማፅዳት እንቅስቃሴዎች ላይ ቢንያም ታደሰ ከፊት ሆኖ አስተባባሪ ነው። በዚህም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች የእስር ዋራንት ሲፃፍ ለእርሱም አብሮ ይፃፋል። የዛሬው እስሩም ይኸው ነው። ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ መልኩ ኦርቶዶክሳውያን ሲታሰሩ ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሠኖሪያ ቤቱ ተወስዶ በፒያሳ፤ እቴጌ ጣይቱ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ታስሯል።
ለወቅቱ እስር ምክንያት የሆነው በዕለቱ በመቀል አደባባይ ሊደረግ ታስቦ በፖሊስ የተከለከለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አውደ ምህረት ላይ መገኘቱ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ ቢንያም የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች አስተባባሪም ነው። በስታዲዮም ውስጥ ደጋፊዎችን መዝሙሮች በማስዘመርና በማስጨፈር ይታወቃል። እንግዲህ የእስር ዋራንቱ ወደ ስታዲዮም ከዞረም ቢንያም ማስታወሱ አይቀርም።
ይህ ለእኛ ቀላል ሊመስለን ይችላል። ለገዥዎች ግን እጅግ አስፈሪ ነው። ‘ሕዝበ ክርስቲያኑን፣ በብሔር ተለይቶ ተጎጅውን እና የእግር ኳስ ቤተሰቡን የማስተባበር እድል ያለው ሰው ፖለቲካውንም የመጠምዘዝ ሃይል ይኖረዋል’ የሚል ነው ፍርሃቱ። ፈሪ ደግሞ ያስራል፤ ይገድላልም።
Filed in: Amharic