>

የእኔ ወሎ፣  የእኔ ኢትዮጵያ እንዲህ ትመስላለች! (አገሬ አዲስ)

የእኔ ወሎ፣  የእኔ ኢትዮጵያ እንዲህ ትመስላለች!

አገሬ አዲስ

 


በሰሞኑ በወሎ ክፍለሃገር ፣በአጠቃላይም በኢትዮጵያ የተከሰተው ሃይማኖትን ተገን ያደረገ የሕዝብ እርስ በርስ ግጭትና ቀውስ  ብሎም አገር ለመበታተን ታስቦ የተደረገ ሴራ እንደኔ ያለውን አገር ወዳድ ብቻ ሳይሆን ሌላውንም የሰው ልጅ በመላ ትልቅ ሃዘንና ስጋት ላይ የጣለ ነው።ይህ ጸረ ኢትዮጵያ በሆነ  የፖለቲካ ቡድን ታስቦና ታቅዶ የተከሰተ ችግር በጊዜው ካልተገታ አጥፊዎቹ ያሰቡት ዓላማ ግቡን እንደሚመታ ጥርጥር የለውም።በኢትዮጵያ ጠላቶች በሆኑት የውጭና የውስጥ የሴረኛው ቡድን በቀሰቀሰው ቀውስ ውስጥ ሃይማኖታቸው የተነካባቸው የመሰላቸው የዋህ ሙስሊም ወጣቶች በተለይም በደሴ ከተማ ትልቁ መስጊድ ውስጥ ባካሄዱት ስብሰባ የጥፋት እጃቸውን ለመሰንዘር ባደረጉት ቅስቀሳ፣ያልተገራና መርዘኛ ቃላትን በአንደበታቸው እዬረጩ በመስማቴ፣በአዲስ አበባና በሌላውም ያገራችን ክፍሎች  የሃይማኖት ተቋማትን በማውደምና በመዝረፍ ምእመናኑንም በድንጋይና በቆንጨራ በመቀጥቀጥ የሰው ልጅ ህይወት በማጥፋት  የትርምስ መሣሪያ ሲሆኑ በዝምታ ማዬት ተገቢ ባለመሆኑ  እኔና የእኔ ትውልድ በሚያውቃት  ወሎና ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት እንደኖርን የታሪክ ምስክርነትን በመስጠት ወጣቱን ትውልድ ከስህተት ጎዳና የማውጣት አላፊነት አለብን በማለት ይህችን ምክር አዘል ጽሑፍ ለመከተብ ተገድጃለሁ። 

