ይድረስ ለአማራ ፋኖ!
ከብሥራት ደረሰ
ከዚህ አንቀጽ በታች ያለውን አጭር ጦማር የጻፍኩት ከጥቂት ቀናት በፊት ነበር፡፡ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ በተለቀቀ ማግሥት አካባቢ ነው የጫጫርኩት፡፡ አሁን ላይ ሆኜ ያለፉትን ጥቂት ቀናት ስመለከት ነገሮች በጣም ተለዋውጠዋል፡፡ የነገሮች መለዋወጥ ደግሞ እጅግ እየፈጠነ ነው – በብርሃን ፍጥነት በምንለው አገላለጽ የኢትዮጵያ ጉዳይ ወደመጨረሻው ምዕራፍ እየተዳፋ ይመስላል፡፡ የታያቸውን አላውቅም የኦሮሙማው ኦህዲድ/ኦነግ ሸኔ ሰዎች በጣም እየተጣደፉ ናቸው፡፡ ሞት ሲቃረብ ሁለመናን ያጃጅላል፡፡ እናም እስርና አፈናውን በስፋት ቀጥለውበት ሀገሪቱ ብዙ አንጡራ ሀብት ያፈሰሰችባቸውን የጦር አበጋዞችና ምሁራን በጠራራ ፀሐይ እያፈኑና እየደበደቡ ይገኛሉ፡፡ ከጠገቡ አይቀር ደሞ እንደዚህ ነው – የምን ቁጥ ቁጥ ነው – እንደዚህ በጅምላ እያፈሱ ማጎር ነው እንጂ፤ አብዛኛው አማራና ሌላውም ኢትዮጵያዊ ተራው እስኪደርሰው እንደቤቶች ድራማ ባለታሪክ እንደእከ ለሽ ብሎ ይተኛ፡፡ ኦሮሙማዎች አማራን ከመናቃቸው የተነሣ በደንገጡራቸው በብአዴን አማካይነት የአማራን ክልል ተቆጣጥረው የፈለጉትን እያደረጉ ናቸው፡፡ የአማራ ክልልን የደምብ ልብሶች በማልበስ ኦነግ ሸኔን በአማራ ፋኖና በአማራ ሕዝብ ላይ እዚያው እክልሉ ድረስ ገብተው እንዲሸናና እንዲጸዳዳ እያደረጉ ይገኛሉ፤ ይህን ሁሉ ድፍረትና ልበ ድፍንነት ከየት እንዳገኙት ሳስበው ይገርመኛል፡፡ ያለድካምና ያለችሎታ ከባዶ ሜዳ የተገኘ ሥልጣንና ሀብት ለካንስ እስከዚህ ያባልጋል! የዚህ የተካለበ ኦሮሙማዊ ሩጫ ወዴት እንደሚያደርሰን ጥቂት ጊዜያትን መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ ለማንኛውም ባለፈው ሰሞን የጻፍኩትን ማስታወሻ ከዚህ በታች አስቀምጫለሁና ማንበብ የሚፈልግ ያንብብ፡፡
በቅድሚያ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እንኳን ወደ ቤቱ ገባ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ብዙ ተጨንቀን ነበርና እንደራሱ አባባል ምንም ጉዳት ሳይደርስበት በታፈነ በዘጠንኛው ቀን ወደቤቱ መግባቱ እሰዬው የሚያሰኝ ነው፡፡ ጋዜጠኛንና የመብት ተሟጋቾችን ማፈንና ደብዛቸውን ማጥፋት የወሮበላ መንግሥታት ጠባይ በመሆኑ ፈጣሪ ይጠብቀን እንጂ አሣራችን ገና ብዙ ነው፡፡ እኒህ ሰዎች ካላለቅንላቸው አይለቁንም፡፡
አማራን ከምድረ ገጽ በማጥፋት ኦሮምያ የምትባለውን ታላቅ የምሥራቅ አፍሪቃ ኢምፓየር ለመመሥረት የሚደረገው የኦሮሙማ ዘመቻ ግቡን ሊመታ እግዜር አይበለው እንጂ አንድ ክረምት ብቻ የቀረው ይመስላል፡፡ በዚያም ምክንያት ሁሉም የኦሮሙማ አባላትና ለከርሳቸው ያደሩ ምስለኔዎቻቸው አቅል የሳተ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እነተመስገን ጥሩነህና አገኘሁ ተሻገር፣ እነአበባው ታደሰና በርካታ የብአዴን አባላት ለዚሁ ዘመቻ ስኬት አቅላቸውን ስተው በመንቀሳቀስ አማራን እያሳረዱና ንብረቱንም እያወደሙ ናቸው፡፡ የመጨረሻውን ውጤት አሳምረን ብናውቀውም ወደዚያ ውጤት ከመደረሱ በፊት ያለውን የጨለማ ጊዜ እንረዳለንና መደናገጣችን አይቀርም፡፡ ይህም መደናገጣችን ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ፈጣሪ በቃችሁ ብሎ ይህን ጨለማ በቶሎ እንዲያነጋው ሁላችንም ወደርሱ እንጸልይ፡፡ እርሱ ይቻለዋልና፡፡
