>

ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም በዛሬዋ ዕለት ...!!!! (ታሪክን ወደኋላ)

ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም በዛሬዋዕለት …!!!!

ታሪክን ወደኋላ

ከ 33 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን በከፍተኛ የጦር ሹማምንት  በኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም ላይ በአዲስ አበባና በአስመራ ላይ የተካሄደው ደም አፋሳሽ መፈንቅለ መንግስት  የተሞከረበት ዕለት ነበር።

የአብዮታዊው ሰራዊት ጥቁር ቀን)

(ያልተሳካና ደም አፋሳሽ የነበረው መፈንቅለ መንግስት ሙከራ)

ይህች ቀን በተለይም  በአዲስ አበባ  እና በአስመራ የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች እቅዳቸውን ለማስፈፀም የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን ለጉብኝት ከሀገር መውጣት ተከትሎ እንቅስቃሴ የጀመሩበት ነበረች።

የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች በግንቦት 8 ቀን አዲስ አበባ አምባሳደር አካባቢ በሚገኘው የመከላከያ ሚኒስቴር  ህንፃ ውስጥ በኢታማጆር ሹሙ ሜጀር ጀነራል መርዕድ ንጉሴ መሪነት የዕቅዱ አተገባበር ላይ ውይይት ይዘዋል።

ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም  ወደ ምስራቅ ጀርመን ለጉብኝት ለመጓዝ በኢትዮጵያ  አየር መንገድ አውሮፓላን ውስጥ ገብተዋል። የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች ኮ/ል መንግስቱን  ለመገልበጥ  መከላከያ ሚኒስቴር መ/ቤት የዕቅድ አፈፃፀም ውይይት ላይ  የተለያዩ እቅዶች ቀርበው ነበር።

አንደኛው “ኮሌኔሉን  በአየር ላይ እንዳሉ በአየር ሃይል ጀቶች ይመቱ /እናጋያቸው አሊያም በአየር ኃይል ጀቶች ተገደው አስመራ አርፈው በቁጥጥር ስር ይዋሉ በሚሉና ” ኮሌኔሉን የያዘቸው አውሮፕላን ሳትመታ እሳቸው ከሀገር ሲወጡ ግልበጣው ይፈፀም ፤ ምክንያቱም አብረዋቸው ያሉ ንፁኃን ሲቪሎች መጎዳት የለባቸውም ፤ የአየር መንገዳችን በጎ ገፅታ መጉደፍ የለበትም ”  በሚሉ ሀሳቦች የጦሩ ከፍተኛ መሪዎች መሃከል  አለመግባባት ነበረ። በዚህ መስማማት ባጣው ውይይት መሃል ርዕሠ ብሔሩን ያሳፈረው አውሮፕላኑ የኢትዮጵያን የአየር ክልል ለቆ ወጣ።

አዲስ አበባ ያሉት የጦር መሪዎች እርምጃ ሳይጀምሩ ቀደም ብሎ በታሰበው የአፈፃፀም እቅድ መሰረት አስመራ የነበረው  በሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ደምሴ ቡልቶ የተመራው ኃይል ከአዲስ አበባ በተላከለት መልእክት መሠረት ኮ/ል መንግስት እንደተወገዱ ስለተነገረው እሱ መረጃ ይዞ  እቅዱን ወደ ማስፈፀሙ ገብቶ መንግስቱ ኃይለማርያም ከስልጣን መውረዱን በአስመራ ራዲዮ አስነገረ።

አዲስ አበባ ያለውንም እንቅስቃሴ ለመርዳት እና ቁልፍ ቁልፍ የተባሉ ቦታዎች (ራዲዮና ቴሌቭዥን ጣቢያ ፣ አየር ማረፊያ ፣ ቴሌኮሚኒኬሽን፣ የጦር ክፍሎች ፣…)  ለመቆጣጠር እንዲቻል መቺ ኃይል የሆነውን ኤርትራ የነበረውን 102ኛ አየር ወለዱን በሁአሠ ም/አዛዥ በነበሩት ሜ/ጀነራል ቁምላቸው ደጀኔ ዋና መሪነትና በኮ/ል ካሳዬ ታደሰና በኮማንደር ሀይለጎርጊስ ማማስ አስተባባሪነት ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ ላከ ።

ይሁን እንጂ በኋላ ከዳ በተባለለው የደህንነት ሚንስትሩ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደስላሴና በሻንበል መንግስቱ ገመቹ በሚመራው የልዩ ጥበቃ ብርጌድ  አማካኝነት የአዲስ አበባው መፈንቅለ መንግስት ሙከራው ከሸፈ። ኮሎኔል መንግስቱም ከምስራቅ ጀርመን ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።