ትውልድና የልጅነት ዕድሜዬን ያሳለፍኩት ወሎ ክ/ሃገር ዋና ከተማ በሆነችው ደሴ ከተማ ሳላይሽ ሰፈር ነው።ትውልዴም ከሁለቱ ሃይማኖት ተከታይ ፣ሙስሊምና ክርስቲያን ቤተሰብ ነው።ገና የአራት ዓመት ህጻን ሆኜ አባቴ ለክርክር አዲስ አበባ ሄዶ በሶስት ቀን በሽታ ሞቶ እዛው በቀጨኔ መድሃኒዓለም ተቀበረ።በጊዜው ከደሴ አዲስ አበባም ሆነ ከአዲስ አበባ በመኪና የሚወስደው ጊዜ ሶስት ቀን ነበር፣ያንን ከአራት  መቶ ኪሎሜትር የማይበልጥ መንገድ በዚህ የጊዜ ተመን የሚፈጅበት አውቶብስ እንደ አሁኑ በስድስትና በሰባት ሰዓት ውስጥ ተምዘግዝጎ የሚደርስ ሳይሆን ሃጂ ሃሰን እረሽድ የተባሉ የጊዜው  የከባቢው ቱጃር የጭነት መኪናውን በነጆቫኒ በተባሉት ጣሊያኖች ጋራጅ አስቀጥቅጠው መስኮትና ጣራ ገጥመውለት፣እንዲሁም አግዳሚ ወንበር ደርድረው ያዘጋጁት አውቶብስ ነበር።ከደሴ ካራ ቆሪ፣ከካራ ቆሪ ደብረ ብርሃን ፣ከደብረብርሃን አዲስ አበባ በሁለት ብር ክፍያ የሚጓጓዙበትን ዕድል የፈጠሩት ቱጃር ስማቸውና ውለታቸውን እንደኔ ያለው በአሁኑ  የሰባ ዓመት ዕድሜ ውስጥ ያለው የከባቢው ተወላጅ የማይረሳው የከተማዋ  የታሪክ አካል ነው።ታዲያ በዚህ አይነቱ ጉዞ  የአባቴን  አስከሬን ጭኖ መመላለስ ለቋሚም መንገደኛ አዳጋችና አስቸጋሪ ነበር።ስለሆነም አባቴ በቀደሰበትና አያት ቅድመአያቶቹ በተከሉት ቤተክርስቲያን መካነ መቃብር አፈር ሳይበቃ በወጣበት ሞቶ ለመቀበር አንዱና ብቸኛው አማራጭ ነበር።ከዓመት በዃላ እኔንና ታላቅ ወንድሜን ይዛ እናታችን ባባታችን የተጀመረውን ክርክር ለመቋጨትና ለደጅ ጥናት  በዚሁ የሦስት ቀናት ጉዙ አዲስ አበባ የሄድኩት የአምስት ዓመት ልጅ ሆኔ ነበር።ያረፍንበት የዘመድ ቤት በቀበና አካባቢ ስለነበር ልብሳችን የሚታጠበውና እኛም በውሃ የምንቦጫረቀው እዛው ወንዝ ነበር።ከእለታት አንድ ቀን እኔና ወንድሜ እውሃው ውስጥ ስንጫወት ፈጥኖ ደራሽ ጎርፍ ሳይታሰብ መጣና እኔን እያንከባለለ ወሰደኝ፤እኔን ለማዳን እዬጮኸ ወንድሜ ከዳር ዘሎ ገባ፤በከባቢው የነበሩት ትልልቅ ሰዎች ተሯሩጠው ሁለታችንንም አዳኑን።ይኸው ዛሬ ከ65 ዓመት በዃላ ታሪኩን ለመጀመሪያ ጊዜ ለመጻፍ በቃሁ።

ወደ ተነሳሁበት እርዕስ ልመለስና የተወለድኩባት ደሴ ከተማ እስላሙም፣ክርስቲያኑም ተጋብቶና  ተዋልዶ፣ለመኖሩ እኔው እራሴ ማስረጃ ነኝ።በወሎ ውስጥ ሰው  በሃይማኖት የተጋጩበት ጊዜ አላዬሁም፣አንዱ ከሌላው ጋር ተባብሮ መከራና ደስታ ተካፍሎ የኖረና የሚኖር ሕዝብ ነው።ሰርግ ሲደግስ የሙስሊምና የክርስቲያን ምግብ ተዘጋጅቶ በአንድ ዳስ ውስጥ በተሰናዳ አውራጅ ተብሎ በሚጠራ ረድፍ(ተርታ)ወንበር ላይ ተቀምጦ የሚበላ፣ለሙስሊሙ ቀሪቦ(እምቡሽቡሽ) ለክርስቲያኑ ጠላና ጠጅ ተጠምቆለት የሚጠጣ፣ ሙሽሮች በሁለቱም የእምነት አባቶች፣ ሽማጌሌዎች ጉልበት ስመው ተመርቀው የሚወጡበት አገር ነው።ትዝ ከሚለኝ ሁሉ  እኔን አጥምቀው  የክርስትና ማተብ ያሰሩልኝ የሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የደብር አለቃ አባ ሃዲስና የሸዋ በሩ መስጊድ ኢማም የነበሩት ሸህ አሊ(ሃሰን)ለጊዜው ስማቸውን እረሳሁት፣ሁለቱም በቁመት እረጃጅም የሆኑ የሃይማኖት አባቶች ደሴ አስፋልቱ ላይ ሲገናኙ ተሳስመውና እጅ ለእጅ ተያይዘው ወደ መሃል ፒያሳ ሲራመዱ ያዬሁት የተለመደ ፍቅርና ወንድማማችነት እስከዛሬ ድረስ በህሊናዬ ይመላለሳል።ታዲያ እነዚህ ደጋጎች የአሁኑን ክስተት ቢያዩ ምን ይሰማቸው ይሆን? የእስልምና አስተማሪ የነበረው በቅርቡ ያለፈው ዘመዴ የሱፍ አደምስ ይህንን ጉድ ቢያይ ምን ይሰማው ይሆን።የሰጠው መልካም የቁርዓን ትምህርት በዚህ ሰይጣናዊ ስነምግባር ሲተረጎም መንፈሱ ዝም ትል ይሆን?አይመስለኝም።የሞቱትም ሆኑ በህይወት ያሉ ቀናና ደግዬ ሙስሊም ወሎዬዎች ለመግለጽ ባይችሉም ውስጣቸው በሃዘን ሳይዋጥ የሚቀር አይመስለኝም።የወሎ ሕዝብ ለአንድነትና ለአብሮነት ተምሳሌት መሆኑን ሁሉም የሚያውቀው ነው።ለዚያም ነው ወሎ ገብሱ ተብሎ የሚጠራው።ገብስ ጤናና ጉልበት የሚሰጥ ፣ለሁሉም አይነት የምግብ ዝግጅት የሚያገለግል እህል በመሆኑ ሕዝቡንም እንደዚያው ከሁሉም ጋር ተስማምቶና ተጋብቶ፣ተዋልዶ፣ሁለገብ ማንነትና ባህል ይዞ  በመኖሩ የተሰጠው የጋራ መግለጫ ሆኗል። በመሆኑም በወሎ ምድር፣ለዚያውም በደሴ ከተማ አሁን የሚታዬውና የሚሰማው ነገር ሲከሰት የዘመኑን መርከስ፣የትውልዱን መበከል የደረሰበትን ጣራ ማሳያ ነው።ለወሎ ሕዝብ እንግዳና ባዳ እኩይ ኩነት ነው።ለወሎ ሕዝብ ቀርቶ በወሎ መሬት ያለፈና የረገጠ ሰው ያደርገዋል ተብሎ አይገመትም።

