>

ይድረስ ለኦሮሞ አባቶችና ልሂቃን (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

ይድረስ ለኦሮሞ አባቶችና ልሂቃን

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ


ምን ብዬ እንደምጀምር ጨንቆኝ ከወረቀቱ ጋር ተፋጥጬ ብዙ ቆየሁ፡፡ ግን መጀመር አለብኝና እንደምንም ጀመርኩ፤ ሰላምታየን ላስቀድም ታዲያንም፡፡ ደግሞም እንኳን ለጠንቀኛዋ የግንቦት ወር በሰላም አደረሳችሁ፡፡

ዘሩ በያይነቱ ተዘራ፡፡ ቡቃያው አደገ፡፡ ሰብሉም ጎመራ፡፡ እነሆ የዐውድማው ወቅት ደረሰ፡፡ ዘሪውም ወቂውም ደስ ይበለው፡፡ ታዛቢም ይታዘብ፤ ታሪክም ይመዝግብ፡፡ ሁሉም ሆኖ አንድ ነገር ብቻ ቀረ – የኢትዮጵያ ማይቀር ትንሣኤ፡፡

ኢትዮጵያን በተለይም አማራን የማጥፋቱ ዕቅድ ከመቶዎች ዓመታት በፊት በኃያላኑ የስለላ ድርጅቶች ተጠንስሶ፣ በሀገር ውስጥ ከሃዲዎችና ሆዳሞች ተደግፎ ይሄውና ወደመገገባደጃው ተጠግቷል፡፡ ኢትዮጵያን ስለማጥፋት ዕቅድና ዓለም አቀፍ ሤራ አሁን አንተነትንም፡፡ ብዙ ስለተነገረለት ግልጽ ነውና፡፡ በዚህ ታላቅ ሤራ ተሣታፊ ከሆኑት ወገኖች መካከል ግን በአሁኑ ወቅት ወጧ እንዳማረላት ሴት ከወዲያ ወዲህ በደስታ ሰክረው የሚያደርጉትን ያጡትን የኦሮሞ አክራሪዎች በተመለከተ አጭር ማስታወሻ መጻፍ ፈለግሁ፡፡ በመሠረቱ ምንም መናገር  ባልተገባኝ፡፡ ግን ጥቂት መሃል ሠፋሪዎችንና ቅርብ ተመልካቾችን ማዳን ከቻልኩ መጻፌ ካለመጻፌ ይሻላል፡፡ “ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል” ይባል የለም? እንጂ የሀገራችንን ችግር በመዘርዘርና መፍትሔዎችንም በመጠቆም ብዙ ባጅተናል፡፡ ሰሚ በመጥፋቱ ግን የተባለው ሁሉ ላይቀር ግድ ሆኗል፡፡ ስለሆነም ከንጋት በፊት የመጨረሻ ያልኩትን አስተያየት መቀጠሌ ነው፡፡ በትግስት ተከታተሉኝ፤ የሰማችሁም ላልሰማ ወገኔ አድርሱልኝ፡፡

ውድ የኦሮሞ አባቶችና ወንድሞች!

እንደጨለመ የቀረ ሌሊት የለም፡፡ እንደቦረቀ ዝንታለሙን የቆዬ ጥጃም ታይቶ አያውቅም፡፡ የወጣ መውረዱ፣ የወረደ መውጣቱ ያለና የነበረ ነው፡፡ ይህን እውነት ማንም ይረዳዋልና ለማስታወስ ያህል እንጂ አዲስ ነገር እንዳልተናገርኩ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡

ልጆቻችሁና ልጆቻችን የኦሮሞ አክራሪ ወጣቶች ከአራት ኪሎ እስከ ደምቢዶሎ ምን እየሠሩ እንደሆነ ታውቃላችሁ፡፡ አገር ጠባቸው ይሆኑትን አጥተዋል፡፡ በጥላቻ ነፍዘው፣ በዘር ፖለቲካ ሃሽሻዊ መርዝ ደንዝዘው፣ በሀብትና በሥልጣን ስካር ናውዘው የሚሠሩትን ያጡት በኦሮሙማ ፍልስፍና ህልም አይባል ቅዠት የሚቅበዘበዙት አክራሪ ኦሮሞዎች አሁን አሁን በተለይ ኅሊናቸው ታውሮ የሚያደርጉትን አጥተዋል፡፡ በመሆኑም ተፋቅሮና ተከባብሮ እርስ በርስ እየተጋባና እየተዋለደ የኖረውን የኢትዮያ ሕዝብ ከወያኔ ዘመንም በከፋ ደረጃ በዘርና በጎሣ፣ በሃይማኖትና በጎጥ ከፋፍለው ሀገራችንን የለየላት ሦርያና የመን አድርገዋታል፡፡ በእግዚአብሔር ልዩ ቸርነት እንዳለን ተቆጠርን እንጂ በመካከላችን እንደገባው ንፋስ ቢሆን ኖሮ አንድም ቀን ማደራችን አጠራጣሪ በሆነ ነበር፡፡

