>

መች በደረሱ እያልን የሚናፍቁን በዓላቶቻችንን እንድንፈራቸው ሆነ እኮ...!!! (ያሬድ ሐይለማርያም)

መች በደረሱ እያልን የሚናፍቁን በዓላቶቻችንን እንድንፈራቸው ሆነ እኮ…!!!
ያሬድ ሐይለማርያም

 

*….  በኢድ ቀን በመስቀል አደባባይ ዙሪያ የሚገኙትን ማለትም፣ ሃዲያ ሱፐር ማርኬት፣ የኢዜማ ቢሮ፣ የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት፣ ሲንቄ ባንክ፣ ወጋገን ባንክ 2 ብራንቾች፣ ወጋገን ባንክ ኤቲኤም፣ የኢትዮጵያ መድኅን ድርጅት፣ rendez – vous፣ LA patissere cafe፣ ቤልሞን ካፌ፣ ሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየሙ ከሁለት መኪናዎቹ ጭምር፣ ከቦሌ ወደ ስታዲየም ያለው እካፋይ የመንገድ ብረት፣  የመስቀል አደባባይ የተወሰኑ መቀመጫ ወንበሮች፣ የመስቀል አደባባይ ፖርኪንግ መግቢያ፣ በመስታውት የተሰራ ቤት ሞደን ሴራሚክ፣ ብሔራዊ የጀግኖች ሕጻናት አምባ፣ ኢትዮ ባስ ትኬት ቢሮ፣ አባይ ባስ ትኬት ቢሮ፣ መስቀል አደባባይ የትራፊክ ማረፊያ፣ የመስቀል አደባባይ ፖሊስ ኮሚኒቲ ቢሮ እና ሌሎችንም እንዲህ ነበር ያወደሟቸው።
ኸረ ወገን እንደ ሀገር ምን እየሆንን ነው? ምን ነካን?
ባዘቦቱም፣ በባዕላትም ቀን ደስታና ሰላም ከእኛ እየራቁን፣ እርስ በርስ ተፋጠን እንዴት ይዘለቃል? አውድ አመቶችን ከደስታና ከፈንጠዝያ ይልቅ በውጥረት፣ በግጭትና ሁከት ማሳለፍ ከጀመርን ከራረምን እኮ። መች በደረሱ እያልን የሚናፍቁን በዓላቶቻችንን እንድንፈራቸው ሆነ እኮ። አዛውንቶች፣ አቅመ ደካሞች፣ እናቶችና ሕጻናት ልጆች የክት ልብሳቸውን ለብሰው፣ አገር አማን ነው ብለው ባዕላትን በአደባባይ ሊያከብሩ ሲወጡ እንዲህ ያለ ወከባ፣ ትርምስ፣ ሁከትና ግጭት ምን የሚሉት ነው? በጥምቀት የተፈጸመውን አይነት ነውር በኢድ ከደገምነው ጥልቅ ችግር ውስጥ ነን ማለት ነው። ኸረ ወደቀልባችን እንመለስ። በምክክርና በውይይት የማይፈታ ምድራዊ ችግር የለም። ለሰላም እና እርቅ መረታት ማሸነፍ ነው። በሁሉም ሃይማኖት ጎራ ውስጥ ያላችሁ ወጣቶች ተረጋጉ፣ ሰከን በሉ። የሃይማኖት አባቶች የምትመሩትን ምዕመን አንድ በሉ። የእረኝነት ተግባራችሁን ተወጡ። የጸጥታ ሃይሎችም ሰላም ስታስከብሩና አጥፊዎችን ለፍርድ የማቅረብ ሥራችሁን ስታከናውኑ የምትወስዷቸው እርምጃዎች ከልክ ያለፋ፣ ያልተመጣጠኑና ግጭቶችን የሚያባብሱ አለመሆናቸውን አረጋግጡ።
Filed in: Amharic