ሌላም ምሳሌ ልጥቀስ፣ በንጉሥ ሃይለሥላሴ ዘመን የፓርላማ ምርጫ ሲካሄድ የደሴ ሕዝብ እስላም ክርስቲያን ሳይባል በነቂስ ወጥቶ የመረጣቸው የዛን ጊዜውን ትንታግ ወጣት ፣የወይዘሮ ስሂን ተማሪዎች የውይይትና የክርክር ክለብ አባልና መሪ፣በግጥምና በድርሰት ጽሑፉ ታዋቂ  የነበረውን አሊ ዘገዬንና የሰፈሬን ጎልማሳ ሰው ክቡር አመዴ ለማን ነበር።እነዚህ የተከበሩ የፓርላማ አባላት በሃይማኖታቸው ሳይሆን በንጹህ ኢትዮጵያዊነታቸውና ለሰው ልጆች ክብርና መብት ከነበራቸው አቋም፣ መልካም አስተሳሰብና ስነምግባር በመነሳት ነበር እስላሙም ክርስቲያኑም ድምጹን የሰጣቸውና ለመመረጥ የበቁት።ከዚያም ወዲህ በዬጊዜው በማህበራዊ ኑሮና እንቅስቃሴዎች ብዙ አስተዋጽኦ ያደረጉ የሙስሊምና የክርስቲያን እምነት ተከታይ የሆኑ ደግዬ ወሎዬዎችን ቆጥሮ መጨረስ ያዳግታል።የቀድሞው የሙስሊሙ ጁማአ መሪ የነበሩት የሃጂ ሳኒም ሆኑ የአሁኑም የሙስሊሙ መሪ የሃጂ ሙፍቲ መገኛ የወሎ መሬትና ማህበረሰብ ነው።የጥንቱም ድንቅዬ ወልይ (ትንቢተኛ) የሆኑት ሸህ ሁሴን ጅብሪል የዚሁ ዕድለኛ ክፍለሃገር የወሎ መሬት ያበቀላቸው ናቸው።