ውድ ወገኖቼ! ምድር ጠባቸው ለታዛቢ እስኪገርም ድረስ የእግዜሩን ዐይን እየወጉ ያሉ ባለጊዜ ልጆቻችንን እንምከር፡፡ የዱባ ጥጋብ የትም እንደማያደርስ እንንገራቸው፡፡ አሁን የያዙትን መሣሪያ፣ አሁን የተቆናጠጡትን ሥልጣን ለውድመት መጠቀማቸውን እስከቀጠሉበት ድረስ ጊዜ ተለዋዋጭ ነውና የዕኩይ ተግባራቸው ውጤት ለአጠቃላዩ የኦሮሞ ሕዝብም እንደሚተርፍ በግልጽ እናስረዳቸው፡፡ ለኦሮሞ ማኅበረሰብ እያሰጡት ያለው ያልተገባ ስም በአብሮ ኗሪነቱ ለሚታወቀው ኦሮሞ በፍጹም አይመጥንም፡፡  

በሕወሓት ጦስ ትግራይና ሕዝቧ በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ የምናውቀው ነው፡፡ ጥጋብን ያለመቆጣጠር ችግር የሚያስከትለው መዘዝ ከፍተኛ መሆኑን ከደርግና ከወያኔ መማር ካልተቻለ የአእምሮ ጤንነት ተዛብቷል ማለት ነውና ችግሮች ከአሁኑ በባሰ ሳይከፉ እንመካከር፡፡ ጥጋብ ወደራብ መንዳቱ ዱሮም ነበር፡፡ አንዳንድ ጥጋብና ዕብሪት ግን በርሀብ ብቻ አይወሰንምና በብርቱ እናስብበት፡፡

ዛሬ እርግጥ ነው – ኢትዮጵያ የለችም፡፡ ትናንት በወያኔ እግር ከወርች ታስራ ለቅርጫ የቀረበችው ኢትዮጵያ ዛሬ ለይቶላት በኦሮሙማ አስተሳሰብ በሚነዱ ኃይሎች በአራት ዓመታት ውስጥ ብቻ ወያኔን ዕጥፍ ድርብ በሚያስከነዳ ጭካኔና መሪር ፈርዖናዊ አገዛዝ ሀገራችን እንጦርጦስ እየወረደች ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ከኦሮሙማ አገዛዝ የለየለት ሲዖላዊው የሠይጣን አገዛዝ ሳይሻል አይቀርም፡፡

የነገ አሸናፊን ከአሁኑ መናገር ለብዙኃን እፎይታን ቢሰጥም በአንዳንዶች ዘንድ ወቀሳን ማስከተሉ አይቀርም፡፡ እናም እርሱ ይቅር፡፡ የሆነው ቢሆን ግን የእውነትንና የግፍ ሰለባዎችን አሸናፊነት አለመመስከር የታሪክን ሂደት፣ የፈጣሪንም ፍትኃዊ ፍርድ እንደመካድ ይቆጠራልና ይህን ሃቅ በስሱም ቢሆን ማስታወሱ አይከፋም፡፡ እናም እንወቀው እውነት በመጨረሻ ታሸንፋለች፡፡ …

ኦሮሙማዎች እጅግ ነብርረዋል፡፡ አይዟችሁ ያላቸው ለመኖሩ ግልጽ ነው፡፡ ግን ያ ኃይል አሁን በዩክሬን ጉዳይ ዳር ሆኖ ከማጨብጨብና “በርቱ ግፉበት” ከማለት በዘለለ የብዙ ሰው ሕይወት ሲረግፍና በርካታ ንብረት ሲወድም አላስጣለም፡፡ ያ ዓለምን ለብቻየ ጠቅልዬ እንዳሻኝ መግዛት አለብኝ ብሎ የሚያምን ኃይል ጦርነትን መለኮስና ለጦርነት የሚውሉ ግብኣቶችን ማቀበል እንጂ በራሱ የትኛውንም ጦርነት ሲዋጋ አይስተዋልም፡፡  ያ ኃይል ባይኖር ኖሮ ዓለማችን ግሩም የመኖሪያ ሥፍራ ልትሆን እንደምትችል የብዙዎቻችን ግምት ነው፡፡ ግና አልታደልንም፡፡ በጥባጭ ሳለ ደግሞ ጥሩ ውኃ አይጠጣም፡፡ ስለሆነም ዩጎዝላቪያን፣ ሶማሊያን፣ ሦርያን፣ አፍጋኒስታንን፣ ሊቢያን፣ በጥቅሉ መላው ዓለምን በመሣሪያውና በተፅዕኖው ሥር አውሎ ምድርን የመከራና የስቃይ መናኸሪያ አድርጓታል፡፡ ይሁን፡፡ ቀድሞ የተነገረው የመጨረሻ ዘመን ምልክቶች መገለጫ በመሆኑ ወደላይኛው ከመጮህ ውጪ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ ቢሆን የዚህም ጣዖታዊ ኃይል ክንዶች የሚሰባበሩበት ጊዜ እየቀረበ መሆኑን መጠቆም እምብዝም ሟርተኛ አያስብልም፡፡

