>
5:31 pm - Tuesday November 12, 2385

ለአስተዳዳሪዎቻችሁ ያላችሁን  ታማኝነት ለመግለጽ ወገንን ማጥቃት እጅግ አጸያፊ ተግባር ነው...! አሳዬ ደርቤ

ለአስተዳዳሪዎቻችሁ ያላችሁን  ታማኝነት ለመግለጽ ወገንን ማጥቃት እጅግ አጸያፊ ተግባር ነው…!!

አሳዬ ደርቤ

*… ጃልመሮና ደብረ ጽዮን የደህንነት መሥሪያ ቤቱ ባለሥልጣን ሆነው ቢሾሙ እንኳ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ካዘጋጁት ሰነድ የላቀ የዘመቻ እቅድ ጽፈው ፋኖ ላይ ሊዘምቱ አይችሉም።
*…. ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ይቅርና ከጥቂት ወራት በፊት በአማራ ሕዝብ ላይ ያደረሳችሁትን ግፍ ለመጻፍ ሳስብ ዘልዛላ ታሪካችሁ እረዝሞ ከሊዮ ቶልስቶይ መጽሐፍ በላይ ግዙፍ ገጽ ያለው ይሆንብኛል፡፡ ታላቁን ሕዝብ እንዴት እንዳዋረዳችሁት ሳሰላስል ፋኖን ለመመታት ማሰባችሁ ቀርቶ አመራር ሆናችሁ መቀጠላችሁ ያስገርመኛል፡፡
ቆይ እኔ እምለው
➔የአማራን ሕዝብ እንደ ሕዝብ የሚያወድም ወራሪ ጦር ሲመጣ ሕዝቡን በዞን ከፋፍላችሁ፣ የድርጅታችሁን ገንዘብ ተከፋፍላችሁ፣ ለቤተሰቦቻችሁ እና ለእራሳችሁ የአውሮፕላን ትኬት ገዝታችሁ… ማምለጫ ቀደዳ ስትፈልጉ የነበራችሁ ጉዶች ዛሬ ላይ ፋኖን ለማጥፋት የሚያስችል ሰነድና እቅድ ለማዘጋጀት የበቃችሁት የአማራን ሕዝብ ምን ያህል ብትንቁት ነው?
➔የአማራ ወጣት የትጥቅ ጥያቄ ሲያቀርብ እንቢ ብላችሁ መጋዘን ሙሉ ጦር-መሣሪያ ለወራሪው ሃይል ጥላችሁ እንዳልሸሻችሁ… በክትክታ ዱላ ማርኮ የታጠቀን ፋኖ ትጥቅ ለማስፈታት የደፈራችሁት ስንት ዳብል ውስኪ ብትጠጡ ነው?
የአማራን ሕዝብ ምን ያህል ብትጠሉት ነው?
➔መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ፈጽመው ነፍሱን እና ትጥቁን የሚቀሙ፣ የዙፋን ጥያቄያቸውን ንጹሐን በመግደል የሚገልጹ እልፍ አእላፍ አማጺያን ባሉበት ሁኔታ… ከሠራዊቱ ጎን ቁሞ አብሮ ሲሞት የነበረውንና ወደፊትም አብሮ ለመሠዋት የተዘጋጀውን ፋኖ ከመከላከያ ጋር ማጋጠም የፈለጋችሁት የአማራን ሕዝብ ምን ያህል ብትጠሉት ነው?
ከትሕ-ኦነጎች ምን ያህል ገንዘብ ብትቀበሉ ነው?
➔በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጭ የሚኖረው አማራ በኦ-ያኔ እና በሸኔ ከበባ ውስጥ ወድቆ እየተሰቃዬ ባለበት ጊዜ… ሌሎች አካባቢዎች ላይ ወረራ በሚፈጽሙና ንጹሐንን በሚያወድሙ ኃይሎች ፈንታ ክልሉን የመከላከል ተግባር ይዞ የተደራጀውን ፋኖ ለማክሰም የሚያስችል ሰነድ ተቀብላችሁ ለማስፈጸም የበቃችሁ ከትሕ-ኦነጎች ምን ያህል ገንዘብ ብትቀበሉ ነው?
የትኛው የአማራ ሕዝብ ‹‹ፋኖ ስጋት ስለሆነብኝ አጥፉልኝ›› ብሏችሁ ነው?
➔ይሄስ የጥፋት እቅድ በፋኖ ላይ የተዘጋጀው የትኛውን ክልል ወርሮ ነው? የትኛውን የመንግሥት ሠራዊት አጥቅቶ ነው? የስንት ባለሥልጣናትን ሕይወት ነጥቆ ነው? የትኛው የአማራ ሕዝብ ‹‹ፋኖ ስጋት ስለሆነብኝ አጥፉልኝ›› ብሏችሁ ነው?
እርግጥ በፋኖ ሥም የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ አጭበርባሪዎች በገዛ ሕዝባቸው ላይ አንዳንድ ጥፋት ሊፈጽሙ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን በውጫዊ ኃይሎች የትጥቅ ድጋፍ ኢትዮጵያን የማፍረስና መንግሥትን የመገርሰስ ዓላማ አንግበው በምድሩ ላይ ከተቀፈቀፉት አማጺያን ጋር ሲወዳደር የእነዚህ ኃይሎች ጥፋት መከላከያን ለማዝመት ቀርቶ የአገርም ሆነ የመንግሥት ስጋት ሊሆን አይችልም፡፡  እናንተ ግን በአማራዎች ወንበር ላይ የተቀመጣችሁ የትሕ-ኦነጎች አሽከር በመሆናችሁ የምስራቅ አማራን ፋኖን በመምታት ታማኝነታችሁን መግለጽ ፈለጋችሁ፡፡
አንድ ነገር ልንገራችሁ…?
በአማራ ሕዝብ ላይ እንደ ሠራችሁት ወንጀል ቢሆን ኖሮ ፋኖ ነበር ሰነድ አዘጋጅቶ ወደ እናንተ መምጣት ያለበት፡፡ መከላከያ ሠራዊቱም ቢሆን ትናንት አብሮት ሲሞት ከነበረው ፋኖ ላይ በመተኮስ ፈንታ ‹‹በጓዶቼ ሞት ላይ ተደራድራችሁብኛል›› ብሎ እናንተን ነበር መውቀስ የነበረበት፡፡
በተረፈ
ፋኖ ላይ የጀመራችሁትን ዘመቻ ተግባራዊ ማድረግ የምትችሉት የአማራን ሕዝብ ከሕልውና ስጋት ነጻ ያደረጋችሁ ቀን ብቻ ነው፡፡ ወይም ደግሞ መላው አማራን ማጥፋት የቻላችሁ ቀን ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን የምትጀምሩት እንጂ የምትጨርሱት ዘመቻ አይኖራችሁም፡፡ እናም ፋኖን ለማጥፋት የነደፋችሁትን እቅድ መሰረዝ ካልቻላችሁ ገመድ ሆኖ የእናንተ አንገት እንደሚሸመቀቅ ጥርጥር የለውም፡፡
Filed in: Amharic