ታዲያ የአሁኖቹ በተለይም የሰሞኑ አገር አጥፊና ሕዝብ አሸባሪ እንቅስቃሴ ከዬት ሊመጣ ቻለ ብለን ብንጠይቅ መልሱ ቀላል ነው።ይህ ክስተት ለረጅም ጊዜ ታስቦና ተወጥኖ ለመጨረሻ  ሙከራ ጊዜና ምክንያት ጠብቆ የወጣ የጥፋት  ካርድ መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው።የካርዱ አዘጋጆችም የሚታወቁ  ናቸው። በአክራሪነት የተጠመቁ፣ በግብጽና በሳውዲ አረቢያ ለቁርዓን ትምህርት ሄደው የተመለሱ፣በአገር አጥፊው የፖለቲካ ቡድን በህወሃትና በኦነግ ፣ወለዱ የኦሕዴድ ስብስብ የሚታገዘው ቡድን  ያሰለጠናቸው፣ሰርጎ ገቦች የሚዘወር እንቅስቃሴ ለመሆኑ ከሚያደርሱት ጥፋትና መፈክር ማወቅ ይቻላል።ላሰቡት ዓላማ እንቅፋት ይሆናል ያሉትን አገር ወዳዱን አማራ ና የሱንም የመከላከያ ሃይል ከክርስቲያኑና ከሙስሊሙ እምነት ተከታይ ከሆነ ማህበረሰብ የተውጣጣ፣ ድልና መከራውን፣ሞትና መቃብሩን እኩል የሚካፈል ፋኖን እንዲሁም  የኦርቶዶክስ ተዋህዶን እምነት ተቋም ለማጥፋት በተለያዩ ቦታዎችና ጊዜዎች የተሞከረውና የከሸፈውን የጥፋት ተልእኮ አሁን ሕዝብ ተዳክሟል፣ኑሮ አስመርሮታል፣ተከፋፍሏል ብለው ባሰቡበት ጊዜ የተነሳ የተቀናጀ ድርጊት ነው።የፖለቲካው ተላላኪ የጥፋት ሃይል ለመሆኑም መንግሥት ተብዬው ቡድን በዬዜና ማሰራጫው የሚያሰማው ውንጀላ፣ እርግማንና  እንዲሁም ዛቻ  የጥፋት ተላላኪው መንጋ  በየመንገዱና በዬመስጊዱ የሚያሰማው ጸረ ፋኖና ጸረ አማራ ጩኸት መመሳሰሉ የቅንጅቱን ትስስር፣ምንጭና መነሻ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ይህንን ድርጊት ሁሉም አገር ወዳድ እምነትና ጾታ ሳይለዬው በጋራ ሊያኮላሸው ይገባል።ይህንን የመካከለኛው ዘመን የጅሃድና  የመስቀል ጦርነት ናፋቂ ሃይሎች የሚያራምዱት ግጭት ሁሉንም መቀመቅ የሚከት፣ሁሉንም አገር አልባ የሚያደርግ እኩይ ተልእኮስለሆነ በጋራ ማክሸፍ ይገባል።ሃይማኖትም ሆነ የጎሳ ማንነት ተከብሮ ሊኖር የሚችለው አገርና ሕዝብ ሲኖር ነው።

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ አላህ አኩበር ማለት ፈጣሪ ትልቅ ነው!፣ፈጣሪ ክቡር ነው! ፈጣሪ ፍቅርና ትህትና ነው!፣ፈጣሪ ይመስገን!ማለት እንጂ ቆንጨራና ዱላ መዘው ለመግደል ሲሄዱ የሚያሰሙት  የደደቦች ፉከራ አይደለም።እኔ የወሎው፣የደሴው ሳላይሽ ልጅ የቤተሰቤን ማንነትና የተወለድኩባትን ደሴ ከተማን  ማንነት ለመግለጽ ቃላት ቢያጥረኝም፣ በዚህም አጭር ጽሑፍ ለማቅረብ ቢያዳግተኝም  ተከታዩን ልጨምርበትና ስለወሎ ከሃያ ዓመት በፊት የጻፍኩትን ግጥም አስፍሬ ላጠናቅቅ።