ወደሀገራችን ስንመለስ የተለዬ ነገር አናገኝም፡፡ ሁሉም እንቅስቃሴዎቻችን ከዐውሬው የታለመና የታቀደ እንቅስቃሴ ጋር የተሰናኙ ናቸው፡፡ አሁን አሁን የሀገራችን ሁኔታ ሲቃኝ ነገሩ ሁሉ የህልም እንጂ የእውን አይመስልም፡፡ መሪ የሌላት ብቻ ሳትሆን መሪዋ ፀረ-ሀገርና ፀረ-ሕዝብ የሆነ ሰው ሆኖ ስትመለከት ከህልምም በላይ ነው፡፡ ባለሥልጣኖቿ ሁሉ ፀረ-ሕዝብና ፀረ-ሀገር ሆነው ስታይ ትደነግጣለህ፤ ትጨነቃለህም፡፡ የፖለቲካ ተሹዋሚው በአብዛኛው ጭንቅላቱን ሆዱ ውስጥ ሸጉጦ በሆዱና በዘር ማንነቱ ብቻ ሲያስብ ስታይ ሰው ሆነህ በመፈጠርህ ዝቅ ሲልም ኢትዮጵያ ውስጥ በመፈጠርህ ራሱ ትሸማቀቃለህ፡፡ ሀገር(ህ) ውስጥ ሀገር አልባ ሆነህ የበይ ተመልካችና ከዚያም በከፋ በማንነትህ ስትገደልና ከሥራም ከመኖሪያ ሥፍራም ስትፈናቀል “የት ነው ያለሁት?” በሚል ክፉኛ ትጨነቃለህ፤ መፈጠርህንም ትራገማለህ፡፡ ሰው መሃል ሆነህ ሰው የሚናፍቅህ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ይመስለኛል፡፡ 

ግን የዛሬው እውነት ነገም ይቀጥላል ማለት አይደለም፡፡ ነገም ሌላ ቀን መሆኑ ተደጋግሞ የሚነገረው ለዚህ ነው፡፡ ታላቅ አውነት ነው፡፡ እናም ነገ ላለማፈር መሠረቱ የሚጣለው ዛሬ ነውና በስም የጠቀስኳችሁ ወገኖቼ ይህችን ቀጭን ጊዜ በሰላም እንድናልፍ ልጆቻችንን ምከሩ፡፡ ኦቦ ደቻሣ ልጅዎን ይጥሩና ስለቀደመችዋ የጋራ ኢትዮጵያ ይንገሩት፡፡ ጠላት ለራሱ ዓላማ ሲል ጭንቅላቱ ውስጥ የሸቀሸቀበትን መርዘኛ ፕሮፓጋንዳ ውሸት መሆኑን ያስረዱት፡፡ በሀገራችን ጡት ቆራጭ እንዳልነበረም ይግለጹለት፤ ጡት ቆራጭና ጽንስ ከእናት ማኅጸን አውጥቶ የሚበላ፣ ሰውን በግፍ ከገደል በኋላ ዘቅዝቆ የሚሰቅልና ያም አልበቃው ብሎ ሬሣውን በመኪናና በሞተር የሚጎትት ሰይጣናዊ ትውልድ የመጣው አሁን በዚህ ዘመን መሆኑን ይንገሩት፡፡ በዳይና ተበዳይ ካለም ሁሉም ሁሉንም በድሏል እንጂ እንዳሁኑ ዘመን በዘር የተቧደነ ጎራ በሌላ ዘር ላይ ተነስቶ ጥፋትና ውድመትን እንዳላስከተለ ይመስክሩለት፡፡ ኢትዮጵያን የገዙት ነገሥታትና የጦር አበጋዞች በአብዛኛው ኦሮሞዎች እንደነበሩ የትናንትናዎቹን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤንና መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን በመጥቀስ ያስረዱት፡፡ ውድ ሰርቤሣ – ልጅህን ጫልቱን ጥራትና አጠገብህ አስቀምጠህ ለኦቦ ደቻሣ የጠቆምኩትን እያነሳህ ምከራት፡፡ 

