>

የጎንደሩ የሀይማኖት ግጭት ( ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ )

የጎንደሩ የሀይማኖት ግጭት

ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ

ከጥቂት መንግስታዊ የግጭት ጥንሰሳዎች ውጭ ሙስሊም እና ክርስቲያኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት ተከባብረው የኖሩ ማህበረሰቦች ናቸው፡፡ በዘመናችን እንዳየነው የጎንደሩ የሀይማኖት ግጭት የመንግስት እጅ እንዳለበት ለመረዳት አያዳግትም፡፡ የአማራን ህዝብ አንድነት ለመከፋፈል እና ለህዝባችን ዋልታ የሆነውን ኃይል (ፋኖን) ትጥቅ ለማስፈታት መንግስት በርካታ ዘዴዎችን ሲያማትር እንደቆየ ይታወቃል፡፡ መፍትሄ አድርጎ የተጠቀመበት መላ ምት የሀይማኖት ግጭትን ጠምቆ ፋኖን ትጥቅ ማስፈታት እና የህዝቡን አንድነት ማዳከም ነው፡፡

ፋኖ፣ ዘርማ እና ቄሮ በ2010ዓ.ም. ለውጡ እንዲመጣ ተጋድሎ ያደረጉ የለውጥ አቀንቃኞች ሲሆኑ ጠቅላዩ በፋና ቴሌቪዥን ህዳር 22/2012ዓ.ም. ባደረጉት ንግግር ለለውጡ የፋኖን፣ የዘርማን እና የቄሮን ተጋድሎ አድንቀው እነዚህ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ሀውልት እንደሚቆምላቸው ዲስኩር ቢጤ ሰንዝረው ነበር፡፡ 

የትህነግ አማፂያን ኃይሎች የአማራን ክልል በወረሩበት ጊዜ እና መከላከያ በተወጋበት ስዓት  ፋኖ እና የአማራ ልዩ ኃይል ባደረጉት ተጋድሎ እና በከፈሉት መስዋዕትነት ዛሬ ላይ ልንደርስ ችለናል፡፡ የፋኖ እና የአማራ ልዩ ኃይል የወጊያ ብቃት፣ጀግንነት እና ተጋድሎ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና በአውደ ወጊያው የነበሩ ምስክሮች ናቸው፡፡ ጠቅላዩም በጊዜው ምስክርነታቸውን ሰጥተው ነበር፡፡  

ስለዚህ ህዝቤ ሆይ ስማኝ!! የሚደረገውን የፖለቲካ ሸፍጥ ተረድተህ ቆም ብለህ ጉዳዩን በአንክሮ መመርመር እንጅ ወንድም በሆኑት የክርስቲያኖች/የሙስሊሞች የአምልኮ ቦታ ላይ ጥቃት መሰንዘር የመንግስት አጀንዳ አስፈፃሚ ሁኖ መገኘት ነው፡፡ በመካከላችን መወጋገዝ፣ መለያያት እና ለግጭት መሯሯጥ አይበጀንም፡፡ አሁንም ቢሆን በአማራ ልዩ ኃይል እና በፋኖ መካከል ግጭት ሊጠነስሱ እንደሚችል መረዳት ያስፈልጋል፤ እንዲሁም በጎጃም፣ በጎንደር፣ በወሎ እና በሸዋ አማራ መከከል መለያየት እና አለመግባባት ሊፈጥሩ እንደሚችሉም መጠርጠር ተገቢ ነው፡፡ የአማራ አንድ መሆን ለብሄርተኞች ውጋት ስለሚሆንባቸው አሁንም ሌላ ሸፍጥ ከመጥመቅ አይቦዝኑም፡፡ 

አማራ የሚሸረብበትን ተንኮል እና ሴራ ተረድቶ ያለ ምንም ልዩነት በአንድ ላይ በመቆም እና አክራሪ ብሄርተኛ ያልሆኑ ኢትዪጵያዊያንን ሀይሎች ከጎኑ አሰልፎ ህልውናውን ሊታደግ እና የኢትዮጵያን ትንሳኤ ሊያበስር ይገባል፡፡  

ኦነግ ሸኔ ተብሎ የዳቦ ስም የተሰጠው በኦሮሞ ብልፅግና ድጋፍ የሚደረግለት ንፁኃንን በመግደል የሚታወቀውን ነፍሰ ገዳይ ቡድንን ታቅፎ የያዘ መንግስት ለምን በነፃነት ታጋዬች በፋኖ ላይ አመረረ? ከሞት ከተረፉት ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ስርዓተ መንግሰቱን ያቆመው የአማራ ልዩ ኃይል እና የፋኖ ተጋድሎ እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ውለታ ቢስ መሆን ያስተዛዝባል፡፡

Filed in: Amharic