ከላይ እንደገለጽኩት ቤተሰቤ የሙስሊምና የክርስቲያን እምነት ተከታዮች ናቸው።ሁለቱም እናቴና አባቴ የአምባሰል ነዋሪ ቤተሰብ ልጆች ናቸው።የአባቴ  ቤተሰቦች በአምባሰል አውራጃ  በልዩ ልዩ ቦታዎች ቤተክርስቲያን ያቋቋሙና የመሩ ቀሳውስት ሲሆኑ የእናቴም ቤተሰቦች ማመዶች ከሚባለው ቤተሰብ ውስጥ የተወለደች ናት።በወሎ ውስጥ ለፍቅር ግንኙነትና ጋብቻ ሰውነትና ስነምግባር ብቻ እንጂ ሃይማኖት ብዙም ቦታ ስላልነበረው በወላጆች ፈቃድና ፍላጎት ልጆች ተጋብተው መኖራቸው እንግዳና ባዳ ባህል አልነበረም።  አባቴ በቀጨኔ መድሃኔዓለም መቀበሩንም ጠቅሻለሁ።እናቴም ሌላ ሳታገባ  ቆይታ በከበቧት ሙስሊም ዘመዶቿ ግፊት ሰልማ ስትሞት ሰኞ ገበያ አፋፉ ላይ በሚገኘው የሙስሊም መቃብር ተቀብራለች።ለቀብሯ ባልደርስም ከቀናት በዃላ መቃብር ቦታዋ ድረስ ሄጄ እንባዬን አፍስሼና ሰደቃ አውጥቼ ተመልሻለሁ።እኔንና እናቴን የሚያገናኘን እትብቷ እንጂ ሃይማኖቷ አይደለምና ሃይማኖቷን በመቀዬሯ ቅር አላለኝም፣እኔም ለሃይማኖት ክብር ቢኖረኝም እስከዚህም አይደለሁም።ዱሮ ለፋሲካ በዃላም ለአረፋ የሚያስፈልጋትን እያደረኩኝ በፍቅርና በምርቃት ተሳስረን ኖረናል።ምርቃቷም ከብዙ አደጋዎች የጠበቀኝ ነው ብዬ አምናለሁ።

በልጅነቴ የጥምቀት በዓሉ ሲከበር በተጠመኩበትና ክርስትና በተነሳሁበት የሚካኤል ታቦት ሲወጣና ወደማደሪያው ሆጤ ሜዳ ሲያመራ ከጓደኞቼ ጋር ካባ ለብሼ ቃጭል አንቃጭዬ ያሳለፍኩት ጊዜ ከህሊናዬ የማይጠፋ ማህተም ይዞ ተቀምጧል።።  

ወደ ኢትዮጵያዊነት ቤተሰቤ ሳመራ ፣ እኔ ለአስር ከሲዳማ እናት ለተወለዱ፣ለሁለት ከኦሮሞ አባት ለተወለዱ ሴት ልጆች፣ለስምንት ከአማራ አባቶች ለተወለዱ፣ለአንድ ከትግሬ እናት ለተወለደች፣ለአንድ ከጉራጌ እናት ለተወለደች፣ለአንድ ከአገው አባት ለተወለደ ወንድ ልጅ ፣ከነዚህ ጎን ለጎንም አንዱ ያባቴ ልጅ ወንድሜ ለወለዳቸው ሁለት ሴት ልጆች፤ከነሱም አንዷ ልጁ ከአፋር ተወላጅ ጋር ተጋብታ የአምስት ልጆች እናት ሆናለች።ታናሽ እህቷም ዝርዝሩን ባላውቀውም  በቅርቡ መውለዷንና አዋሳ ከተማ መኖሯን ሰምቻለሁ።በጠቅላላው ለ25  በህይወት ላሉና ለሞቱ የዬጎሳው ተወላጆች ከሆኑ ሚስቶችና ባሎች ከተፈጠሩ የወንድምና  የእህቶቼ ልጆች አጎት ነኝ።እነዚህም ልጆች ከወደዱት ጋር ከተለያዬ ጎሳ ተወላጅ ጋር ተጋብተው ወልደዋል ከብደዋል።ይህ የእኔ የትውልድ የቤተሰብ ሃረግና የህይወት ተመክሮ ታሪክ የብቻዬ ሳይሆን የብዙ ኢትዮጵያውንም ተመሳሳይ ታሪክ መሆኑን አልጠራጠርም። በጣም የማያሳስበኝ ግን አሁን ያለው አገር አጥፊ የጎሰኞችና  የጸረ አንድነት ሥርዓትና እንቅስቃሴ ያሰበው ዓላማ ከተሳካለት እነዚህ ከተለያዩ ጎሳዎች የተወለዱትንና የተዋለዱትን በተለያዬ ቦታ የሚኖሩትን ዘመዶቼን ለመጠየቅ አለመቻሌ ወይም እንደ ባዕድ አገር ዜጋ  ቪዛ እዬጠየኩ መሄዴ ነው።ያ እንዳይሆን ግን በምችለው መንገድና ዘዴ እከላከላለሁ።እስከዛሬም የምጽፈውና ይህም ጽሁፌ የዛው ትግል አካል ነው።