በተረፈ አንድ ጄኔራልና አንድ ኮሎኔል ማፈን፣ በአንድ በኩል የራስን ወምበዴ እየቀለቡና ዘመናዊ ጦር መሣሪያ እያስታጠቁ በርሱም አማካኝነት ማጥፋት የሚፈልጉትን ነገድ በየቦታው እያስፈጁ በሌላ በኩል ከመኖሪያ አካባቢው ያልወጣን የአንድን ነገድ አለኝታ ኃይል ማሰርና ማንላታት፣ ጥቂት ጋዜጠኞችንና የሰብኣዊ መብት ተማጋቾችን ደብዛ ማጥፋት ወዘተ. የነጻነት ትግልን ያጠናክራል እንጂ አንድ ጋት ወደኋላ አያስቀረውም፡፡ በማፈንና በመግደል ፍላጎት የሚሣካ ቢሆን ኖሮ ከደርግና ከወያኔ በላይ ለሽዎች ዓመታት የሚገዛ ባልነበረ፡፡ ከሚያጥበረብሩ የቀን ቅዠቶች እንላቀቅ፡፡ የሚታይ የሚመስል ሁሉ ውሸት ነው፡፡ ያለን የሚመስለን ሁሉ የለንም፡፡  ስሜታዊነት ማንንም ጠቅሞ አያውቅም፡፡ ምክንያታዊነት ግን ትልቅ ምርኩዝ ነው፡፡ የማንኛውም ዘመን ሰው መሆን ዕድለኛነት ነው፡፡ በየትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው የውር ድምብር አካሄድ እየተመሩ ዛሬን መክበርና ነገን ማበላሸት ከጤናማ ሰው አይጠበቅምና በጊዜያዊ ድል ስካር ያበዳችሁ ኦሮሞ ወንድሞቼ ወደኅሊናችሁ ተመለሱ – ብዙም ሳይረፍድ ታዲያ፡፡ እዩኝ እዩኝ ማለት ደብቁኝ ደብቁኝን እንደሚያስከትል ካላወቅን ተሳስተናል፡፡ 

ሳይወለድ የጨነገፈው ብአዴንም አያዋጣችሁም፡፡ በአንድ ጥፊ የሚዘረር ሰካራም እንኳንስ እናንተን የቁርጡ ቀን ሲመጣ ራሱንም አያድንም፡፡ … ይሄ ሰውን ማፈናችሁን የተበላ ዕቁብ የሕጻናት የዕቃቃ ጨዋታ ደግሞ በፈጠራችሁ ተውት፡፡ የሚያስቅ ግን ጊዜ ያለፈበት ድራማ ነው፡፡ ከአባታችሁ ከወያኔ ተማሩ እንጂ! የዘሩትን ማጨድ እንዳለ እንዴት ዘነጋችሁት? አንድ ተፈራ ሲታፈን ሽህ ተፈራዎች ወደ አደባባይ እንደሚወጡ ካላወቃችሁ፣ አንድ ጎበዜ ሲታፈን ሽህ ጎበዜዎች ወደ በረሃ እንደሚተሙ ካልተረዳችሁ አእምሯችሁ በርግጥም ሥራውን አቁሟል ማለት ነውና ወገን ካላችሁ አሁኑኑ ወደሀኪም ቤት ይዟችሁ ይሂድ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ በኦሮሙማ ፖለቲካ ጥርሳቸውን ተወቅረው ከሚስቁ ወገኖች መካከል አንዱ መሆኔን ልደብቅ አልፈልግም፡፡ የሚሠሩት ሁሉ የሚያሳዝነውና የሚያስለቅሰው እንዳለ ሆኖ አብዛኛው ግን በሣቅ ጦሽ የሚያደርግ ነው፡፡ በዋና ከተማ ውስጥ በመከላከያ መኪና አሥርና አሥራ አምስት እንደነገሩ የለበሱ ከዕውቀትም ከትምህርትም የተፋቱ ባለጊዜዎች አንድን ሰው አፍነው ሲወስዱ ይታያችሁ፡፡ ይህ ሕጻንነቱን ሳይጨርስ የመርከቢቷ መሪ የጨበጠ ጎልማሣ ሰውዬ ገና ብዙ ጉድ ሳያሳየን አይቀርም፡፡ እርግጥ ነው – እርግጥ ነው – መንገድ ጠራጊው ሲሄድ ግሩም ዘመን ይተካል፡፡ ይህንንም በኩራት እንመሰክራለን፡፡ አሸናፊውንም እናውቃለን፡፡ የዚያ ሰው ይበለን፡፡  …     

Filed in: Amharic