>

  ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እውነት ከመናገር ውጭ ሌላ ወንጀል የለበትም ...!!! (ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ)

ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እውነት ከመናገር ውጭ ሌላ ወንጀል የለበትም …!!!

ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ
*….. ጋዜጠኛው ታሰረ የሚለው መረጃ እውነት ከሆነ መንግስት ለሁለተኛ ጊዜ ተሸነፈ ማለት ነው። አንደኛው ለምን እውነትን ዘገብህ ብሎ ከኢሳት እንዲባርረ ሲያደርገው ሲሆን ሁለተኛው አሁን እየተባለ እንዳለው በእርግጥም ጎበዜን አፍነው የወሰዱት የመንግስት ሀይሎች ከሆኑ ማለት ነው።
 
ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ የራያ ልጅ ነው፣ በዚህም ምክንያት በጦርነቱ ወቅት ከራያና አካባቢው ወቅታዊውን ሁኔታ የሚገልጽ መረጃ ይደርሰው ነበር። ይህን እውነት ለማረጋገጥ ወደ ስፍራው አቀና፣ በጆሮው የሰማውን በአይኑ አይቶ አረጋገጠና እውነታውን ያውም በልኩ አድርጎ ሁሉም ሰው እንዲያውቀው በራሱ የፌስ ቡክ ገጹ ላይ ለጠፈው።
ይኸኔ ከብልጽግና ጉያ ተወሽቆ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይንና ጆሮ ነኝ ሲል የነበረው የኢሳት ሀላፊዎች ተከፉ። እናም በግል የፌስ ቡክ ገጽህም ቢሆን መንግስትን እንዲህ በድፍረት የሚያጋልጥ ዘገባ የምታወጣ ከሆነማ ከእኛ ጋር መቀጠል አትችልም ብለው አባረሩት። በሙያው የሚተማመነው ጋዜጠኛ ጎበዜም ምንም ሳይደናገጥ ስራውን አጠናክሮ ቀጠለ።
ከእኛ ቴሌቪዥን ጋር በመሆንም በዛ ቃውጢ ወቅት በአፋር ክልል ጭፍራንና አካባቢውን አቆራርጦ ዞብል በመግባት ጉራ ወርቄ ድረስ ሄዶ የራያ-ቆቦ ወረዳ ሕዝብ ለትህነግ ታጣቂዎች የጎን ውጋት እንደሆነባቸው በግልጽ አሳየን። ይህም ሆኖ የመንግስት ድጋፍ ባለመኖሩ ሚሊሻውና ፋኖው ብቻ ሳይሆን የአካባቢው ሕዝብ በከፋ ችግር ውስጥ እንደሚገኝም አጋለጠ።
ከራያ እንደተመለሰም በአዲስ አበባና አካባቢው የሚገኙ የራያ ተወላጆች ተሰባስበን በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ለመርዳት ኮሚቴ እንዲቋቋም ሲደረግ እሱ የኮሚቴው ሰብሳቢ እንዲሆን ተደረገ። ትንሽ ቆይቶም ጊዜያዊ ኮሚቴው ወደ ቋሚ ማህበርነት ሲቀየርም የራያ ሰላምና ልማት ማህበር ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመረጠ።
በቅርቡ ደግሞ ሙያውን ተጠቅሞ የአማራ ፋኖዎችን ሚና አጉልተው የሚያሳዩ ዘገባዎችን በተከታታይ ማውጣት ጀመረ። ከዛም አልፎ የአማራ ድምጽ በሚል ስያሜ በማህበራዊ ሚዲያው የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ጥረት ማድረጉን አጠናክሮ ቀጠለበት። እንግዲህ የአሁኑ እስር እነዚህን ሁለገብ ጥረቶቹን ለማንኮላሸት መሆን አለበት።
እናም እውነተኛ የአማራ ልጆች በአጠቃላይና የራያ ሰላምና ልማት ማህበር ስራ አስፈጻሚዎችና አባላት ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ የሚገኝበትን ቦታ ለማወቅ ጥረት ከማድረግ ጀምሮ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቅ የሚቻለውን ያህል ግፊት ማድረግ ይኖርባቸዋል። እስካሁን ባለኝ መረጃ መሰረት ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እውነትን ከመግለጥ ውጭ ሌላ ወንጀል አልሰማሁበትም።
Filed in: Amharic