ከዓመታት በፊት ስለወሎ የጻፍኩት የግጥም መልእክት ይህንን ይመስላል።በወቅቱም በከሚሴ አካባቢ ሊቀሰቀስ ታስቦ የነበረውን የአሁኑ አይነት የሃይማኖት ጽንፈኞች  እንቅስቃሴ በማብረድ አስተዋጽኦ አድርጓል፣አሁንም ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ። 

       ወሎ

ከቶ አይሰለችም ስሙ ቢደጋገም፣

ወሎ ያገር ዋልታ፣ወሎ ያገር ቅመም፡፡

የዘር አምባጓሮ ያይማኖት ንትርክ ወሎ መች ለመደ፣

ስሙ ምስክር ነው፤ ፋጤ ገ/ማርያም፣ሰለሞን እንድሪስ፣

አሰለፈች አሊ፣ሙሃመድ ከበደ። 

የዘመዶቹ እምነት ክርስትናና ኢስላም፣

ተጋብተው ወልደዋል፣ባንድነት ኖረዋል በፍቅር በሰላም።

መስጊድና ደብር ባንድ ሰፈር ሲኖሩ፣

ፋሲካና አረፋ ባንድ ላይ ሲያከብሩ፣

የምነት አክራሪዎች ከወሎ ይማሩ።

በወለጋ፣ አሩሲ፣በከፋ፣ ሲዳሞ፣በትግራይ በባሌ

ወሎ ክፍለ ሃገር ይቅረብ በምሳሌ።

በወሎ ክልል ውስጥ በሰላሙ ቦታ፣

ተቀባይ የለውም የምነትና የዘር አክራሪ በሽታ።

በኢትዮጵያዊነቱ ዝምድናው ቢነሳ፣

ቅድመ አያቱ ጎይቶም አጎቱ ዲሳሳ።

በኢትዮጵያዊነቱ በአንድነቱ ጸንቶ፣

ዘር ሳይመለከት ከሁሉም ተጋብቶ፣

የህብረ ብሔር ድር ቤተሰብ መስርቶ።

ከጠባብ እይታ ከክልል ተሻግሮ፣

ኢትዮጵያዊነቱን አክብሮ አስከብሮ፣

ወሎዬ ይኖራል ከሁሉም ተባብሮ።

የነነዬ ድቤ የነሞሃይ አገር፣

የሸህ የቀሳውስት የወልዮች አገር፣

ወሎ በቅጥ ያውቃል ተከባብሮ መኖር።

የጊሸኗ ማርያም፣ ቅዱስ ላሊበላ፣አቡዬ፣ ተክልዬ፣

አብዱዬ ጀላሌ መርሳ አባ ገትዬ፣

መማጸኛው ናቸው ለእስላም ለክርስቲያን፣ ለሁሉም ወሎዬ።

የጋርዮሽ አገር የክርስቲያን የስላም፣

ክፉ ነገር እንጂ ወሎ ሰው አይጠላም።

እጁ አይታጠፍም እንግዳ አይዘነጋም፣

አህሪቡ ግቡ ነው ወሎ ቤት አይዘጋም።

ያለውን ጀባ ነው በቁጠባ አያምንም፣

ተካፍሎ ይበላል ተከፋፍሎ አይኖርም።

ታሪክ ቢመሰክር ትውልድ ቢናገር፣

የቆንጆ ማህጸን የባህል ማህደር፣

ከቶ የት ይገኛል ወሎን ያህል አገር?