የአማራ ፋኖ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ትልቁ እርሾ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከውድመት ለማዳን የተሠለፉ በግልጽ የሚታወቁም የማይታወቁም ኃይሎች አሉ፡፡ ከነዚህ አንዱ የዳግማዊ ግራኝ አህመድ መንግሥት ክፉኛ የሚፈራውና ሊያጠፋው ዕቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰበት የሚገኘው የአማራ ፋኖ ነው፡፡ ስለሆነም ፋኖ መጠንቀቀቅ አለበት፡፡ ሊሆን ያለው ሁሉ ከመሆን የሚያግደው ነገር ባይኖርም ፈጣሪ ራሱ ራሳችን ለራሳችን እንድንጠነቀቅ ባዘዘን መሠረት ለራሳችን መጠንቀቁ አይከፋምና ፋኖዎች ራሳችሁን ጠብቁ፡፡ ሰውን ውደዱ እንጂ አትመኑ፡፡
ዋናው ጥንቃቄ መጀመር ያለበት ፋኖ ራሱንና ውስጣዊ አደረጃጀቱን በመፈተሸ ነው፡፡ ተመሳስለው ገብተው ጉድ እንዳይሠሩት ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ እርግጥ ነው – አማርኛ ቋንቋ የሁሉም ሀብት ንብረት እንደመሆኑ ይህን ቋንቋ የሚናገር ሁሉ አማራ ነኝ ብሎ ፋኖን በመቀላቀል ያልተጠበቀ ጉዳት ሊያደርስበት እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ በመሠረቱ ደግሞ አማራ የዘረኝነት አባዜ አያጠቃውምና ማንንም በፋኖ አባልነት መቀበሉ ለፋኖ ችግር ባይሆንም በዚህ መንገድ ከሚሠርጉ አባላት አደጋ ለመዳን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ለነገ የሚተው አይደለም፡፡ አማራን ያጠቃው ዋናው ነገር እንዲያውም የአማራ ዘረኛ አለመሆንና የአማርኛ ቋንቋ በሁሉም የአማራ ጠላቶች ዘንድ መነገሩ ነው፡፡ ስለሆነም በአመራርም ይሁን በአባልነት የሚገኙ የፋኖ ሰዎች ይህን ተስፋ የተጣለበት ህዝባዊ ተቋም አስመሳይ ሠርጎ ገቦችና የጠላት ተላላኪዎች በዕኩይ ምግባራቸው እንዳያበላሹትና ሕዝባዊ ተአማኒነቱን እንዳይሸረሽሩት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል፡፡ ከቅሚያና ዝርፊያ ራሱን ማራቅ አለበት፡፡ በስሙ ከሚነግዱ ሰዎችና ከዋልጌዎች ራሱን ይከላከል፡፡ በስመ ፋኖ ብዙ ተንኮልና ደባ ሊሠራ ይችላልና ትልቁ የፋኖ ዘመቻ ራሱን ማጽዳት ይሁን፡፡ ማንም ወለፈንዴ ተራ ሽፍታ በፋኖ ስም እንዳይፏልልና ስሙን እንዳያስጠፋ ይህ ነገር ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ መሪዎቹንም ይጠብቅ፡፡ ተክለ ሰውነት ግንባታ አይጠቅመውምና በዚህ ረገድ አቢያዊነትን የመሰለ የአምባገነን ስብዕና ግንባታ አጥብቆ ይዋጋ፡፡ አመራሮቹን ይለዋውጥ፤ መሪዎችንም እየመለመለ ዝግጁ ያድርግ፡፡ አንድ ጎበዝ አለቃ ሲሰዋ ሌላው በቶሎ ይተካ እንጂ በዚያ ላይ ማላዘንና ተስፋ መቁረጥ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ምሥጢራዊነትን ይጠብቅ፡፡ ሙስናንና ኢሞራላዊ አሠራሮችን ይጠየፍ፡፡ ሌላው ቀላል ነው፡፡
ፋኖ ለሥልት ያህል አማራ ይምሰል እንጂ አደረጃጀቱም ሆነ አሠራሩ ሀገራዊ እንደሆነ የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ አማራ ተጨንቆ አማራነትን አነሳ እንጂ የአማራ ሕዝብ በጎሠኝነት የሚታማ አይደለም፡፡ አማራነትና ኢትዮጵያዊነት ተዋህደው አንድ በመሆናቸው አማራዊነት የሁሉም ኢትዮጵያዊነት የጋራ ሀብት ነው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ የምትነሳው ለአንድ ወይ ለውሱን ነገዶች ሳይሆን ለ86ቱም ጎሣና ነገዶች ነውና የሁሉም ጎሣና ነገድ ጤናማ አባላት ከፋኖ ጋር ተባብረው ሀገራቸውን ነጻ ማውጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንንም ተግባር ፋኖ ሊዘነጋው አይገባም፡፡ ለምሣሌ አፋርንና ሱማሌን ከኢትዮጵዊነት መነጠል የሚችል እንዳልተገኘ እናውቃለን – ቅቤው እንኳን ሞክሮ አልተሳካለትም፡፡
ፋኖ ዐይኖቹ የንሥር ጉልበቱ የአንበሣ እንዲሆንና አእምሮውም የሰላ ሆኖ በሩቅ አሳቢነት በመጓዝ ሀገሩን ከውጭና ከውስጥ ምንደኛ ጠላቶች ነጻ እንዲያወጣ ሁላችንም ከጎኑ እንቁም፡፡ መልካም የነጻነት ትግል፡፡ ድል ለኢትዮጵያ ትንሣኤ ታጋዮች፡፡