የአዲስ አበባው መፈንቅለ መንግስቱ በተለያዩ ምክንያቶች ከጥቂት ሰአታት በኃላ ሲከሽፍ ኢታማጆር ሹሙ ሜጀር ጄኔራል መርዕድ ንጉሴ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ለብሰው መከላከያ ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ራሳቸውን በገዛ ሽጉጣቸው አጠፉ ።

የአየር ኃይል አዛዡ ሜ/ጀነራል አመኃ ደስታም በተመሳሳይ ሁኔታ እራሳቸውን ገደሉ ። የእንዱስትሪ ሚኒስቴር የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ፋንታ በላይ ከሙከራው በኋላ ተሰውረው በደህንነት ሃይሎች ሲፈለጉ ቆይተው ከሙከራው አራት ቀን በኋላ መከላከያ ሚኒስቴር ግቢ ውስጥ ተሸሽገው ተገኙ ።

ጄኔራል ፋንታ ከተያዙ ከቀናት በኋላ እዚያው የታሰሩበት ማዕከላዊ ምርመራ ግቢ ውስጥ ባልታወቀ ምክንያት ተገደሉ።

ሌላው የመፈንቅለ መንግስቱ ዋና ጠንሳሽ የዘመቻ መምርያ ኃላፊ የነበሩት ሜ/ጀነራል አበራ አበበ ጠንሳሾቹን ለማነጋገር የመጡትን የወቅቱን የመከላከያ ሚኒስቴር የነበሩትን ሜ/ጀነራል ኃ/ጊዮርጊስ ሀ/ማርያምን በሽጉጥ አቁስለው ከጊቢው በአጥር ተንጠላጥለው አመለጡ ። ቀሪ ጀነራል መኮንኖች መፈንቅለ መንግስቱን ለማክሸፍ በሻንበል መንግስቱ ገመቹ በተመራው የልዩ ብርጌድ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ ።

የሁአሠ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ የመሩት የአስመራው የመፈንቅለ መንግስቱን ከሶስት ቀናት ሙከራ በኃላ  መክሸፋ ተከትሎ የ102 ኛ አየር ወለድ ወታደሮች ጀነራል ደምሴን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ መኮንኖችን በአሰቃቂ ሁኔታ  በጥይት እየደበደበና በጭካኔ እናነቀ በአሰቃቂ መንገድ ፈጃቸው።

የዘመቻ መምሪያ ዋና ኃላፊ የነበሩት ሜጀር ጄኔራል አበራ አበበ መፈንቅለ መንግስቱ ከተካሄደበት መከላከያ ሚኒስቴር ግቢ አጥር ዘሎ አምልጠው ለወራት ሲፈለጉ ከቆየ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኝ የዘመዱ ቤት ውስጥ ተደብቀው ቆይተው በጥቆማ ፖሊሶች ደርሰውባቸው ቤቱ ሲከበብ ጄኔራል አበራ አጥር ዘሎ ለማምለጥ ሲሞክሩ በተተኮሰባቸው ጥይት ተገደሉ ።

መቺ ሀይል ከአስመራ በአንቶኖቭ ጭነው አዲስ አበባ የመጡት ሜ/ጀነራል ቁምላቸው ደጀኔ የነገሮች መበላሸትና የግንኙነት መስመር ስለተቋረጠባቸው ተሠውረው በመቆየት ከሀገር በሙውጣት በመጨረሻ አሜሪካን ገቡ ። ዋና ተዋናይ ሆነው ብቸኛ በህይወት የተረፋ ጀነራልም መኮንንም እሳቸው ብቻ ናቸው።

ከሁለተኛው አብዮታዊው ሰራዊት

ዋና አዛዥ ሜ/ጀነራል ደምሴ ቡልቱ ጋር በአስመራ ከተማ በ102ኛ አየር ወለድ ክፍለ ጦር ህይወታቸው በአሰቃቂ ና በዘፈቀደ ሁኔታ ያጡት ስመጥር ጀነራሎች እና ሌሎች መኮንኖች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

1. ብ/ጀነራል አፈወርቅ ወ/ሚካኤል = የኤርትራ ክ/ሃገር የአስቸኳይ ጊዜ ዋና አስተዳዳሪ

2. ብ/ጀነራል ታዬ ባላኪር = የኤርትራ ክ/ሃገር  አቢዮታዊ ፖሊስ ዋና አዛዥ

3. ብ/ጀነራል ታደሰ ተሰማ = የሁአሰ ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ

4. ብ/ጀነራል ወርቁ ቸርነት = የሁአሰ ፖለቲካ መምሪያ ኃላፊ

5. ብ/ጀነራል ንጉሴ ዘርጋው = የአስመራ አየር ኃይል ዋና አዛዥ

6. ብ/ጀነራል ከበደ መሀሪ = የሁአሰ ድርጅት መምሪያ ኃላፊ

7. ብ/ጀነራል ተገኔ በቀለ = የኤርትራ ክ/ሃገር የአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር ዘመቻ መኮንን