መለስ ብለን ብናይ ታሪክ ወደዃላ፣

ወሎ ብዙ ይዟል እንደነ ውጫሌ እንደነ መቅደላ።

ለሃብተ ጊዮርጊስ ለምዬ ምኒልክ፣

የዲፕሎማሲው የፖለቲካው መስክ፣

የውጫሌ ሜዳ የውይይቱ መድረክ።

የጠላት አሻጥር አንቀጽ አስራ ሰባት የተጋለጠበት፣

የነጻነት ደወል ለተደወለበት፣

ለጥቁር አርነት ችቦ ለበራበት፣

ለአድዋ ጦርነት ምክንያት የሆነበት፣

የውጫሌ ሜዳ ይነሳ ይወደስ፣

ትውልድ እንዳይረሳው በታሪክ ይዳሰስ።

የመቅደላ ጎራ የመቅደላ ዳገት፣

አንበሳው ቴዎድሮስ የተፋለመበት፣

አዋግቶ ተዋግቶ እጅ ያልሰቀለበት፣

ግርማ ሞገስ ለብሶ ሞት የመረጠበት።

የመቅደላ ምሽግ የመቅደላ ዋሻ፣

ወኔ ሚቀሰቅስ ጀግና ማስታወሻ።

የምቅ ሃብት ጓዳ የጨዋ ሕዝብ አገር፣

ወሎ ብዙ ይዟል ጥሩ ጥሩ ነገር፣

ከቶ አያልቅበትም ቢነገር፣ቢነገር፣ቢነገር፣ቢነገር…

ጥማቴ ቢጠና ብዙ ፈሳሽ ጠጣሁ፣

እንደ ደሴ ውሃ፣እንደ ሳላይሽ ምንጭ፣የሚጥመኝና የሚያረካኝ አጣሁ።

እንደ ቦሩ ሜዳ እንደ ሩጋ ዳገት፣

እንደ ቦርከና ወንዝ እንደ ጦሳ አቀበት፣

መገን የወሎ ሰው፣

ደግነት አያንሰው፣ፍቅር አያልቅበት።

ትንሹ ትልቁን መች ይዘነጥላል፣

እታለም፣ጋሽዬ

አይዋ፣ ክንድዬ

እያለ ሲጣራ ካፉ ማር ጠብ ይላል።

ክራር ቢደረደር ማሲንቆ ቢመታ፣

አንች ሆዬ ለኔ፣ አረ ባቲ ባቲ፣አምባሰል ትዝታ፣

የቅኝቱ ጳጳስ የኪነቱ ጌታ፣

ወሎ ባህሉ ነው እንግዳ መቀበል ቁም ነገር ጨዋታ።

በደቡብ ገብቼ በሰሜን ወጣሁ፣

በምስራቅ ገብቼ በምዕራብ ወጣሁ፣

እኔስ እንደ ወሎ የጋራ አገር አጣሁ።

ማዕዛው የሚያውድ ባሪቲ ባሽኩቲ፣

ኮመቦልቻ፣ ከሚሴ፣ አሳይታና ባቲ።

ዋድላና ደላንታ ኩታበር አምባሰል፣

እንዲያ ነው አስተዋይ ፣በተፈጥሮ አዋቂ ሳይማሩ መብሰል።

ወረኢሉና ተንታ ሳይንትና የጁ፣

ተፈጥሮ የሰጠው ሁሉንም በደጁ።

ውሃ ባይጠጣ እህል ባይበላ፣

የመንፈስ ምግብ ነው የነድንቅዬ አገር ላስታ ላሊበላ።

ደሴ መሃል አገር የቆንጆ መዲና፣

የልባሞች አገር ከላላ ቦረና።

ሃይቅና ወልድያ ጃሪ ወረባቦ፣

ፍቅር መላበሻ ደርቦ ደራርቦ።

እራያና አዘቦ ቆቦና ሰቆጣ፣

ግንባሩን አያጥፍም የመጣው ቢመጣ፣

መሞቱን ይመርጣል በዘር ተሸንሽኖ ኢትዮጵያን ከሚያጣ።

ቦሩና ውጫሌ ቀለምና ሩጋ፣

አቤት አበቃቀል ያም ሸጋ ያም ሎጋ።

ያመነውን አምኖ፣

የሆነውን ሆኖ፣

የሠራውን ሰርቶ፣

የሸጠውን ሸጦ፣የገዛውን ገዝቶ፣

በአማርኛ ጽፎ በአማርኛ አውርቶ 

ሕዝብ የሚኖርበት ተግባብቶ ተስማምቶ፣

