>

የግፍ እስረኛው ቢንያም ታደሰ በፖሊስ ተደበደበ!! መአዛ መሀመድ

የግፍ እስረኛው ቢንያም ታደሰ በፖሊስ ተደበደበ!!

መአዛ መሀመድ


በጎንደር ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ተከትሎ”‘ኦርቶዶክስ ተነስ’ በማለት የሃይማኖት ብጥብጥ ፈጥረሃል” በሚል የቅጥፈት ውንጀላ ከአለፈው ሚያዚያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ፤ ማዕከላዊ በእስር ላይ የሚገኘው ወጣት ቢንያም ታደሰ ማታ ማታ በተደጋጋሚ በፖሊስ እንደሚደበደብ ተናግሯል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በድብደባው የከፋ አካላዊ ጉዳት አልደረሰበትም።

ወጣቱ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አባል ከመሆኑ ጋር የተያያዙ በርካታ ጥያቄዎች በመርማሪ ፖሊሶች በሌሊት እየተወሰደ እንደሚቀርብለትም ገልጿል። ከእነኝህ መካከል “ባልደራስን መቼ ተቀላቀልክ?፣ ለምን ከእስክንድር ነጋ አትርቅም?፣ ከባልደራስ ትዕዛዝ እየተቀበልክ ብጥብጥ ታስነሳለህ ወይ?” የሚሉ ይገኙበታል።

በዱላ ለታጀቡ እነዚህ ጥያቄዎች የወጣቱ ምላሽ “እኔም ሆንኩ ፓርቲዬ ባልደራስ ብጥብጥ አስነተን አናውቅም። ወደ ፊትም አናስነሳም። ብጥብጥን እንፀየፈዋለን። አባቢን (እስክንድርን ማለቱ ነው) እስከቀራኒዮ እከተለዋለሁ” የሚል እንደነበር አረጋግጠናል።

በተጨማሪም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረባ የሆኑ መርማሪ ፖሊሶች ከሕግ ውጭ በሌሊት ብቻውን አስወጥተው ከሚጠይቁት ጥያቄዎች መካከል “ፋኖ ነህ፤ የደበቅከውን ጠመንጃ አምጣ” የሚል ይገኝበታል።

ለዚህም “እኔ የከተማ ውስጥ ሰላማዊ ታጋይ ነኝ። ጠመንጃም የለኝም። ፋኖነት ደግሞ ሀገር ጠባቂነት እንጂ ወንጀል አይደለም”  በማለት መልሶላቸዋል። ይሁን እንጂ በሀሰት ክስ ላይ አስገድደው ለማሳመን የተነሱ ፖሊሶች በምላሾቹ ባለመደሰት በተደጋጋሚ እየደበደቡት መሆኑን የግፍ እስረኛው ቢንያም ታደሰ ተናግሯል።

ቢንያም ባለፈው ሚያዚያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ወንጀል ችሎት ቀርቦ የነበረ ሲሆን “የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ለማሰባሰብ” በሚል የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶታል። በዚሁ መሰረት የፊታችን ግንቦት ዘጠኝ ቀን 2014 ዓ.ም. ተመልሶ ችሎት ይቀርባል።

Filed in: Amharic