8. ብ/ጀነራል ከተማ አይተንፍሱ = የ 606ኛ ኮር ዋና አዛዥ

9. ብ/ጀነራል ከበደ ወ/ጻዲቅ = የ 606ኛ ኮር ዋና ም/አዛዥ

10.ብ/ጀነራል ሰለሞን ደሳለኝ = የ 102ኛ አየር ወለድ ክ/ጦር ዋና አዛዥ

11. ዶ/ር ኮሎኔል ጌታቸው አወቀ = የሁአሰ ሆስፒታል ሜዲካል ዳሬክተር

12. ኮሎኔል መስፍን አሰፋ = የ2ኛ ሜካናይዝድ ክ/ጦር አዛዥ

13. ኮሎኔል ፈቃደ እንግዳ = የሁአሰ ዘመቻ መምሪያ ረ/ኃላፊ

14. ሌ/ኮ ዘርአይ እቁባአብ = የሁአሰ ቀዳሚ መምሪያ ፖለቲካ ኃላፊ

15. ሌ/ኮ ዮሀንስ ገብረማሪያም = የመከላከያ ቀዳሚ መምሪያ ወታደራዊ መረጃ ኃላፊ

16.ሻለቃ ካሳ ፈረደ = የሁአሰ መሀንዲስ መምሪያ ኃላፊ

17. ሻለቃ ሚካኤል ማርቦ = የ 2ኛ ታንከኛ ብርጌድ ፖለቲካ መምሪያ ኃላፊ

18. ሻምበል ጌታሁን ግርማ = የሁአሰ ዋና አዛዥ ልዩ ረዳት

መምሪያ ኃላፊ

በተመሣሣይ መንገድ ግንቦት 8/1981 ዓ.ም ከመከላከያ ሚኒስቴር ጊቢ ውስጥ በሻምበል መንግስቱ ገመቹ የሚመራው የልዩ ጥበቃ ብርጌድ በቁጥጥር ስር የዋሉት

1/ ሜጀር ጀነራል ኃይሉ ገ/ሚካኤል = የምድር ጦር ዋና አዛዥ

2/ ሜጀር ጀነራል ወርቁ ዘውዴ = የፖሊስ ሰራዊት ጠቅላይ አዛዥ

3/ ሜጀር ጀነራል ዓለማየሁ ደስታ = የምድር ጦር ምክትል አዛዥ

4/ ሜጀር ጀነራል ዘውዴ ገብረየስ =የ 603ኛ ኮር ዋና አዛዥ

5/ ብ/ጀነራል ደሣለኝ አበበ = የጦር ኃይሎች አካዳሚ ዋና አዛዥ

6/ ብ/ጀነራል ሰለሞን በጋሻው = የአየር ኃይል ምክትል አዛዥ

7/  ብ/ጀነራል ተስፋ ደስታ = የአየር ኃይል ዘመቻ መኮንን

8/ ብ/ጀነራል እንግዳ ወ/አምላክ = የ606ኛ ኮር ዋና አዛዥ /ሁአሰ

9/ ብ/ጀነራል እርቅይሁን ባይሣ = የ607ኛ ኮር ዋና አዛዥ /ሁአሰ

10/ ብ/ጀነራል ነጋሽ ወልደየስ = የ 608ኛ ኮር ዋና አዛዥ /ሁአሰ

11/ ብ/ጀነራል ገናናው መንግሥቴ = የ6ኛው አየር ምድር ዋና አዛዥ /ሁአሰ

12/ ብ/ጀነራል ተስፋዬ ትርፌ = በአገር መከላከያ ሚኒስቴር ዘመቻ መኮንን

ለአንድ አመት ያህል ባስቻለው የጦር ፍርድ ቤት የእስር ውሣኔ ቢመስንባቸውም በፕ/ት መንግስቱ ኃ/ማርያም ቀጥተኛ ፖለቲካዊ ትእዛዝ ግንቦት 1982 ዓ.ም በግፍ ተጨፍጭፈው ተረሽነዋል ።

የዚህ ሁሉ የጦር ጠበብቶች እልቂትም ግዙፋን ሰራዊት ያለ እውነተኛ መሪ በማስቀረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ውድቀት ዳርጎታል ።

ይህ ቀን በአብዮታዊው ሰራዊት ታሪክ ጥቁር ቀን ተብሎና የማይጠገን ጠንካራ ስብራት ጥሎ ያለፈ አሳዛኝ ቀን በመሆን ተመዝግቦ አልፋል ።

ፈጣሪ የሀገር ባለውለታ የነበሩትን የመፈንቅለ መንግስቱ ሰለባ ጀነራል መኮንኖችን ፤ ከፍተኛ መኮንኖችን እና መስመራዊ መኮንኖችን ነፍስ ይማር !

ታሪክን_ወደኋላ 

©️ አብዮታዊው ሰራዊት ገፅ

Filed in: Amharic