ዘር ሃይማኖት አይልም ወሎና መርካቶ።

አማርኛው የኔ፣

ኦሮሞኛው የኔ፣

አርጎብኛው የኔ፣

አፋርኛው የኔ፣

አገውኛው የኔ፣

ትግርኛውም የኔ፣

ክርስትናው የኔ፣

እስልምናው የኔ፣

ሁሉም ክልል የኔ፣

ሁሉም ባህል የኔ፣

ያም እኔ ያም የእኔ፣

ያገር ልጅ ወገኔ፣

በጣም ያኮራኛል ንጹህ ኢትዮጵያዊ ወሎዬ መሆኔ።

አገሬ አዲስ   

  ሰኔ 1989ዓ.ም.(June 1997)

ከሰሞነኛው የወያኔና የኦነግ ወረራ ጋር በተያያዘ  ይህንን ብያለሁ።

የወሎን ገራገር ድንቅዬ የሰው ዘር፣

በጎሳና በእምነት ተራ  በመመንዘር፣

ሥልጣኑን ጨብጠው በመግደል በማሰር፣

እቅድ ዘርግተዋል አይ የጅሎች ነገር!

ታጋሽ ደግነቱን ከጅልነት ቆጥረው፣

የኢትዮጵያን ባለቤት አማራን  ገፍትረው፣

ከመሬቱ አባረው፣ባዕድ አገር ፈጥረው፣ 

እነሱ ሊኖሩ ኢትዮጵያን ሰባብረው።

ጅሎች ተነስተዋል ሊያጠፉት ተባብረው።

የሚያስተምር ምሁር መካሪ ካላቸው፣

የሚያስቡት ነገር አይሆንም ፣ቅዠት ነው፣እብደት ነው  በላቸው፤

አጥፍቶ መጥፋት ነው ወይም ባርነት ነው ትርፋችሁ በላቸው፤

የፈጸማችሁት ለተተኪው ትውልድ የታሪክ ማፈሪያ ተግባር ነው በላቸው። 

እጆቹን ዘርግቶ፣ቤት ለእንግዳ ብሎ በተቀበላችሁ፣

ምን አይነት ምላሽ ነው፣እስኪ ተመልከቱት

የሰው ልጅ ህሊና  አይምሮ ካላችሁ? 

ማመስገን ሲገባ ለዋለው ውለታ፣ 

በቀዬው መጥታችሁ ከመኖሪያው ቦታ

ህጻን ሽማግሌ ሳይቀር አረዳችሁ፣

ንብረቱን ጥሪቱን በሃይል ዘረፋችሁ፣

መኖሪያ ጎጆውን አመድ አረጋችሁ።

እንስሳት ሳይቀሩ አርዳችሁ በላችሁ፣የተቀሩትንም በጥይት ቆላችሁ፣

በጠላት ተልእኮ ወገንና ሃገር ሰላም አሳጣችሁ፣

የአላህና ነቢን  ስም እዬጠራችሁ፣

ሕዝብ አሸበራችሁ ህጻን አረዳችሁ፣

መስጊድና ደብር በሳት አጋያችሁ፣

ለፈጸማችሁት አምላክ ይፍረዳችሁ።

የተረሳ መስሎ ጥቃት ቢውል ቢያድርም፣

በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም። 

ለሁሉም ጠቃሚው የሚበጀው ነገር፣

እንደጥንቱ ጊዜ ተሳስቦ በመኖር

ጎሰኛን ሥርዓት እስከነአስተሳሰቡ እንዳያንሰራራ፣

ከነስራስሩ መንጥሮ በመንቀል

ኢትዮጵያዊነትን በጠንካራ ዋልታ ሰንደቋንም መትከል።   

ሚያዝያ 24 ቀን 2014 ዓም(02-05-2022)

                            ኢትዮጵያ ከጎሳና ከሃይማኖት በላይ ናት!!

                 ኢትዮጵያ በነጻነትና በአንድነት ለዘላለም ትኑር!!

Filed in: Amharic